ፈልግ

የዓለም የስደተኞች ቀን የዓለም የስደተኞች ቀን   (LEAH MILLIS)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለደኅነታቸው ሲሉ ለሚሰደዱት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሰኔ 14/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ካደረሱ በኋላ ብራዚል ውስጥ በመኪና አደጋ የተጎዱትን በጸሎታቸው በማስታወስ ለጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ባቀረቡት የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ማጠቃለያ፥ ሰኔ 14/2018 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት የተከበረውን የዓለም የስደተኞች ቀን አስታውሰው፥ ስደትን፣ ዓመፅን እና ግጭትን ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎችን ለመጠበቅ አዲስ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስደተኞች የሚገኙበትን ሁኔታ በማየት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1951 ዓ. ም. የተደረገው ስምምነት 75ኛ ዓመት መታሰቢያ ዕለት፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ስምምነት የስደተኞችን መብቶች ለመጠበቅ እና መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ ለተገደዱት ሰዎች ሕጋዊ ጥበቃ የመስጠት ዘላቂ ጠቀሜታ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ “ይህንን አስፈላጊ ዓለም አቀፍ ሠነድ ለማዘጋጀት ያነሳሳው መንፈስ ዛሬ ኃላፊነት ያላቸውን ሰዎች ህሊና ማብራት እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በሰው ልጅ ስቃይ ውስጥ ግድ የለሽነት አማራጭ እንዳልሆነ አፅንዖት የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ “ማንም ሰው ጥበቃ እና ደህንነት ከሚሹት ሰዎች ፊቱን ዞር ማድረግ አይችልም” ብለው፥ ማኅበረሰቦችም ስደት የደረሰባቸውን ሰዎች በሰላም እና በክብር ተቀብለው የወደፊቱን በተስፋ እንዲመለከቱ አበረታተዋል።

በብራዚል አደጋ ለደረሰባቸው ወጣቶች የቀረበ ጸሎት

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት መካከል ከብራዚል ለመጡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ በቅርቡ በብራዚል ሰሜናዊ ምሥራቅ ሴአራ ግዛት ውስጥ በተከሰተው የመኪና አደጋ የበርካታ ወጣቶች ሕይወት ማለፉን አስታውሰዋል።

“ከጥቂት ቀናት በፊት በብራዚል ሴአራ ግዛት በደረሰ የመኪና አደጋ የሞቱትን ወጣቶች በጸሎት አስታውሳቸዋለሁ” ብለዋል። በአደጋው ሰባት የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፥ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 22 ዓመት የሆናቸው እነዚህ ሰለባዎች ከበርካታ የብራዚል ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች እና ከጁአዜሮ ዶ ኖርቴ ከተማ የመጡ የቀድሞ ተማሪዎች እንደ ነበሩ ተገልጿል።

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ጋር የሚደረግ ውይይት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጴንጤቆስጤ ማኅበረሰቦችን ከአምስት አሥርት ዓመታት በላይ በጋራ መግባባት እና በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ያሰባሰበ የካቶሊክ-ጴንጤቆስጤ ዓለም አቀፍ ውይይት ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ሌክስ ኦራንዲ፣ ሌክስ ክሬደንዲ” (የጸሎት ሕግ የእምነት ሕግ ነው) የሚለውን ጥንታዊ መርህ በመጥቀስ፥ በዛሬው ዓለም በጸሎት እና በእምነት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ውይይቱ በተለይ በክርስቲያኖች መካከል የተሻለ ግንዛቤን ለማጎልበት፥ በምስክርነት እና በአገልግሎት ትብብርን ለማበረታታት እንደሚጥር አስረድተዋል።

 

 

 

22 Jun 2026, 16:30