ፈልግ

የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ምርት የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ምርት   (Gerasimov)

ቅድስት መንበር፥ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ አስቸኳይ የሞራል ግዴታ ነው” ስትል ገለጸች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ስርጭትን ለመግታት እንዲሠራ፥ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቻ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ስርጭትን ለመከላከል እና ለማስወገድ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቻ ይህን ጥሪ ያቀረቡት፥ የተባበሩት መንግሥታት የ80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ኮሚቴ ማክሰኞ ጥቅምት 11/2018 ዓ. ም. በኒውዮርክ የጦር መሣሪያ ላይ ባካሄደው ውይይት ላይ ባቀረቡት መግለጫ እንደ ነበር ታውቋል።

“ቅድስት መንበር የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመቆጣጠር፣ ለመገደብ፣ ለመቀነስ እና በመጨረሻም ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶች ከእውነታው የራቁ ተስፋዎች ሳይሆኑ ሊተገበሩ የሚችሉ እና አስቸኳይ የሞራል ግዴታዎች መሆናቸውን በጠንካራ እምነት አረጋግጣለች” ብለዋል።

“ሰላም ሙሉ በሙሉ በመጥፋት ስጋት ወይም ሊጠፉ በሚችሉ አደጋዎች መረጋጋት ሊገኝ ይችላል በሚለው ቅዠት ላይ መገንባት የማይችል በመሆኑ ይህም በሥነ ምግባር እና በስትራቴጂካዊ መልኩ ዘላቂነት የሌለው ነው” ብለዋል።

አገራት የጦር መሣሪያ ማስፈታት ስምምነቶችን መቀላቀል አለባቸው

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ካቻ፥ “ሁሉም የኒውክሌር መሣሪያ የታጠቁ አገሮች የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች አለማስፋፋት ስምምነት (NPT) አንቀጽ 6 መሠረት የተጣለባቸውን ግዴታዎች እንዲወጡ” በማለት አሳስበው፥ ክምችቶቻቸውን ለመቀነስ እና በመጨረሻም ለማስወገድ በማሰብ በቅን ልቦና እንዲደራደሩ አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ካቻ በመቀጠልም፥ ቅድስት መንበር መንግሥታት የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች የሚከለክል ስምምነት (TPNW) እንዲቀላቀሉ እና አጠቃላይ የኑክሌር መሣሪያዎችን ክልከላ ስምምነት (CTBT) ተግባራዊ ማድረግን፣ የማምረቻ ቁሶችን በተመለከተ ስምምነት ላይ መደራደርን እና ጠንካራ የማረጋገጫ እና የእርዳታ ዘዴዎችን ማጠናከርን ጨምሮ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚያስከትላቸው አደጋዎች

የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ካቻ፥ “ዛሬ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን መጠቀም አደጋ ላይ የሚጥል፣ አስደንጋጭ የንግግር ውዝግብ የሚታይበት፣ በእንከን የለሽ ማስጠንቀቂያ የጦር መሣሪያዎችን ለማስፋፋት የተደረጉ አዲስ ጥረቶች እየተከሰቱ ናቸው” በማለት “ይህም በምትኩ ፍርሃትን የሚያበረታታ እና ዓለም አቀፍ ደህንነትን የበለጠ የሚያናጋ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት “የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ራስን የቻሉ ሥርዓቶች እና የሳይበር ቴክኖሎጂዎችን ከኒውክሌር ትዕዛዝ፣ ቁጥጥር እና ማሰማሪያ ሥርዓቶች ጋር ማዋሃድን በተመለከተ አፅንዖት ሰጥተዋል።

እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የውሳኔ አሰጣጥ ብቃቶችን በማሳጠር “የሰውን ቁጥጥር ይቀንሳሉ፣ በተሳሳተ ስሌት ስህተት የመፍጠር አደጋን በመጨመር እና እርግጠኛ አለመሆንን የሚያስከትሉ በመሆናቸው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘላቂ ትኩረትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

ለጦር መሣሪያ ምርት የሚፈሱ ሃብቶች የሞራል ውድቀት ምልክቶች ናቸው

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ካቻ በመግለጫቸው፥ ከ 80 ዓመታት በፊት በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የተፈጸሙት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ጥቃቶች አሁንም ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት ትልቅ ስጋት እየፈጠሩ እንደሚገኙ አጉልተው ገልጸዋል።

ከእነዚህ ክስተቶች የመነጨው ስቃይ እና ውድመት፣ የእነዚህ የጦር መሣሪያዎች አስከፊ አቅም እና እንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ ክስተቶች እንደገና እንዳይከሰቱ መከላከል የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል።

ብዙዎች እየተሰቃዩ ባሉበት ጊዜ ለጦር መሣሪያዎች የዋለው እጅግ ከፍተኛ ሃብት ከባድ የሞራል ውድቀትን አስከትሏል” ሲሉ ገልጸው፥ እውነተኛ ደህንነት፣ ሕይወትን መጠበቅ፣ ፍትህን ማስፋፋት እና ሰላምን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አክለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በመጨረሻም፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በውይይት፣ በወንድማማችነት እና እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮ የተሰጠውን ክብር ማክበርን መሠረት ያደረገ የደህንነት ራዕይ በሰው ላይ ያተኮረ እንዲሆን አሳስበዋል።

 

23 Oct 2025, 14:33