ፈልግ

ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር   (https://christian.net/wp-content/uploads/2024/02/when-were-the-apostles-empowered-to-begin-the-mission-of-jesus-1708180246.jpg)

የጥር 24/2018 ዓ.ም የሦስተኛው መደበኛ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ኢሳያስ 8፡23-9፡3

2.    መዝሙር 26

3.    1ቆሮ 1፡10-13.17

4.    ማቴዎስ 4፡12-23

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ

ኢየሱስ ዮሐንስ እንደታሰረ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ። ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም ክልል ወደ አለችው በባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ በዮርዳኖስ ማዶ ያለ፥ የባሕር መንገድ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና በሞት ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።”

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ።

ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደ ጠራ

በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ሳለ፥ ሁለት ወንድማማቾች፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። እርሱም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያውኑ መረባቸውን ጥለው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በታንኳ ውስጥ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር መረባቸውን ሲጠግኑ አየና ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በዛሬው የመስዋተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ከማቴ. 4: 12-23 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በገሊላ ሐይቅ አጠገብ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ብለው ሁሉን ነገር ስለተው የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ጥሪ ይተርካል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት መካከል ከጥቂቶቹ ጋር፣ ከአጥማቂው ዮሐንስ ጋር በሌላ አጋጣሚ ተገናኝቶ ነበር።  እግዚአብሔርም የእምነት ዘርን በእነዚህ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ አስቀምጦ ነበር። (ዮሐ. 1: 35-39) ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሚኖሩበት አካባቢ ሄዶ ይፈልጋቸው ጀመር። ይህም እግዚአብሔር ዘወትር እንደሚፈልገን ያስረዳል። በዚህ ጊዜ ግን ‘ተከተሉኝ!’ በማለት በቀጥታ ጥሪውን አቀረበላቸው። (ማቴ. 4: 19) ደቀ መዛሙርትም ወዲያው መረባቸውን ትተው ኢየሱስን ተከተሉት (ማቴ. 4: 20) ጊዜ ወስደን በዚህ ታሪክ ላይ እናሰላስል። ያ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ሙሉ ሕይወታቸውን የሚያስታውሱበት፣ በቅዱስ ወንጌል ታሪክ ውስጥ የሚካተቱበት እና ከኢየሱስ ጋር ወሳኝ ግንኙነት ያደረጉበት ወቅት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስን ተከተሉት። እሱን ለመከተል ብለው ያላቸውን ንብረት በሙሉ ነገር ተው። 

 

‘ኢየሱስን ለመከተል ብለው ያላቸውን ሁሉ ነገር ተው!’ ኢየሱስን መከተል ሲጀምሩ ሁሌ እንደዚህ ነው። ኢየሱስን መከተል በአንድ ነገር በመሳብ ስሜት ሊጀምር ይችላል። ምናልባትም በሌሎች ሰዎች ምክንያት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስን ለመከተል ያለን ግንዛቤው ግላዊ ሊሆን ይችላል። በልብ ውስጥ ብርሃን ሊበራ ይችላል። ክስተቱን ለሌሎች ማጋራቱ የሚያስደስት ይሆናል፡- ‘ያ ለአገልግሎት እንድነሳሳ ያደረገኝ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ልቤን ነክቶኛል!’ ብለን እናወራለን። በመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ላይ የሆነው ይህ ነው (ዮሐ. 1: 40-42)። ነገር ግን ፈጠነም ዘገየም ኢየሱስን ለመከተል ሁሉን ነገር መተው የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመጣል (ሉቃ. 11: 27-28)። መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ አንዳንድ እርግጠኞች የሆንንባቸውን ነገሮች በመተው፣ ‘ይህን  አዲስ ጀብድ ልጀምር ወይስ ልቆይ?’ በማለት እራሳችንን እንጠይቃለን። ይህ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ወሳኝ ጊዜ ነው። ምክንያቱም የሁሉም ነገር ትርጉም ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ወቅት ነውና። አንድ ሰው በሕይወት ጉዞ ላይ ድፍረት ካላገኘ የእራሱ ሕልውና ተመልካች ሆኖ የመቆየት እና እምነትን ግማሽ መንገድ ብቻ የመጓዝ አደጋ ያጋጥመዋል።

ከኢየሱስ ጋር መሆን ወይም ከእርሱ ጋር እንዳንሆን የሚያግዱ ነገሮችን ወደ ጎን ማለት ድፍረትን ይጠይቃል። ወደ ጎን መተው ያለብን ነገር ምንድነው? ወደ ጎን መተው ያለብን ክፉ ነገሮቻችን እና ኃጢአቶቻችን ናቸው። እነዚህ በሙሉ በሕይወታችን ውስጥ እንቅፋት በመሆን ወደ ፊት እንዳንራመድ ያደርጉናል። እንቅፋት የሚሆኑንን ነገሮች መተው ስንጀምር የእግዚአብሔርን ምሕረት ጠይቆ መጀመር ትክክል ነው። ለሠራናቸው ኃጢአቶች ምሕረትን መጠየቅ ጥሩ ነው።

‘ወደፊት መራመድ እንድችል እነዚህን ወይም እነዚያን ክፉ ነገሮች መተው አለብኝ!’ ብሎ መወሰን ያስፈልጋል። ሕይወትን በሙላት እንዳንኖር የሚያግዱን ነገሮችን መተው ያስፈልጋል። ለምሳሌ ፍርሃትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ በግል ደኅንነት ላይ ያሉንን ዋስትናዎች መተው ያስፈልጋል። በብዙ የማይረቡ ነገሮች ላይ የምናባክነውን ጊዜንም ያካትታል። ለምሳሌ አድካሚ የሆነውን እና በአገልግሎት ላይ የሚመጣውን አደጋ ማስወገድ ያስፈልጋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ወዳጅነት ለማደግ ጊዜአችንን ለጸሎት መሰጠት ምን ያህል ያማረ ነው። እንዲሁም እናት እና አባት ለመሆን ብለው የሚያስደስቱ ብዙ ጀብዶች እራሳቸውን በመነጠል ጸጥታ ያለበትን ሕይወት የሚኖሩ ወጣት ቤተሰቦች እንዳሉ አስባለሁ።

በእርግጥ ይህ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ነገር ግን ይህን ደስታ ለማግኘት የተወሰኑ ምቾቶችን መተው ትክክለኛ ምርጫ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። የተወሰኑ ባለሙያዎች፣ ለምሳሌ የሕክምና ዶክተሮች ወይም የጤና ሠራተኞች እራሳቸውን ለሙያው ብቁ ለማድረግ ብዙ ነፃ ጊዜያትን በጥናት ያሳልፋሉ። በርትተው ቀን እና ሌሊት ሚሠሩ፣ ብዙ የአካል እና የአእምሮ መስዋዕትነት የሚከፍሉ፣ ለታመሙ ሰዎች ጉልበታቸውን የሚያውሉ የጤና ባለሙያዎች እንዳሉ አውቃለሁ። የምቾት ነገርን በመተው ጠረጴዛ ላይ እንኳ ምግብ አስቀምጠው መብላት የማይፈልጉ ሠራተኞች እንዳሉ አስባለሁ። ባጭሩ፣ ሕይወትን ለመኖር አንዳንድ ነገሮችን የመተው ፈተናን መቀበል አለብን። ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ግብዣ ለእያንዳንዳችን ያቀርብልናል።

ስለዚህ እነዚህን አንዳንድ ጥያቄዎችን ልጠይቅ። ከሁሉ አስቀድሞ፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኘሁበት ጊዜ መቼ ነበር? እያንዳንዳችን የሕይወት ታሪካችንን ልናውቅ ይገባል። እራሳችንን መጠየቅ ያለብን ሌላው ጥያቄ፥ በሕይወቴ ውስጥ ኢየሱስን ያገኘሁበት ጉልህ ጊዜ መቼ ነበር? በሕይወቴ ውስጥ የተከሰተ አንድ መልካም ነገር የቱ ነው? ጠቃሚ ያልሆኑ ነገሮችን በመተዌ በሕይወቴ ውስጥ ያተረፍኩት መልካም እና ጠቃሚ ነገር አለን? ዛሬስ ቢሆን እንድተወው ኢየሱስ የሚጠይቀኝ ነገር አለ? በእውነት “አዎ” ለማለት መተው ያለብኝ ቁሳዊ ነገር፣ የአስተሳሰብ መንገድ እና አመለካከትቭ የቱ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስን በሚገባ ለመከተል ምን መተው እንዳለብን እና እንደ እርሷ ለእግዚአብሔር አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን። ኢየሱስን ለመከተል ፈልጋችሁ ከሆነ የማይጠቅማችሁን ነገር በሙሉ ችላ ማለትን አትፍሩ። ይህን የምናደርግ ከሆነ ሁሌም የተሻልን ሆነን እንገኛለን።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)- ቫቲካን

 

 

31 Jan 2026, 14:48