ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ ዩ ሂዩንግ-ሲክ፥ ካኅናት ወንድማማችነትን እንዲያሳድጉ መጋበዛቸው ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልዕክታቸው፥ ካኅናት ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለቃሉ እና ለቤተ ክርስቲያን ታማኞች በመሆን የክኅነትን ውበት መጠበቅ፣ ለሌሎች መመስከር እና ማሳደግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “መጭውን ጊዜ የሚያለመልም ታማኝነት” በሚል ርዕሥ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት፥ የክኅነት አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ ወደር የሌለው አገልግሎት ነው” በማለት አፅንዖት መስጠታቸውን ካርዲናል ላዛሩስ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው ለካኅናት ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት፥ ካኅናት ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለቃሉ እና ለቤተ ክርስቲያኑ ታማኞች ሆነው የክኅነትን ውበት ለመጠበቅ፣ ለሌሎች ለመመስከር እና ለማሳደግ መከተል ያለባቸውን መንገድ ማመላከታቸውን እና የወንጌልን መሠረታዊ ሃሳብ ሳያሳንሱ ወይም ሳያዳክሙ ነገር ግን በድፍረት የሚያውጁበትን የሐዋርያዊ አገልግሎት ዘዴዎችን እንዲከተሉ ጥሪ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
የላቲን የአምልኮ ሥርዓትን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ከሚከበረው የዘንድሮው ብርሃነ ልደቱ በዓል ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ይፋ በተደረገው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለቫቲካን ሚዲያ ያካፈሉት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የካኅናት ሕይወት፣ ዝግጅት እና አገልግሎት በማስመልከት ይፋ የተደረጉ፥ “Optatam totius” ወይም “የሁሉ ሰው ምኞት” እና “Presbyterorum ordinis” ወይም “የክኅነት ሕይወት” የተሰኙ ሁለት ሐዋርያዊ ድንጋጌዎች ስድሳኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር በመወሰናቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተለይም የክኅነት ሕይወትን ጥንታዊ ውርስ በማድረግ ጥሪው ማራኪነቱን እና ውበቱን እንዳጣ ተደርጎ ሊወሰድ በሚችልበት በዚህ ዘመን ቅዱስነታቸው የወሰዱት ውሳኔ አስፈላጊ እንደሆነ ካርዲናል ላዛሩስ ገልጸው፥ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት የክኅነት ሕይወት ድንቅ ስጦታ እና ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሆነ፥ ከሁሉም በላይ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ አስፈላጊ አገልግሎት መሆኑን ሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሚያስተውሉት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “መጭውን ጊዜ የሚያለመልም ታማኝነት” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት፥ የክኅነት ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ የወደፊት ዕድል ምን እንደሚሆን እንደሚችል የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ፥ መልሱን ከርዕሡ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመው፥ ያለ ታማኝነት የወደፊት ዕድል ሊኖር እንደማይችል እና ታማኝነት በምዕራቡ ዓለም አሉታዊ ዋጋ ቢሰጠውም ይህ ከእውነት የራቀ እንደሆነ እና የቤተ ክርስቲያን ዕጣ ፈንታ ዘወትር የሚገነባው ጥንካሬን ከሚያገኝበት ከዛሬው ታሪክ እና ባሕል እንደሆነ አስረድተዋል።
ታማኝነት ማለት ራስን ለመንፈስ ቅዱስ ድንቅ ሥራ ክፍት ማድረግ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ፥ “ለአገልግሎቱ በተሾሙት ሰዎች በኩል በእግዚአብሔር እና በቤተ ክርስቲያን ለቀረበልን የተልዕኮ ጥሪ ለመገዛት ያለንን ጠንካራ ፍላጎት ማክበር እና መንከባከብ ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“ታማኝነት የልግስና መለኪያ ነው” ያሉት ካርዲናል ላዛሩስ፥ ታማኝነት እውነተኛ እና ግልጽ ፍቅር እንደሆነ፣ በራስ ላይ ያተኮረ ሳይሆን በዋናነት በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ፣ ጥቃቅን እና ትላልቅ የሆኑ የታማኝነት ተግባራትን ማከናወን እንደሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ወደፊት የሚወስደውን መንገድ እንደሚያሳይ እንደሆነ ገልጸው፥ እኛ እንደ የቅድስት መንበር የክኅነት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለቃሉ እና ለቤተ ክርስቲያኑ ታማኝ የሆነ የክኅነት ሕይወት ውበት መጠበቅ፣ ማወጅ እና ማሳደግ አለብን ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ በክኅነት ሕይወት ውስጥ ያለው የኅብረት ልምምድ ውጤታማነት እና ሲኖዶሳዊነት እንደሚያሳስባቸው በግልጽ መናገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ፥ ኅብረት ለክኅነት ሕይወት ተገቢ የሆነውን ነገር በሚገባ የሚገነዘብ መሆኑን አስረድተዋል።
“ማንኛውም ካህን ብቻውን ሊኖር ወይም ሊሠራ አይችልም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ፥ “ካኅናት በሙሉ በቤተ ክርስቲያን አንደነት ውስጥ በመሆን ከሌሎች የተሾሙ አገልጋዮች እና ከእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ጋር አንድ ዓይነት ተልዕኮን በተግባር ይፈጽማሉ” ብለዋል።
“በቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል የሚገኝ እና ሲኖዶሳዊነትን የሚያበረታታ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ምክር እጋራለሁ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ፥ ራስን ከፍ ማድረግ እና ራስን ከሌሎች ማግለል በካኅናት ሕይወት ውስጥ የተለመዱ ፈተናዎች እንደሆኑ ተናግረው፥ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ ሲኖዶሳዊነት ለገለልተኝነት በተጨባጭ ዋና መድኃኒት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ከጳጳስ ጋር፣ ከካኅናት እና ዲያቆናት ጋር እንዲሁም ከምዕመናን ጋር ያለው የጋራ ኃላፊነት፣ የወንድማማችነት እና የወዳጅነት እውነተኛ ግንኙነቶች በካኅን ሕይወት ውስጥ የሚታዩ እውነታዎች ብቻ ሳይሆኑ የአንድን ሰው ጥሪ እና ማንነት በተሻለ መንገድ ለመኖር ፍሬያማ አውዶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
“ሲኖዶሳዊነትን ሙሉ በሙሉ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ሚናዎቿን በሙሉ የምትጋራ ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን ነገር ግን ለእግዚአብሔር መንግሥት ዕድገት በእያንዳንዱ ሰው ልዩ ባህሪ መሠረት የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ በመጋራት እውነተኛ የጋራ ኃላፊነትን ለማሳካት የምትፈልግ ቤተ ክርስቲያን ናት” ሲሉ ካርዲናል ላዛሩስ፥ አስረድተዋል።
“እያጋጠመ ያለውን የጥሪ ቀውስ እየኖረች ያለችው ቤተ ክርስቲያን አለመሆኗ ግልጽ ሊሆን ይገባል” ያሉት ካርዲናል ላዛሩስ፥ በተለይም ዓለማዊነት ዛሬ በሁሉም የኅብረተሰብ ደረጃዎች እየደረሰ ያለው በተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች ብቻ መሆኑ አስረድተዋል።
ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተሾሙት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ጥሪዎች በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ጊዜያዊ ወይም ከፊል ግንኙነቶችን የሚያበረታታ፣ ታማኝ እና ዘላቂ ቁርጠኝነትን የሚያደናቅፍ እና ሁሉም ሰው ጥሪውን ከመፈለግ የሚያዘናጋ ዓለም እንዳለ ተናግረዋል።
“እንግዲህ እንደ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስነታቸው በጻፉት ሐዋርያዊ መልዕክት መሠረት በዚህ ሁኔታ ሳንሸነፍ ከጋብቻ እና ከምንኩስና ሕይወት ጀምሮ እስከ ክኅነት አገልግሎት ድረስ የሁሉንም ጥሪዎች ውበት እና ተደጋጋፊነት ለማወጅ በርትተን መነሳሳት አለብን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለቃሉ እና ለቤተ ክርስቲያኑ ታማኞች ሆነን የክኅነትን ውበት በመጠበቅ፣ የወንጌልን መሠረታዊ ሃሳብ ሳያሳንሱ ወይም ሳያዳክሙ በድፍረት ለሌሎች ለመመስከር እና ለማሳደግ የሚያግዙ የሐዋርያዊ አገልግሎት ዘዴዎችን እንድንከተል ጥሪ ማቅረባቸውን ካርዲናል ላዛሩስ አስታውሰዋል።
“ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው አንቀጽ 25 ላይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ካህናት ለተልዕኮአቸው ታማኞች በመሆን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በኃላፊነት እንዲጠቀሙ ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ ልዩ እና እጅግ አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ያሉት ካርዲናል ላዛሩስ፥ የኢንተርኔት አውድ በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ካኅናት ወንጌልን የሚያውጁበት ቦታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረው፥ በመጥምቁ ዮሐንስ ዘይቤ መሠረት እያንዳንዱ ካኅን ራሱን ሳይሆን ዘወትር ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከቱ ለወንጌል አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው በተግባር እንዲገለጽ የሚጋብዙት የወንጌል አገልግሎት ግንዛቤን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤታቸው ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረው፥ “በቤተ ክርስቲያኒቱ ተልዕኮ መካከል አዳዲስ ተግዳሮቶች በሚታዩባቸው ቦታዎች እና አውዶች ውስጥ በጥበብ ለመኖር የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን ለሁሉም ማቅረብ እንችላለን” ብለው፥ ይህ አቅጣጫ በድፍረት እና በግልጽነት አዲስ የወንጌል ምስክርነት በፍላጎት እና በምኞት እንድንሰጥ እና ከምን ጊዜውም በላይ ለሚቀርብልን ጥሪ ታማኝ ለመሆን የበለጠ ግንዛቤን እና በቂ ዝግጅትን የሚጠይቅ መሆኑን በቅድስት መንበር የክኅነት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ ዩ ሂዩንግ-ሲክ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።