ፈልግ

በምያንማር ፈንጂ የጦር መሣሪያዎች የማምከን ሥራ በምያንማር ፈንጂ የጦር መሣሪያዎች የማምከን ሥራ   (AFP or licensors)

የጦር መሣሪያዎች በሕይወት ወይም በሞት ላይ ውሳኔ መስጠት የማይችሉ መሆናቸው ተገለጸ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በድርጅቱ 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የጦር መሣሪያ ስርጭት በአገሮች መካከል አለመተማመንን በመፍጠር እና ዓመፅን በማቀጣጠል ውይይትን የሚያዳክም በመሆኑ የተለመዱ የጦር መሣሪያዎች መጠቀምን ማስወገድ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በተባበሩት መንግሥታት 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የተለመዱ የጦር መሣሪያዎች አጠቃቀምን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ የጦር መሳሪያዎች መስፋፋት እና ተገቢ ያልሆነ አጠቃቀም በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ሰላምን እና እምነትን ለማምጣት ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑን አብራርተዋል።

የጦር መሣሪያዎችን በነፃነት የመጠቀም ልምድ አለመተማመንን እንደሚያበረታታ፣ ዓመፅን እንደሚያባብስ እና በክልሎች መካከል የሚደረገውን ውይይት እንደሚያበላሽ ገልጸው፥ በዚህም በዓለም ዙሪያ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚወጣው ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. አጠቃላይ ወጭው 2.7 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቻ የጦር መሣሪያዎችን አላግባብ መጠቀምን ማስቆም በማስመልከት ባቀረቡት ጥሪ፥ ዓለም አቀፍ የሰላም ምኞትን ለጦር መሣሪያ ክምችት እንዳይሆን ለማድረግ ያለንን ጥረት  እንቀጥላለን በሚለው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቃላት ላይ በማሰላሰል፥ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ለሰብዓዊ እርዳታ እና ድጋፍ ከማዋል ይልቅ ለጦር መሣሪያ መዋላቸውን ገልጸዋል።

የፈንጂ መሣሪያዎች እገዳ ስምምነትን መተው

ከሩሲያ በኩል የሚመጣውን ስጋት በመጥቀስ፥ በሐምሌ ወር አምስት የአውሮፓ አገራት ከኦታዋ ፀረ-ሰው ፈንጂዎች ስምምነት መውጣታቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1999 ዓ. ም. ተግባራዊ የሆነው ይህ ስምምነት ፀረ-ሰው ፈንጂዎችን መከልከሉን እና አገሮች የጦር መሣሪያ ክምችቶቻቸውን እንዲያወድሙ፣ የተቆፈሩ ቦታዎችን እንዲያጸዱ እና የፈንጂ መሣሪያ ተጎጂዎችን እንዲረዱ ይጠይቃል።

በዩክሬይን ፈንጂ መሣሪያዎችን የማምከን ሥራ
በዩክሬይን ፈንጂ መሣሪያዎችን የማምከን ሥራ   (ANSA)

“ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው” በማለት ያስጠነቀቁት ሊቀ ጳጳስ ካቻ፥ ምክንያቱም ፈንጂዎች “በግለሰቦች፣ በማህበረሰቦች እና በአካባቢ ላይ ያለ ልዩነት ዘላቂ ጉዳት ስለሚያደርሱ፣ ግጭቶች ከቆሙ ከረጅም ጊዜ በኋላም የሚያስከትሉት ጉዳት የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ገለጻ፣ በአማካይ በየሰዓቱ አንድ ሰው በፈንጂዎች እና በሌሎች ፈንጂ መሣሪያዎች እንደሚሞት ወይም እንደሚጎዳ ተገልጿል። ይህም ከሰብዓዊነት እና ከዓለም አቀፍ ህግ መርሆዎች ጋር እንደሚጋጭ ሊቀ ጳጳሱ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ይህ የሚመለከተው ፈንጂ መሣሪያዎችን ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ቁጥጥር የማይደረግባቸውን የጦር መሣሪያዎች በሙሉ እንደሆነ ገልጸው፥ “በሕይወት እና በሞት ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ለጦር መሣሪያዎች መሰጠት የለባቸውም” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቻ አፅንዖት ሰጥተዋል።

አውዳሚ ውጤቶች

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቻ፥ ፈንጂ የጦር መሣሪያዎች ምርት አለማቆሙን ገልጸው፥ ነገር ግን የክላስተር ጥይቶችን እና ህገ-ወጥ ትናንሽ እና ቀላል የጦር መሣሪያዎች ዝውውር መጨመር ያስከተለውን ችግርንም አንስተዋል።


እነዚህን መሳሪያዎች በሕገ-ወጥ መንገድ መጠቀም አስከፊ ውጤቶችን ያስከትላል ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥በተለይም አቅመ ደካሞችን እንደሚጎዳ እና ልጆች ብዙውን ጊዜ ወደ ወንጀል ወይም ወደ አሸባሪነት በመመለስ የትምህርት ዕድላቸውን እና የወደፊት ተስፋቸውን እንደሚነፈጉ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ሁሉም ሰው “በጦር መሣሪያዎች አማካኝነት የሚገነባ የደህንነት ቅዠት ትቶ በምትኩ በውይይት፣ በፍትህ እና በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት ክብር ላይ የተመሠረተ ሰላምን ለመገንባት ያለማቋረጥ እንዲጥር አሳስበዋል።

27 Oct 2025, 16:32