ፈልግ

በደቡብ ላምፔዱሳ በስደተኞች ላይ ለሰደሰ የባሕር ላይ አደጋ የነፍስ አድን ዕርዳታ ሲሰጥ በደቡብ ላምፔዱሳ በስደተኞች ላይ ለሰደሰ የባሕር ላይ አደጋ የነፍስ አድን ዕርዳታ ሲሰጥ 

የር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የላምፔዱሳ ሐዋርያዊ ጉብኝት የስደት ቀውስን አጉልቶ እንደሚያሳይ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላምፔዱሳ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብሎ የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) አማካሪ እና ተሟጋች አማያ ቫልካርሴል በሰጠው አስተያየት፥ ቅዱስነታቸው በደሴቲቱ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወሳኝ በሆነ ወቅት የሚካሄድ እና የሰውን ልጅ ዋና ማዕከል በማድረግ መልዕክት የሚያስተላልፉበት መሆኑን አስረድቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅዱስነታቸው መልዕክት ዋና ዓላማ ብዙ ጊዜ ችላ የሚባሉ እንደ ምያንማር እና ሱዳን ባሉ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ጦርነቶች ምክንያት ለስደት እና መፈናቀል የሚጋለጡ ንፁሃን ሰዎችን ለማስታወስ የሚያግዝ ኃይለኛ መልዕክት ያለው እና ዓለም ሰብዓዊ ክብርን እና አንድነትን ማዕከል እንዲያደርግ ጥሪ የሚያቀርብ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላምፔዱሳ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከዚህ በፊት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የከፈቱትን መንገድ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ዓ. ም. ከስደተኞች እና ከጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር ለመገናኘት ያደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ትንሿን የሜዲትራኒያን ደሴት ላምፔዱሳን የአብሮነት ምልክት ማድረጉ ታውቋል። ያ ታሪካዊው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓለም አቀፋዊ ግዴለሽነትን  በማውገዝ “ወንድምህ የት አለ?” የሚለውን ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።


በኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) ዓለም አቀፍ ተሟጋች እና አማካሪ የሆኑት አማያ ቫልካርሴል፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላምፔዱሳ ሐዋርያዊ ግብኝታቸው ድሆች፣ ተጋላጭ የሆኑት እና የተገለሉት ሰዎች የወንጌል መልዕክት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ እና ጉብኝታቸውንም ተጨባጭ መግለጫ አድርገው እንደሚመለከቱት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስደተኞች ሁኔታን በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1951 ዓ. ም. የተደረገ ስምምነት 75ኛ ዓመት መታሰቢያን በዓል በቅርቡ ማክበራቸውን ያስታወሱት አማያ፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ስምምነት የስደተኞችን መብቶች ለመጠበቅ እና እንዲሰደዱ ለተገደዱ ሰዎች ሕጋዊ ጥበቃ ለማድረግ ያለውን ዘላቂ ጠቀሜታ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 21/2026 ዓ. ም. ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ “ይህን አስፈላጊ ዓለም አቀፍ ሠነድ ለማዘጋጀት ያነሳሳው መንፈስ ዛሬ ኃላፊነት ያለባቸውን የአገራት መሪዎች ኅሊናን ማብራት እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በላምፔዱሳ የሚገኝ ወደ አውሮፓ መግቢያ በር
በላምፔዱሳ የሚገኝ ወደ አውሮፓ መግቢያ በር

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ፈለግ መከተል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በላምፔዱሳ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላምፔዱሳ ያደረጉትን የመጀመሪያ ጉብኝት የሚያስታውስ እና ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በስደተኞች ላይ የሚያሳዩትን የግድየለሽነት ስሜት እንዲያቆሙ ጥሪ ያቀረቡበት ወቅት እንደ ነበር ይታወሳል።

እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለስደት ምላሽ መስጫ ማዕቀፍ የሆኑትን አራት ግሦች እነርሱም፣ ማስተናገድ፣ መከላክል፣ ማስተዋወቅ እና ማዋሃድ የሚሉ መሆናቸውን አማያ አስታውሰው፥ “ስደት ክስተት ሳይሆን ስሞች፣ ፊቶች፣ ታሪክ እና ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ናቸው” ብለው፥ በአንድ አጋጣሚ ሁላችንም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ልንሆን እንችላለን” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት በድንበር ላይ ሰዎችን ሊደርስ ለሚችል ሞት ኃላፊነትን እንዲወስዱ እና ለሚሰቃዩት ሰዎች ያላቸውን ርኅራሄ እንዲያድሱ ጥሪ ማቅረብን እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ላምፔዱሳ ደርሰው ምዝገባን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ስደተኞች
ላምፔዱሳ ደርሰው ምዝገባን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ስደተኞች   (ANSA)

የተረሱ ግጭቶችን የሚያስታውስ ድምጽ

አማያ በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰላምን እንደ ማዕከላዊ ጭብጥ እና ከግዳጅ መፈናቀል መንስኤዎች ጋር ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚያመለክት ጠቁመው፥ ቅዱስነታቸው ብዙውን ጊዜ በዓለም አቀፍ ዜናዎች ውስጥ የማይጠቀሱ አገሮችን እና ቀውሶችን በተደጋጋሚ እንደሚስቡ፣ ምያንማር እና ሱዳን የመሳሰሉ ቦታዎችን በጸሎታቸው ዘወትር እንደሚያስታውሷቸው፥ ስቃያቸው መዘንጋት የሌለባቸው ንጹሐን ሰዎችን እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።

ከድንበር ባሻገር መመልከት

የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) በላምፔዱሳ ውስጥ በቀጥታ ባይገኝም በሲሲሊ የሚገኙት ቡድኖች በደሴቲቱ የሚገኙ በርካታ ሰደተኞችን እንደሚደግፉ ታውቋል።

የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) አማካሪ እና ተሟጋች አማያ በአስተያየታቸው የስደት ፖሊሲዎች ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ፣ ከአውሮፓ የስደተኞች ሕግ እና በአውሮፓ ኅብረት ከሚወሰዱት የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው አጥብቀው ተናግረዋል።

ሰዎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እና ድንበሮች እንዲዘጉ የሚያዙ ፖሊሲዎች መረቀቅ የፈጠረባቸውን ስጋት ገልጸው፥ “ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገራቸውን ትተው እንዲወጡ ለሚያደርግ ምክንያት መልስ ማግኘት ቁልፍ ጉዳይ ነው” ብለው “ወደ መንስኤዎች መሄድ እና ሰዎችን ማክበር ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅርቡ ሰዎች ስደተኞች በመሆናቸው ብቻ ለማስወገድ በሚፈልጉ የስደት ፖሊሲዎች ላይ የሰነዘሩትን ትችት ያስታወሱት አማያ፥ ይህም የግለሰብ ሁኔታዎችን በመመልከት እያንዳንዱ ሰው በክብር እንዲያዝ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

ውህደት ማለት ስደተኞች የአዳዲስ ማኅበረሰቦች ቋንቋ፣ ህግ እና ባህል የሚማሩበት የጋራ ሂደት መሆኑን በማስረዳት፥ አስተናጋጅ ማኅበረሰቦች ስደተኞች የራሳቸውን ማንነት እና ባሕል እንዲረሱ ማድረግ እንደሌለባቸው እና በደስታ ተቀብለው እንዲያስተናግዱ አሳስበዋል።

ስደተኞች ከማኅበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል የሚያግዝ የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት የስልጠና መርሃ ግብር
ስደተኞች ከማኅበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል የሚያግዝ የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት የስልጠና መርሃ ግብር   (@JRS)

የስደትን መጥፎ ገጽታ መለወጥ

የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) አማካሪ እና ተሟጋች አማያ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የላምፔዱሳ ሐዋርያዊ ጉብኝት አስፈላጊ አስተዋጽኦዎች መካከል አንዱ ስደትን በማስመልከት በሚደረጉ የሕዝብ ውይይቶች ላይ የሰውን ክብር ወደነበረበት ለመመለስ ያላቸው ጽናት እንደሆነ በማመን፥ የሰው ልጅ ክብር እና ውበት የመልዕክታቸው ማዕከላዊ ጉዳይ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።  

የግል ምስክርነቶችን ማዳመጥ የተዛባ አመለካከቶችን ለመፈታተን እና ርህራሄን ለማሳደግ እንደሚረዳ በማመን፥ ብዙ ስደተኞች የጋራ ሰብዓዊነታቸውን እውቅና ብቻ የሚፈልጉ መሆናቸውን የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) አማካሪ እና ተሟጋች አማያ በአስተያየታቸው ገልጸዋል።

የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) አማካሪ እና ተሟጋች አማያ ቫልካርሴል
የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) አማካሪ እና ተሟጋች አማያ ቫልካርሴል   (@JRS)

 

 

 

04 Jul 2026, 17:16