ፈልግ

የጥር 24/2018 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርእዮ 2ኛ ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ የጥር 24/2018 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርእዮ 2ኛ ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ  (ANSA)

የጥር 24/2018 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርእዮ 2ኛ ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፡-

1.    2ኛ ቆሮ. 1፡13-24

2.   1ዩሐ. 2፡22-29

3.   ሐዋ. 13፡20-27

4.   ሉቃ 2፡42-52

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም። ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

የእለቱ አስተንትኖ

በዛሬው እለት በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 2፡42-52)  ይህ የናዝሬት ከተማ ነዋሪ የሆነው ቤተሰብ ማለትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ቅዱስ ዮሴፍ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ያደረጉትን የጉዞ ሁኔታ ያብራራል። ከበዓሉ መልስ ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ሰዓት የአስራ ሁለት ዕድሜ ልጃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው አለመሆኑን ያስተውላሉ። በዚህም ምክንያት እጅግ በመጨነቅ ለሦስት ቀናት ያህል ሲፈልጉት ከቆዩ በኋላ በቤተመቅደስ ውስጥ በመምሕራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸው እና ጥያቄን ሲያቀርብላቸው ባገኙት ጊዜ ተገረሙ። እናቱ ማርያምም ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህን? አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር አለችው።

በዚህ የወንጌል ክፍል በተገለጸውና ይህን ቤተሰብ ባጋጠማቸው ሁለት ክስተቶች፣ እነዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ማርያምና የቅዱስ ዮሴፍ መገረም እና መጨነቅ ላይ ማስተነተን እንደሚገባ ማሳሰብ እወዳለሁ።

የናዝሬት ከተማ ነዋሪ በሆነው በዚህ ቤተሰብ ማለትም በቅድስት ድንግል ማርያም፣ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስና በቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት መካከል የልጃቸው መሰወር እና አልፎ ተርፎም በመምህራን መካከል ተቀምጦ በመወያየት ላይ እያለ ሲያገኙት የተሰማቸው ዓይነት ግርምት ከዚህ በፊት ፈጽሞ አላጋጠማቸውም ነበር። ይህ መገረም የታየው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስን ሲሰሙት የነበሩ መምህራን ሁሉ በማስተዋል ችሎታው በጥበቡና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ለመሆኑ አድናቆት መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? አድናቆትንስ እንድንሰጥ የሚያደርገን ምንድነው?  አንድን ነገር ማድነቅና በአንድ ነገር ላይ መገረም ማለት፣ ለምናየው ወይም ለምንሰማው ነገር ትልቅ ዋስን በመስጠት፣ የራሳችንን የተሳሳተ ግምት ወይም የምንሰጠውን ዝቅተኛ ትርጉም ማስወገድ ማለት ነው። እንደመሰለው የራሱን መንገድ በመከተል ብቻ ትርጉም ወይም የተሳሳተ ተርጉም የሚሰጥ ሰው የአድናቆትና  የግርምትን ትክክለኛ ትርጉም ሊያውቅ አይችልም። አድናቆትን መስጠት ማለት ሌሎች ሰዎች የሚፈጽሙትን ተግባር ለመመልከት ወይም ለማጤን ራስን ሙሉ በሙሉ ክፍት ማድረግ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ወይም ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም ደግሞ የቤተሰብን ይሕወት የወሰድን እንደሆነ በቤተሰብ መካከል የሚከሰቱትን ቅራኔዎች ወይም አለመስማማቶችን ለማስወገድ እጅግ ጠቃሚ መንገድ ነው። በቤተሰብ መካከል ችግሮች ሲከሰቱ ልባችንን በማደንደን፣ ትክክለኛው እኔ ብቻ ነኝ ማለትን በማስወገድ የሌላውንም ሰው መልካም ጎኑን ማስታወስ ወይም ባሰብ ያስፈልጋል። ለመልካም ጎኑ፣ ለመልካም ሥራው፣ ለመልካም አስተሳሰቡ፣ ለመልካም ባሕሪው አድናቆትን መስጠት ይስፈልጋል። ይህን የመሰለ አካሄድ በቤተሰብ መካከል ፍቅርን በመጨመር አንድነታቸውንም ይሳድጋል። በቤተሰቦቻችሁም መካከል ችግር ወይም ቅራኔ ቢከሰት ያ የቤተሰብ ወገን የሚያበረክተውን መልካም ተግባር ወይም መልካም ጎኑን በማስታወስ ለመልካም ተግባሩ አድናቆትን ማሳየት ያስፈልጋል። ይህም በቤተሰብ መካከል የተፈጠረውን ቁስል ለመጠገን፣ ቅራኔንም ለማስወገድ ያግዛል።

በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 2 ላይ የተጠቀሰው ሌላው በልጃቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ከመካከላቸው መጥፋት ምክንያት በማርያምና በዮሴፍ ላይ የደረሰው ድንጋጤ ያስከተለው ጭንቀት ነው። ይህ በማርያምና በዮሴፍ መካከል የተፈጠረው ከባድ ጭንቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ መካከል ትልቅ ስፍራ እንዳለው ያስገነዝባል። ድንግል ማርያምና ዮሴፍም በሕብረት ሆነው ልጃቸው በጥበብና በማስተዋል፣ በመልካም ሁኔታ እንዲያድግ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉ ነበር። ልጃቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ እድሜውም እየጨመረ በሄደ ቁጥር በጥበብና በጸጋ ስጦታዎች እየተሞላ ማደጉን ይመለከቱ ነበር። ይህንን በልባቸው ውስጥ በመያዝ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ። የናዝሬቱ ቤተሰብም ቅዱስ የተባለበት ምክንያትም ይህ ነው። ሕይወታቸውን ለኢየሱስ ፍቅር ስላዋሉትና ሙሉ ትኩረታቸውን በኢየሱስ ላይ በማድረጋቸው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመካከላቸው ጠፍቶባቸው  ያሳለፏቸው ሦስቱ አስጨናቂ ቀናት፣ እኛም ከኢየሱስ ክርስቶስ ተለይተን እንደምናሳልፋቸው፣ ከእርሱ ተለይተን እንደምንቆይባቸው ቀናት ማሰብ ይኖርብናል። ለሦስት ቀናት ያህል ኢየሱስ ክርስቶስን ዘንግተን ብቻችን መቆየት፣ ወደ እርሱ ጸሎት ሳናደርስ መዋል፣ ቅዱሳት መጽሕፍትን ሳናነብ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃና ወዳጅነት ሲቀርብን የሚያጋጥመን ጭንቀት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ብዙን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን በልቤ ሳላስብ ቀናት ያልፋሉ። ይህ ደግሞ መልካም አይደለም። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጭንቀት ሊሰማን ይገባል።  ለሦስት ቀናት ያህል ሲፈልጉት ከቆዩ በኋላ ልጃቸው በቤተመቅደስ ውስጥ በመምሕራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው፣ ሲያስተምራቸውም እንዳገኙት ሁሉ እኛም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሆነን መለኮታዊው አምላካችንን ማግኘት፣ የእርሱን የድነት ቃልን ማዳመጥ ይኖርብናል። በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታችን በኩል ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል እናገኘዋለን። በዚህም ወቅት እርሱ በቃሉን በኩል ይናገረናል። ለመንገዳችንም ብርሃን ይሆነናል። በምስጢራቱ አማካይነት ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል በየቀኑ ይሚያጋጥሙንን ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን እንድናልፍ ሃይል ይሆነናል።

ዛሬ እነዚህን ሁለቱን ቃላት ማለትም መገረምንና ጭንቀትን ይዘን ወደየመጣንበት እንመለስ። በተጨማሪም በቤተስብ መካከል ሌሎቹ ሰዎች የሚያከናውኑትን መልካም ተግባር ስመለከት በእውነት በመገረም ለእነርሱ ያለኝን አድናቆት አሳያቸዋልሁ? ይህን በማድረግ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠሩትን ችግሮች ለማቃለል እሞክራለሁ? ከኢየሱስ ክርስቶስ በርቅሁ ጊዜስ ጭንቀት ይሰማኛል ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ለዓለም ቤተሰብ በሙሉ፣ በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች ፍቅርንና ሰላምን ላጡት በሙሉ እንጸልይ። ለእነዚህ ቤተሰቦች የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ጥበቃ እንዳይለያቸው ጸሎታችንን እናቅርብ።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)-ቫቲካን      

31 Jan 2026, 14:03