ር.ሊ.ጳ ሊዮ '2ኛው የቫቲካን ጉባኤ የቤተክርስቲያኗን ጉዞ አሁንም እየመራ ነው' ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በዕለቱ የተነበበው የእግዚአብሔር ቃል
የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፥ ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው። በልዩ ልዩ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ መልካም የሚሆነው ልባችሁ በጸጋ ቢጸና ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚኖሩትም እንኳን አልተጠቀሙም (ዕብራዊያን 13፡7-9)።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
ወንድሞቼና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በኢየሱስ ሕይወት ምስጢሮች ላይ አተኩሮ ከነበረው የኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ፣ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ላይ ያተኮረ አዲስ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዑደት እና ሰነዶቹን እንደገና መመርመር እንጀምራለን። ይህ የቤተክርስቲያን ዝግጅት ውበት እና አስፈላጊነት እንደገና ለማወቅ ጠቃሚ አጋጣሚ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም የኢዮቤልዩ አመት መጨረሻ ላይ፣ “የሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ለቤተክርስቲያን የተሰጠ ታላቅ ጸጋ እንደሆነ ለማመልከት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብለው ነበር።
እ.አ.አ በ2025 ዓ.ም ከኒቂያ ጉባኤ አመታዊ በዓል ጋር፣ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰባኛውን ዓመት ዝክረ ዓመት በዓል አስታውሰናል። ከዚህ ክስተት የሚለየን ጊዜ ያን ያህል ረጅም ባይሆንም፣ የጳጳሳት፣ የሃይማኖት ሊቃውንት እና የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አማኞች ትውልድ ከእኛ ጋር አለመሆኑ ጭምር እውነት ነው። ስለዚህ፣ ትንቢቱ እንዳይጠፋ እና ግንዛቤዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ መንገዶችን እና ዘዴዎችን መፈለግን ስንሰማ፣ እንደገና በቅርበት ማወቅ እና በተሰጡ “የሰሚ ሰሚ” ወይም ትርጓሜዎች ሳይሆን፣ ሰነዶቹን እንደገና በማንበብ እና በይዘታቸው ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ ይሆናል። በእርግጥም፣ ዛሬም የቤተክርስቲያኒቱ ጉዞ መሪ ኮከብ የሆነ አስተምሮ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንዳስተማሩት፣ “ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ፣ የስምምነት ሰነዶች ወቅታዊነታቸውን አላጡም፤ በእርግጥም ትምህርቶቻቸው በተለይ ለቤተክርስቲያኒቱ አዲስ ሁኔታ እና አሁን ላለው ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ ጠቃሚ መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤን እ.አ.አ በጥቅምት 11 ቀን 1962 ዓ.ም ሲያስጀምሩ ለመላው ቤተክርስቲያን የብርሃን ቀን ማለዳ እንደሆነ ተናግረዋል። ከሁሉም አህጉራት አብያተ ክርስቲያናት የተሰባሰቡ በርካታ አባቶች ሥራ ለአዲስ የቤተክርስቲያን ወቅት መንገድ ጠርጓል። በሃያኛው ክፍለ ዘመን በተካሄደው የበለጸገ የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የቲዎሎጂ (ነገረ መለኮት) እና የአምልኮ ሥርዓት ነጸብራቅ በኋላ፣ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በክርስቶስ ልጆቹ እንድንሆን የሚጠራን አባት አድርጎ የእግዚአብሔርን ፊት እንደገና ገለጸልን፣ በክርስቶስ ብርሃን ውስጥ ያለችውን ቤተክርስቲያን፣ የአሕዛብ ብርሃን፣ በእግዚአብሔር እና በሕዝቡ መካከል የኅብረት እና የአንድነት ምስጢር አድርጎ ተመልክቷታል፤ አስፈላጊ የሆነ የአምልኮ ሥርዓት ተሃድሶን ጀምሯል፣ የመዳን ምስጢር እና የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ንቁ እና ንቃተ ህሊና ያለው ተሳትፎ መሃል ላይ አስቀምጧል። በተመሳሳይ ጊዜ፣ ለዓለም ክፍት እንድንሆን እና የዘመናዊውን ዓለም ለውጦች እና ተግዳሮቶች በውይይት እና በጋራ ኃላፊነት እንድንቀበል ረድቶናል፣ እንደ ቤተክርስቲያን፣ እጆቿን ለሰው ልጆች ለመክፈት፣ የሰዎችን ተስፋ እና ጭንቀት ለማስተናገድ እና የበለጠ ፍትሃዊ እና ወንድማማች ማህበረሰብ ለመገንባት እንደምትፈልግ የገለጸ ጉባኤ ነበር።
ለሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ምስጋና ይግባውና፣ ቤተክርስቲያን “የምትናገረው ነገር፣ የምትሰጠው ትምሕርት፣ የምታደርገው ግንኙነት አላት” ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደ ተናገሩት። በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ጋር እውነትን ለመፈለግ ትጥራለች። ይህ መንፈስ፣ ይህ ውስጣዊ ዝንባሌ፣ መንፈሳዊ ሕይወታችንን እና የቤተክርስቲያኒቱን የእረኝነት ተግባር የሚገልጽ መሆን አለበት፣ ምክንያቱም በአገልግሎት መልኩ የቤተክርስቲያን ተሃድሶን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ስላልቻልን እና ዛሬ ባሉ ተግዳሮቶች ፊት፣ የጊዜ ምልክቶችን በንቃት የምንተረጉም፣ የወንጌል ደስተኛ ሰባኪዎች፣ ደፋር የፍትህ እና የሰላም ምስክሮች እንድንሆን ተጠርተናል። በጉባኤው መጀመሪያ ላይ፣ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የቪቶሪዮ ቬኔቶ ጳጳስ የሆኑት የእኔታ አልቢኖ ሉቺያኒ፣ በትንቢት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፣ “እንደተለመደው፣ ብዙ ድርጅቶችን ወይም ዘዴዎችን ወይም መዋቅሮችን ማሳካት ቢቻ ሳይሆን ጥልቅ እና የበለጠ ሰፊ ቅድስናን ማሳካት ያስፈልጋል። ... ምናልባት የአንድ ጉባኤ እጅግ በጣም ጥሩ እና የተትረፈረፈ ፍሬዎች ከዘመናት በኋላ የሚታዩ እና ግጭቶችን እና አሉታዊ ሁኔታዎችን በድካም በማሸነፍ የሚበቅሉ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ተናግረው ነበር። እንግዲህ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት፣ ጉባኤውን እንደገና ማግኘት “ለእግዚአብሔር ቅድሚያ መስጠትን፣ አስፈላጊ የሆነውን ነገር፣ ጌታዋን እና የሚወዳቸውን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ እጅግ የምትወድ ቤተክርስቲያን” እንድንሆን ይረዳናል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ወንድሞችና እህቶች፣ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ለጉባኤ አባቶች በጉባኤው መጨረሻ ላይ የተናገሯቸው ቃላት ዛሬም ለእኛ መሪ መርህ ሆነው ቀጥለዋል። ከጉባኤው ወጥተው የወንጌልን መልካም ዜና ለሰው ልጅ ለማቅረብ ጊዜው እንደደረሰ አረጋግጠዋል፣ ያለፈው፣ የአሁኑ እና የወደፊቱ ጊዜ የተጠቃለለበትን የጸጋ ጊዜ እንዳሳለፉ በመገንዘብ፡“ያለፈው ጊዜ፡ በዚህ ቦታ ተሰብስበን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከባህሏ፣ ከታሪኳ፣ ከጉባኤዎቿ፣ ከሊቃውንቶቿ፣ ከቅዱሳኖቿ ጋር አለን፤ የአሁኑ ጊዜ፣ ወደ ዛሬው ዓለም ስንሄድ መከራዋን፣ ስቃዩን፣ ኃጢአቷን፣ እንዲሁም አስደናቂ ስኬቶቿን፣ እሴቶቿን፣ በጎነቶቿን ይዘን እንድንሄድ እርስ በርሳችን መተባበር አለብን፣ በመጨረሻም የወደፊቱ ጊዜ የዓለም ሕዝቦች ለበለጠ ፍትህ፣ ለሰላም ባላቸው ፍላጎት፣ ለከፍተኛ ሕይወት ባላቸው ንቃተ ህሊና ወይም ሳያውቁት ጥማቸው፣ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ልትሰጣቸው የምትፈልገውን ሕይወት በአስቸኳይ ጥሪ ውስጥ ማግኘት ነው” ሲሉ ጸፈው ነበር።
ይህ ለእኛም እውነት ነው። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነዶችን ስንቃኝ እና ትንቢታዊ እና ዘመናዊ ጠቀሜታቸውን እንደገና ስናገኝ፣ የቤተክርስቲያኗን ሕይወት የበለፀገ ባህል በደስታ እንቀበላለን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ስለአሁኑ ጊዜ ራሳችንን እንጠይቃለን እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል፣ የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰላም መንግሥት ለማምጣት ወደ ዓለም በመሮጥ ደስታችንን እናድሳለን።
