ር.ሊ.ጳ ሊዮ 14ኛ አርብ የመስቀል መንገድ ጸሎት ላይ መስቀል ተሸክመው ጸሎት እንደሚመሩ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም ኮሎሲየም በሚገኘው ሥፍራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለተ አርብ ቀን የተጓዛቸውን አስራ አራት የመስቀል መንገድ ጉዞዎች የምያስታወሰውን ምስጢር በጸሎት ይመራሉ፤ በመስቀል መንገድ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ሁሉ መስቀሉን ተሸክመው ጸሎት የምያደርጉ ሲሆን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 267ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ቅዱስነታቸው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ደረጃ የምያደርጉት የመጀመሪያ የስቅለተ አርብ ክብረ በዓል ይሆናል።
የዘንድሮው የመስቀል መንገድ ሥነ ሥርዓት የማሰላሰያ ጸሎቶች እ.አ.አ ከ2016 እስከ 2025 ዓ.ም ድረስ የቅድስት ምድር ጠባቂ ሆነው ላገለገሉት ለፍራንችስካዊያን ማሕበር ካህን አባ ፍራንችስኮ ፓተን እንዲያዘጋጁ አለፊነት ተሰጥቷቸዋል። የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽሕፈት ቤት የመስቀል መንገድ ሥነ ሥርዓት የማሰላሰያ ጸሎቶች ጽሑፎቹ አርብ ጠዋት ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም፣ እኩለ ቀን አካባቢ እንደሚታተም አስታውቋል።
ብዙውን ጊዜ በዮርዳኖስ ውስጥ ከሚገኘው ከኔቦ ተራራ የሚጽፉት አባ ፓተን፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በግጭት እና አለመረጋጋት በተሞላው በዚህ ወቅት ለመካከለኛው ምስራቅ ሕዝብ ስቃይ በተደጋጋሚ ድምጽ ሰጥተዋል።
ባለፈው ዓመት፣ ልክ እንደ 2024 ዓ.ም፣ የመስቀል መንገድ ሥነ ሥርዓት የማሰላሰያ ጸሎቶች ያዘጋጁት በሮም በሚገኘው የጂሜሊ ሆስፒታል ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ ወደ ቅድስት ማርታ የጳጳስ ቤት ከተመለሱ በኋላ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመስቀል መንገድ ሥነ ሥርዓት የማሰላሰያ ጸሎቶች መጻፋቸው ይታወሳል።
