አሜሪካ በኢራን ላይ 'ተከታታይ ከባድ' ጥቃቶችን መፈጸሟ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዮርዳኖስ የሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ የተተኮሱትን የኢራን ሚሳኤሎች ተከትሎ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ አዳዲስ የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟን የገለጸች ሲሆን፥ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) እንደገለፀው እርምጃው የኢራንን የሀይል ጥቃት ሙከራዎች ለመመለስ የተወሰደ ጠንካራ ምላሽ እንደሆነ እና በኢራን ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ወታደራዊ ኢላማዎች መመታታቸው አረጋግጧል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት አሜሪካ በኢራን ላይ ከባድ እርምጃ መውሰድ መጀመሯን ገልጸው፣ አሁን የአሜሪካ ተራ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፥ የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) በበኩሉ በዮርዳኖስ በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ አየር ጣቢያ ላይ ሚሳኤል መተኮሱን ቢገልጽም፣ የአሜሪካና የዮርዳኖስ የአየር መከላከያ ስርዓቶች ሚሳኤሎቹን ሙሉ በሙሉ በአየር ላይ ማክሸፋቸው ተነግሯል።
የኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፤ የአሜሪካ የቅርብ ጊዜዎቹ ጥቃቶች በቁሽም ደሴት ላይ የሁለት ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ደቡባዊ እና ምዕራባዊ ክፍሎች የሚገኙ ሌሎች አካባቢዎችም መመታታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት ውስጥ የኢራን ኃይሎች በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አቅራቢያ የሚንቀሳቀሱ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማሸበራቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ የቀጣናው ስጋት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እያለ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በፍጥነት” ስምምነት ሊደረስ የሚችልበት ዕድል በመኖሩ ኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ማድረጋቸውን ቅዳሜ ዕለት መግለፃቸው የተነገረ ሲሆን፥ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “በፍጥነት ስምምነት ላይ መድረስ እንዲቻል የጥቃት እርምጃው እንዲቋረጥ” መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የሚደረሰው ስምምነት ሆርሙዝ ወሽመጥ ወዲያውኑ እንዲከፈት እንዲሁም “ኢራን የደቀነችው የኒውክሌር ስጋት” እንዲቆም የሚያደርግ ነው ያሉ ሲሆን፥ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከእስራኤል ጋር በመተባበር መሆኑንም ተናግረዋል።
በሚያዝያ ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ በኋላ አሜሪካ እና ኢራን ተከታታይ ጥቃቶችን እና የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎችን መለዋወጣቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱ ሃገራት መካከል ለወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የታሰበ እንደነበር ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ፓኪስታን ሐሙስ ዕለት በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እየቀጠለች መሆኑን የገለጸች ሲሆን፥ ሁለቱም ወገኖች ወደ ኢስላማባድ የመግባቢያ ስምምነት እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቧል።
ባለፈው ሳምንት የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጣሂር ሁሴን አንድራቢ “በተለይም በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አከባቢ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና ፍጥነቱን ለማርገብ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ድርድር ቀጥሏል” ሲሉ በኢስላማባድ ባደረጉት አጭር መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል።