ኢየሱስ ሰባ ሁለቱን ላካቸው ኢየሱስ ሰባ ሁለቱን ላካቸው  

የሐምሌ 19/2018 ዓ.ም የ4ኛ እለተ ሰንበት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.    1 ተሰሎንቄ 2፡1-12

2.    1 ጴጥሮስ 2፡1-12

3.    ሐዋርያት 20፡1-12

4.    ሉቃስ 10፡1፣ 17-24

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ሰባ ሁለቱን ላካቸው

ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው {...} ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ።እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”

በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና።

“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።”

ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤  እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 10፡1, 17-20) ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዐስራ ሁለቱ ደቀ-መዛሙርት ባሻገር ተጨማሪ 72 ሐዋሪያቱን ሲልክ እናያለን። ሰባ ሁለት ቁጥር ምን አልባት ሁሉንም አገራት የሚወክል ቁጥር ሊሆን ይችላል። በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ 72 ቁጥር በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን 72 የተለያዩ አገራትን እንደ ሚወክል ይገልጻል (ኦዘፍ. 10፡1-32)። ስለዚህ ይህ አገላለጽ የቤተክርስቲያን ዋነኛው ተልዕኮ ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ የማዳረስ ተልዕኮ እንዳለባት ያሳያል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን በላከበት ወቅት ““መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት!” (ሉቃ 10፡2)።

ይህ የኢየሱስ ጥያቄ ሁልጊዜ ተቀባይነት ያለው ነው።  “የመከሩ ባለቤት” እግዚአብሔር ሲሆን የእርሱ የመከሩ ሥፍራ ወደ ሆነ ወደ ዓለም ሠራተኞቹን ይልክ ዘንድ ሁልጊዜ መጸለይ ይኖርብናል። እያንዳንዳችን በተከፈተ ልብ እና ሚስዮናዊ በሆነ መንፈስ ልንጸልይ ይገባል፣ ጸሎታችን ለእራሳችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ብቻ ለመጠየቅ ማዋል የለብንም፣ ነገር ግን ለሁላችን ለጋራ ፍላጎቶቻችን መጸለይ ይገባናል፣ አንድ ጸሎት ትክከለኛ የክርስቲያን ጸሎት ነው የሚባለው ሁሉን አቀፍ ጸሎት ሲሆን ብቻ ነው።



ኢየሱስ 72ቱን ሐዋርያት በላካቸው ወቅት ተልእኮውን የሚገልጽ ትክክለኛ መመሪያዎችን ይሰጣቸዋል። የመጀመሪያው “ሂዱ” የሚለው ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ጸልዩ” የሚለው ነው፣ ከእዚያን በመቀጠል ደግሞ “በእጃችሁ ኰረጆ ወይም ከረጢት” . . . ወዘተ አትያዙ፣ “ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ አስቀድማችሁ፣ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ” . . .  ወዘተ፤ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ፣ በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው፣ ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ. . .  ከእዚያም ከተማውን ለቃችሁ ሂዱ” በማለት ይልካቸዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች ተልዕኳው ጸሎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንደ ሚገባ ያሳያል፣ ተጨባጭ ሊሆን ይገባዋል፣ ተጓዥ የሆነ ተልዕኮ ሊሆን የገባዋል፣ ከነገሮች ጋር ያለንን ቁርኝት ማስወገድ እና በድህነት መንፈስ የሚደረግ ተልዕኮ እና የእግዚኣብሔር መንግሥት መቅረቡን በሚያመለክት መልኩ ፈውስን በማምጣት ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንዲቀይሩ ማስገደድ ሳይሆን የእግዚኣብሔርን ቃል በትህትና በመመስከር እና በማወጅ ሊከናወን የሚገባው ተልዕኮ ነው፣ በተጨማሪም ይህ ግልጽነትና ወንጌላዊ ነጻነት እንዲወጣ በማድረግ የደህንነትን ምንጭ የሆነውን ቃል በእርግማን እና በማውገዝ ሳይሆን ያለእንቢታ በኃላፊነት ይቀበሉ ዘንድ ማደረግን ያጠቃልላል።

በእዚህ አኳን የሚደረግ ተልዕኮ ቤተክርስቲያን በደስታ የተሞላች እንድትሆን ያደርጋታል። ይህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል የተጠናቀቀው በምን ሁኔታ ነበር? “ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመለሱ” በማለት ነበር። ይህ ከተልዕኮ ስኬት የመነጨ ጊዜያዊ የሆነ ደስታ አይደለም፣ በተቃራኒው “ስማችሁ ግን በመንግሥተ ሰማይ ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ” በማለት ኢየሱስ በተናገራቸው የተስፋ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ደስታ ነው። በዚህ አገላለጽ ውስጥ ውስጣዊ ደስታን እና የእርሱ ልጅ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል በእግዚአብሔር መጠራታችንን በመገንዘባቸው የሚገኘውን ነቀፋ የሌለበት ደስታ ነው። የእርሱ ደቀ መዝሙር በመሆናችን ብቻ የሚገኝ ደስታ ነው። ለምሳሌ ዛሬ በእዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተሰበሰብን እያንዳንዳችን ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት የተሰጠንን የመጠሪያ ሥም ማሰብ እንችላለን፣ ያ መጠሪያ ሥም "በላይ በሰማይ” በሚገኘው በእግዚአብሔር አብ ልብ ውስጥ ተጽፎ የገኛል። እናም የእያንዳንዱን ደቀመዝሙር ሚስዮናዊ፣ ከጌታ ኢየሱስ ጋር የሚራመድ፣ ጌታ ለራሱ ሳይሰስት ራሱን በሙሉ ለሌሎች አሳልፎ እንደ ሰጠ ሁሉ ከእዚህ ሁኔታ በመማር ራሱን በሙሉ ለሌሎች ለመስጠት የተዘጋጀ፣ ከራሱ እና እርሱ ካለው ሐብት ንብረት ጋር ያለውን ቁርኝት መስበር ለቻሉ ሰዎች ሁሉ የሚሰጥ ነጻ የደስታ ስጦታ ነው።

ሁላችንም በቅድሚያ የክርስቶስ ደቀመዛሙርትን ተልዕኮ በሁሉም ስፍራ በተሳካ መልኩ ይከናወን ዘንድ፣ እያንዳንዳችንን እግዚአብሔር እንደሚወደን፣ እኛን እንደሚያድነን እና የእርሱ መንግሥት ተካፋዮች እንድንሆን እንደ ሚፈልግ እንድናውጅ የተሰጠን ተልዕኮ በተገቢው ሁኔታ ማከናወን እንችል ዘንድ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጥበቃ እና ድጋፍ እንማጸናለን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 30/3011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት) -ቫቲካን

 

 

25 Jul 2026, 16:14