ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ' የእግዚአብሔር ቃል የሕይወታችን መመሪያ ነው' ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስለ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነዶቹ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረግ መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 20/2018 ዓ.ም ከእነዚህ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰንዶች መካከል "ስለ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ቃል መገለጥ" በሚገልጸው ዶግማዊ ሕገ ደንብ ዐብይ አርእስት ላይ ተንተርሰው "አንድ ቅዱስ ሀብት፤ በቅዱሳት መጻሕፍትና በቱፊት መካከል ያለው ግንኙነት" በተሰኘው ንዑስ አርስት ላይ ያተኮረ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን 'የእግዚአብሔር ቃል የሕይወታችን መመሪያ ነው' ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በዕለቱ የተነበበው የእግዚአብሔር ቃል

ኢየሱስ ለደቀ-መዛሙርቱ እንዲ አለ "በእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል" (ዩሐንስ 14፡25-26)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣ እንኳን ደህና መጣችሁ!

በላቲን ቋንቋ " Dei Verbum" (የእግዚአብሔር ቃል) ስለ መለኮታዊ ራዕይ በሚናግረው የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰንድ ላይ ማድረግ የጀመርነውን አስተምህሮ ዛሬም በመቀጠል ዛሬ በቅዱስ መጽሐፍ እና በቱፊት መካከል ስላለው ግንኙነት እናሰላስላለን። ሁለት የወንጌል ትዕይንቶችን እንደ ዳራ ልንወስድ እንችላለን። በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ በተከናወነው፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ባደረገው ታላቅ ንግግሩ-ኪዳኑ ላይ እንዲህ ሲል አረጋግጧል፡- “በእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። … የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ. 14፡25-26፤ 16፡13)።

ሁለተኛው ትዕይንት በምትኩ ወደ ገሊላ ተራሮች ይወስደናል። ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ራሱን ለደቀ መዛሙርቱ ገለጠ፣ ተገርመውና ተጠራጣሪ ለሆኑት፣ እንዲህ ሲል መክሯቸዋል፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ… ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” (ማቴ. 28፡19-20) በማለት ተናግሯቸው ነበር። በእነዚህ በሁለቱም ትዕይንቶች፣ ክርስቶስ በተናገራቸው ቃላት እና ባለፉት መቶ ዘመናት ቅዱስ ወንጌል በተሰራጨባቸው ቦታዎች መካከል ያለው የቅርብ ትስስር ግልጽ ነው።

የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ቀስቃሽ ምስልን በመጠቀም የሚያረጋግጠው ይህ ነው፡- “በቅዱስ ቱፊት እና ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል የጠበቀ ግንኙነት እና ትሥሥር አለ። ሁለቱም፣ ከአንድ መለኮታዊ ምንጭ የሚፈሱ፣ በሆነ መንገድ ወደ አንድነት ይዋሃዳሉ እና ወደ አንድ ዓላማ ያዞራሉ” (ዲይ ቨርቡም፣ 9)። የቤተክርስቲያን ትውፊት በታሪክ ሁሉ በቤተክርስቲያን በኩል ይስፋፋል፣ ይህም የእግዚአብሔርን ቃል የሚጠብቅ፣ የሚተረጉም እና የሚያንፀባርቅ ነው። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ (ቁጥር 113) በዚህ ረገድ የቤተክርስቲያን አባቶች መፈክርን ያመለክታል፡- “ቅዱሳን መጻሕፍት በዋናነት የተጻፉት በሰነዶች እና በመዝገቦች ሳይሆን በቤተክርስቲያን ልብ ውስጥ ነው”፣ ማለትም በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ሲል ይገልጻል።

ከላይ በተጠቀሰው የክርስቶስ ቃላት ብርሃን፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ “ከሐዋርያት የሚመጣው ቱፊት በቤተክርስቲያን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያድጋል” (ዲቪ፣ 8) በማለት ያረጋግጣል። ይህ የሚሆነው “በአማኞች በተደረጉ ማሰላሰልና ጥናት”፣ “የሚለማመዱትን መንፈሳዊ እውነታዎች ዘልቆ በመግባት” እና ከሁሉም በላይ ደግሞ “የእውነትን የተረጋገጠ ስጦታ” የተቀበሏቸው የሐዋርያት ተተኪዎች ስብከትን በመጠቀም ነው። በአጭሩ፣ “ቤተክርስቲያን፣ በትምህርቷ፣ በሕይወቷና በአምልኮዋ፣ እሷ ራሷ የሆነችውን ሁሉ፣ የምታምነውን ሁሉ ትኖራለች” (ዲቪ፣ 8)።

በዚህ ረገድ፣ የታላቁ ቅዱስ ግሪጎሪ አገላለጽ ታዋቂ ነው፡- “ቅዱሳት መጻሕፍት ከሚያነባቸው ጋር ያድጋሉ”። ቅዱስ አውጉስጢኖስ “በቅዱሳት መጻሕፍት የሚገለጥ አንድ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፣ እናም በብዙ ቅዱሳን ከንፈሮች ላይ የሚሰማ አንድ ቃል ብቻ ነው” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። የእግዚአብሔር ቃል በቅሪተ አካል የተዋቀረ አይደለም፣ ይልቁንም በቱፊት የሚያድግና የሚበለጽግ ሕያውና ተፈጥሮአዊ የሕይወት እውነታ ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና፣ ትውፊት የእውነትን ባለጠግነት ይገነዘባል እና በታሪክ ተለዋዋጭ መጋጠሚያዎች ውስጥ ይካተታል።

በዚህ ረገድ፣ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ዶክተር ጆን ሄንሪ ኒውማን የክርስቲያን ዶክትሪን ልማት በሚል ርዕስ በጻፈው ሥራው ላይ ያቀረቡት ሀሳብ አስደናቂ ነው። ክርስትና፣ እንደ የጋራ ተሞክሮም ሆነ እንደ አስተምህሮ፣ ኢየሱስ ራሱ በዘሪው ምሳሌዎች (ማር. 4:26-29) ላይ በተገለጸው መንገድ ተለዋዋጭ እውነታ መሆኑን አረጋግጧል፤ ይህም በውስጣዊ ሕያው ኃይል ምክንያት የሚዳብር ሕያው እውነታ ነው።

ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩንና የስብከተ ወንጌል ተባባሪውን ጢሞቴዎስን ደጋግሞ “ጢሞቴዎስ ሆይ፣ የተቀበልከውን ጠብቅ” ሲል አጥብቆ ይመክራል (1ኛ ጢሞቴዎስ 6:20፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1:12-14)። በላቲን ቋንቋ "ዴይ ቨርቡም" (የእግዚአብሔር ቃል) የተሰኘው የዶግማዊ ሕገ ደንብ ይህንን የጳውሎስ ጽሑፍ ያስተጋባል፡- “የተቀደሰ ቱፊት እና ቅዱሳት መጻሕፍት ለቤተክርስቲያን የተሰጡ የእግዚአብሔር ቃል አንድ የተቀደሰ ተቀማጭ ሀብት ይሆናሉ”፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሥልጣኑ የሚተገበረው የቤተ ክርስቲያን ሕያው የማስተማሪያ ቢሮ” (ቁጥር 10) ተብሎ ይተረጎማል። “ተቀማጭ ሀብት” የሚለው ቃል በመጀመሪያ ትርጉሙ በሕግ የተፈቀደለት እና በተቀማጩ ላይ ያለውን ይዘት የመጠበቅ ግዴታ የሚያስገድድ ቃል ሲሆን ይህም በዚህ ጉዳይ ላይ እምነት የሆነው እና ሳይበላሽ የማስተላለፍ ግዴታ ነው።

የእግዚአብሔር ቃል “ተቀማጭ ሀብት” አሁንም በቤተክርስቲያን እጅ ውስጥ ነው፣ እናም ሁላችንም፣ በተለያዩ የቤተክርስቲያን አገልግሎቶቻችን፣ በታሪክና በህልውና ውስብስብነት ውስጥ ለምናደርገው ጉዞ እንደ መሪ  ኮከብ በቅንነት መጠበቅ አለብን።

በማጠቃለያ፣ ውድ ጓደኞቼ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትንና የቱፊት መቀላቀል የሚያጎላውን "ዴይ ቨርቡም"ን እንደገና እናዳምጥ፤ ይህም “አንዱ ከሌላው ጋር ሳይገናኝ መቆም እንደማይችል በጣም የተሳሰሩና የተገናኙ  መሆናቸውን ያረጋግጣል፣ እና… ሁሉም በአንድነትና እያንዳንዱ በራሱ መንገድ በአንድ መንፈስ ቅዱስ ተግባር ለነፍሳት መዳን ውጤታማ በሆነ መንገድ አስተዋጾ ያደርጋሉ” (ቁጥር 10)።

28 Jan 2026, 15:30

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >