ፈልግ

የዘሪው ምሳሌ የዘሪው ምሳሌ  (©LIGHTFIELD STUDIOS - stock.adobe.com)

የሐምሌ 19/2018 ዓ.ም የ15ኛው እለተ ሰንበት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.      ኢሳያስ 55፡10-11

2.     መዝሙር 64

3.     ሮም 8፡18-23

4.    ማቴ 13፡1-23

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የዘሪው ምሳሌ

በዚያ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቷቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ነገር ግን ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ ሌላውም ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”

ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤

“እያዩ፣ አያዩም፤

እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤

እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤

“ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤

ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።

የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤

ጆሯቸውም አይሰማም፤

እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤

ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣

በጆሯቸው ሰምተው፣

በልባቸውም አስተውለው፣

ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’

የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።

“እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። ነገር ግን ሥር ባለመስደዱ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራን ሰው ይመስላል። በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳቹ!

በዛሬው አሥራ አምስተኛ መደበኛ ሳምንት እለተ ሰንበት ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 13፡1-23) ኢየሱስ እኛ ሁላችን በደንብ የምናውቀውን ምሳሌ ማለትም የተለያየ የአፈር ዓይንት ያላቸው ስፍራዎች ላይ የወደቁትን ዘሮች የሚገልጸውን የዘሪውን ምሳሌ በስፍራው ለተሰበሰቡ እጅግ ብዙ ሰዎች ሲናገር እንሰማለን።፡ በዘሮቹ የተወከለው የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን፣ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ረቂቅ ቃል አይደለም ፣ ነገር ግን በማርያም ማህፀን ውስጥ የተጸነሰ ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ የተወለደው የአብ ቃል ክርስቶስ ራሱ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ማለት የክርስቶስን ስብዕና መቀበል ክርስቶስ ራሱን መቀበል ማለት ነው።



የእግዚአብሔርን ቃል የምንቀበልበት የተለያዩ መንገዶች አሉ። በአፋጣኝ ሁኔታ በመንገድ ላይ የተዘራውን እና ወፎች ወዲያው መጥተው ዘሩን ከመንገድ ላይ ወስደው የተመገቡትን ዓይነት ሰው ልንሆን እንችላለን። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ትኩረታችንን ሊስብ በሚችለው በተደቀኑብን የዘመናችን ትልቅ አደጋ የተነሳ ነው። በብዙ ወሬዎች የተነሳ በደረሰባቸው በደል ተበሳጭተው ፣ በብዙ ርዕዮተ-ዓለም ፣ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ትኩረትን ሊከፋፍሉ በሚችሉ አጋጣሚዎች የተነሳ የጸጥታ ፣ የማስታወስ ፣ ከጌታ ጋር የመነጋገር ፍላጎቶቻችንን ልናጣ እንችላለን፣ ይህም እምነት እንድናጣ እና የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንቀበል ሊያደርገን ይችላል። እኛ ሁሉንም ነገር እየተመለከትን ፣ በዓለም ነገሮች ትኩረታችን እየተወሰደ እንረበሻለን።

ሌላ አማራጭ: - አነስተኛ የአፈር ይዘት እንዳለው ድንጋያማ መሬት በመሆን የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል እንችላለን። እዚያም ዘሩ ቀደም ብሎ ይበቅላል፣ ግን ወዲያውም ይደርቃል ፣ ምክንያቱም መሬቱ ድንጋያማ ስለሆነ ሥሩን ወደ ጥልቁ መላክ ስለማይችል ነው።  የእግዚአብሔር ቃል በቅን መንፈስ ወዲያውኑ የሚቀበሉ ሰዎች ምስል ነው ፣ ሆኖም ቃሉ በልብ ውስጥ ጠልቆ ስላልገባ ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ቃል አይመስልም።  እናም በቅድሚያ አንድ ችግር ወይም መከራ ሲያጋጥመን፣ የህይወት መረበሽ ሲያጋጥመን የዚህ ዓይነቱ እመንት በጣም ጠንካራ ባለመሆኑ የተነሳ በድናጋያማ መሬት ላይ እንደ ተዘራው ዘር ወዲያውኑ ይድክምና ይደርቃል።

እንደገና እኛ በምሳሌው ውስጥ ኢየሱስ የተናገረውን ሦስተኛ ዕድል በእሾሃማ ቁጥቋጦዎች በሚበቅሉበት ስፍራ እንደ ወደቀው ዓይነት ዘር የእግዚአብሔርን ቃል እንቀበላለን። እሾህ እኛን ብዙ ጊዜ የሚያሳስቱንን ሀብት፣ ስኬት ፣ ስለዓለም ጉዳዮች ማሰብ የመሳሰሉትን ይወክላል።  እዚያም ቃሉ ትንሽ ያድጋል ፣ ነገር ግን እሾሁ አንቆ ይይዘዋል፣ ጠንካራ ስላልሆነ ይሞታል ወይም ፍሬ አያፈራም።

በመጨረሻም - አራተኛው ዕድል - እኛ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ እንደ ጥሩ መሬት አድርገን እንቀበላለን። እዚህ እና እዚህ ጋር ብቻ ነው ዘሩ ሥሩን ወደ ጥልቁ መሬት መዘርጋት የሚችለው፣ ከዚያም ፍሬ ያፈራል። በዚህ ለም መሬት ላይ የወደቀው ዘር ቃሉን የሚሰሙ ፣ የሚቀበሉትን ፣ በልባቸው ውስጥ የሚጠብቁትን እና በዕለት ተዕለት ኑሮው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉትን ሰዎች ይወክላል።

ይህ የዘሪው ምሳሌ በተወሰነ ደረጃ የሁሉም ምሳሌዎች “እናት” ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፣ ምክንያቱም ቃሉን ማዳመጥ እንደ ሚገባን ስለሚነግረን ነው። ይህ ምሳሌ ፍሬያማ እና ውጤታማ ዘር መሆን እንደ ሚገባን ያስታውሰናል ። ያለምንም ብክነት እና በጥንቃቄ እግዚአብሔር በልግስና በሁሉም ስፍራ ዘሩን ይበትነዋል። የእግዚአብሔር ልብ እንዲሁ ነው! እያንዳንዳችን የቃሉ ዘር የሚወድቅበት መሬት ነን፣ ማንም አይገለልም። ቃሉ ለሁላችን ተሰጥቷል። “ምን ዓይነት መሬት ነኝ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።  እኔ በመንገድ፣ በድንጋያማ፣ በቁጥቋጦ ስር የወደቀውን ዘር ነው የምመስለው? ከፈለግን ግን በእግዚአብሔር ጸጋ መልካም የሆንን ፣ የቃሉ ዘርን ለማሳደግ በጥሩ ሁኔታ የታረሰ በጥንቃቄ ዘሩን የምናበቅል እና ቃሉን የምናበቅል መልካም መሬት ለመሆን እንችላለን። ቀድሞውኑ በልባችን ውስጥ ይገኛል፣  ነገር ግን ፍሬ እንዲያፈራ ማድረጉ የእኛ ተግባር ነው፣ ይህም ለዘሩ በምናደርገው ጥንቃቄ እና አቀባበል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በብዙ ፍላጎቶች ፣ በብዙ ጥሪዎች በመዘናጋት ነፃ በሚያደርገን በጌታ ቃል እና በብዙ ድምጾች መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት እንቸገራለን። የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ እና ማንበብ ጠቃሚ የሆነው በዚሁ ምክንያት ነው።  እኔ እንደገና ከዚህ ቀደም የመከርኩዋችሁን ምክር እንደ ገና ለመናገር እሻለሁ፣ አንዲት ትንሽዬ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በኪስ ልትገባ የምትችል መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ ይዛችሁ እንድትጓዙ በድጋሚ እመክራችኋለሁ። እናም በእየለቱ ትንሽዬ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል በማንበብ ከመጸሐፍ ቅዱስ ጋር ያላችሁን ልምድ አዳብሩ፣ እግዚአብሔር የሚሰጥህን ዘር ተረዱ እናም በየትኛው ምድር ላይ እንደምትቀበል አስቡ።

እግዚአብሔር በታሪክ መካከል እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ስለሆነ ተስፋን ለማግኘት በሚረዱን በኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንን እንቀጥላለን። ዛሬ በመጠኑም ቢሆን ለየት ባለ ምሳሌ ላይ ላተኩር እወዳለሁ። ምክንያቱም ይህ ምሳሌ የሌሎች ሁሉ ምሳሌዎች መግቢያ ነው። በማቴ. 13፡1-17 ላይ የተጻፈውን የዘሪውን ምሳሌ እጠቅሳለሁ። ይህም በዛሬው ዘመን ወንጌልን ስለ መስበክ ብዙ የሚያስተምረን በመሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳቡን ለማጋራት የተጠቀመበትን መንገድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መገንዘብ እንችላለን።

እያንዳንዱ ምሳሌ ከዕለት ተዕለት የሕይወት ልምድ ጋር የተገኘውን ታሪክ ይነግራል። ታሪኩን የበለጠ በመንገር ወደ ጥልቅ ትርጉም ይመራናል። ምሳሌው በውስጣችን ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋል። በዕይታ ላይ ብቻ እንዳንቆም ይጋብዘናል። ‘ከተነገረኝ ታሪክ ወይም ከቀረበልኝ ምሳሌ አስቀድሞ በዚህ ታሪክ ውስጥ የት ነው የምገኘው?’ ብዬ ራሴን መጠየቅ እችላለሁ። ይህ ምሳሌ ለሕይወቴ ምን ያስተምራል? እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ምሳሌ’ የሚለው ቃል የመጣው፥ ‘ፓራባሌይን’ ከሚለው ከግሪክ ግስ ሲሆን፥ ትርጉሙም ፊት ለፊት ማውጣት ማለት ነው። ምሳሌው የሚያነሳሳኝን እና ራሴን እንድጠይቅ የሚገፋፋኝን ቃል ከፊት ለፊቴ ያስቀምጣል።

የዘሪው ምሳሌ ስለ እግዚአብሔር ቃል እና ስለሚያስገኘው ውጤት በትክክል ይናገራል። በእርግጥም እያንዳንዱ የወንጌል ቃል በሕይወታችን ውስጥ በእርሻ ላይ በተበተነ ዘር ይመሰላል። ኢየሱስ የዘሩን ምሳሌ ብዙ ጊዜ ተጠቅሟል። የተለያየ ትርጉም አለው። በማቴ. ምዕ. 13 ላይ የተነገረው የዘሪው ምሳሌ ሌሎች ተከታታይ አጫጭር ምሳሌዎችን ያያዘ ሲሆን፥ አንዳንዶቹም በምድሪቱ ላይ ስለሚሆነው ነገር በትክክል ይናገራሉ። ስለ ስንዴው እና ስለ እንክርዳዱ፣ ስለ ሰናፍጭ ዘር፣ በእርሻ ውስጥ ስለተደበቀ ውድ ሃብት ይናገራል። ታዲያ ይህ አፈር ምንድን ነው? የእኛ ልብ ነው። ነገር ግን ደግሞ የምንኖርበት ዓለም፣ ማኅበረሰብ እና ቤተ ክርስቲያንም ጭምር ነው። በእውነት የእግዚአብሔር ቃል ፍሬያማ ያደርገናል፤ ስለ እያንዳንዱ እውነታ ይገልጻል።

በመጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤቱ ወጥቶ ብዙ ሰዎችን በዙሪያው ሲሰበስብ እናየዋለን (ማቴ. 13፡1)። ቃሉ የሚማርክ እና ቀልብ የሚስብ ነው። በሰዎች መካከል ብዙ የተለያዩ ሁኔታዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ወይም ትምህርት ለሁሉም ነው። በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ በተለያየ መንገድ ይሠራል። ይህ አውድ የምሳሌውን ትርጉም በደንብ እንድንረዳ ያስችለናል።

አንድ ያልተለመደ ዘሪ ለመዝራት ወጣ። ዘሩ የት እንደሚወድቅ ግድ የለውም። ፍሬ ማፍራት በማይቻልበት ቦታ ዘሩን ይበትናል። በመንገድ ላይ፣ በድንጋያማ ቦታ እና በእሾህ መካከል ሁሉ ዘሩን ይበትናል። ይህ አስተሳሰብ አድማጭን በማስገረም፥ ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ ይገፋፋል።

ነገሮችን ማስላት ለምደናል። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን ስለ ፍቅር ሲወራ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ይህ አባካኙ ዘሪ ዘሩን የሚበትንበት መንገድ እግዚአብሔር እኛን የሚወድበት መንገድ ምሳሌ ነው። በእርግጥ የዘሩ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው መሬቱ ወይም እርሻው በሚቀበልበት መንገድ እና ዘሩ በሚኝበት ሁኔታ ላይ ቢሆንም፥ ከሁሉ አስቀድሞ በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ የቃሉን ዘር በሁሉም የአፈር ዓይነት ላይ እንደሚበትን ይነግረናል። ያም እኛ በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ፣ አንዳንድ ጊዜ ትኩረታችን የበለጠ በተከፋፈለበት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሕይወታችን ልንሸከመው በማንችልበት ጊዜ ሲሆን፥ ሌላ ጊዜ ግን ፈቃደኞች የምንሆንበት እና የምንቀበልበት ጊዜም አለ። እግዚአብሔር ይተማመናል፤ ይዋል ይደር አንድ ቀን ዘሩ እንደሚያብብ ተስፋን ያደርጋል። የሚወደንም እንደዚህ ነው። ለም መሬት እንድንሆን ባይጠብቀንም ነገር ግን ሁልጊዜ በልግስና ቃሉን ይሰጠናል። ምናልባትም እርሱ እንደሚያምነን በማየታችን የተሻለ አፈር የመሆን ፍላጎት በውስጣችን ይቀጣጠል ይሆናል። ይህ በእግዚአብሔር የልግስና እና የምሕረት ዓለት ላይ የተመሠረተ ተስፋ ነው።

ኢየሱስ ዘሩ ፍሬ የሚያፈራበትን መንገድ ሲናገር፥ ስለ ሕይወቱም ጭምር እየተናገረ ነው። ኢየሱስ ቃልም ነው፣ ዘርም ነው። ዘር ፍሬን እንዲያፈራ ከተፈለገ መሞት አለበት። ስለዚህ ይህ ምሳሌ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ሊሞት ዝግጁ እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስም ሕይወታችንን ለመለወጥ ሲል መሞቱን ይነግረናል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ ዛሬ በምን ዓይነት የሕይወት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን? በዘር ምሳሌ የቀረበውን ቃሉን የምንቀበልበትን ጸጋ እንዲሰጠን ዘወትር እግዚአብሔርን እንለምነው። ፍሬ የሚሰጥ መሬት አለመሆናችንን ከተገነዘብን ተስፋ መቁረጥ የለበንም። ነገር ግን እህል የሚያበቅል የተሻለ መሬት እንዲያደርገ እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው።

እኛ ለራሳችን እና ለወንድሞቻችን መልካም ፍሬን ማፍራት እንድንችል እሾሃማ ወይም ድንጋያማ የሆንን መሬት ሳንሆን ዘሩ የሚወድቅበት እና ብዙ ፍሬ የሚፋራበት መልካም መሬት መሆን እንችል ዘንድ የመልካም እና ለም መሬት ተምሳሌት የሆነችሁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)- ቫቲካን 

25 Jul 2026, 16:06