ፈልግ

ነርስ ኤልሳቤጥ አርጄሚ ነርስ ኤልሳቤጥ አርጄሚ  

ነርስ ኤልሳቤጥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስለ ወንድሟ የጻፈችውን የመጽሐፍ ስጦታ አበረከተች

በስፔይን ባርሴሎና የሚገኘው የ “ICOF” ሆስፒታል ነርስ ኤልሳቤጥ አርጄሚ በካስቴል ጋንዶልፎ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ተገናኝታለች። ነርስ ኤልሳቤጥ ለቅዱስነታቸው ያበረከትላቸው መጽሐፍ፥ “ለመኖር መሞትን መማር” የተሰኘ ሲሆን፥ በጡንቻ ሕመም በ29 ዓመቱ ያረፈውን የወንድሟ ዛቪየር ምስክርነት የሚያወሳ እንደ ሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ነርስ ኤልሳቤጥ ቅዱስነታቸውን ያገኘቻቸው ማክሰኞ ነሐሴ 12/2018 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ ከሚገኘው ማረፊያቸው ወደ ቫቲካን ለመመለስ ሲዘጋጁ እንደ ነበር ታውቋል።

ነርስ ኤልሳቤጥ ከቅዱስነታቸው ጋር በነበራት አጭር ቆይታ ውስጥ “Learning to Die in Order to Live” የተሰኘ መጽሐፍ ቅጂ በስጦታነት ያበረከትላቸው ሲሆን፥  መጽሕፉ ባለፈው ዓመት በ29 ዓመቱ በጡንቻ መታወክ ሕመም ያረፈውን የወንድሟ ዛቪየር አርጄሚ ምስክርነት የሚያወሳ እንደሆነ ታውቋል።

“ሕይወትን በጣም የሚወድ ወንድም ነበር” የምትለው ኤልሳቤጥ፥ ዛቪየር ሰዎችን እንደሚወድ እና ሰዎችም እርሱን በጥልቅ እንደሚወዱት ይናገር እንደ ነበር ገልጻ፥ ያ ፍቅር ለሕልውናው ትርጉም እንደሰጠ አስረድታለች።

“ሕመሙ ሕይወቱን ቢቀርጸውም ነገር ግን ትርጉሙን አልገለጸለትም” ያለችው ኤልሳቤጥ፥ ዛቪየር ከብዙ ሰዎች ጋር መሆን እና መርዳት መቻሉን በማስታወስ፥ እጅግ የተቀደሰ ሕይወት እንደኖረ እና ካረፈ በኋላም ብዙዎች ወደ ሕይወት እንደ ተመለሱ ተናግራለች።

“ለመኖር መሞትን መማር” የተሰኘ መጽሐፍ
“ለመኖር መሞትን መማር” የተሰኘ መጽሐፍ

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዮ ጋር የነበራት አጭር ቆይታ

ነርስ ኤልሳቤጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር የነበራት ቆይታ አጭር ቢሆንም በውስጧ ዘላቂ ተጽዕኖ አሳድሯል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መጽሐፉን ከተቀበሉ በኋላ ሊያዳምጧት ጊዜ መስጠታቸውን እና እንደ አባት በፍላጎት እና በፍቅር ይመለከቷት እንደ ነበር አስታውሳለች።

ኤልሳቤጥ መጽሐፉን ለቅዱስነታቸው ማበርከት የፈለገችው በባርሴሎና ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ቢሆንም ነገር ግን ሳይሳካላት ቀርቶ በመጨረሻ በካስቴል ጋንዶልፎ ባገኘቻቸው ወቅት እውን መሆኑ ታውቋል።

ይህ ምልክት ልዩ ትርጉም የያዘ ሲሆን ሕይወቱ በሕመም የተመሰከረለት ወጣት ምስክርነት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እምነትንም ጭምር አስገኝቶላቸዋል። የሕይወት ዋጋ የሚለካው አንድ ሰው በሚኖርበት ሁኔታ ላይ ብቻ ሳይሆን ራስን በመውደድ እና በሌሎች ለመወደድ ባለው ችሎታ ላይ የተመሠረተ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባርሴሎና ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋዜማ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በባርሴሎና ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋዜማ   (@Vatican Media)

“በየቀኑ ዓይኖቻችንን ወደ ላይ ማንሳት”

ኤልሳቤጥ በሰኔ ወር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ስፔን ሐዋርያዊ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ያጋጠማትን ተሞክሮም በማስታወስ፥ በጉብኝታቸው ወቅት ያከናወኗቸውን ተግባራት በቅርበት በመከታተል በሞንቲይክ በተደረገው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መሳተፏን እና በእነዚያ ቀናት ውስጥ በባርሴሎና ጎዳናዎች ላይ የተሰበሰቡ ምዕመናንን መቀላቀሏን አስታውሳለች።

ከዚያ ጉዞ ማዕከላዊ መልዕክቶች መካከል አንዱ፥ “ዓይኖችህን አንሳ” የሚል ሲሆን፥ ይህም የወንድሟ ዛቪየርን ውርስ መቀጠል እና ብርሃን ሊፈነጥቅላት የሚችለው “በየቀኑ ዓይኖቻችንን አጥብቀን ወደ ላይ በማንሳት ነው” ብላለች።

ከእይታዋ አንጻር “ይህ የሕይወት አመለካከት የሚደገፈው ጓደኛችን እና ፍቅራችን ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለው ግንኙነት ነው” ብላ፥ እንደ ልምዷ ጸሎት፣ ቅዱሳት ምስጢራ እና ቅዱስ ወንጌል የዚህ የዕለት ተዕለት ጉዞ አካል እንደሆኑ በመናገር፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአድማጮቻቸው፣ በጽሑፎቻቸው እና በቃላቶቻቸው አማካኝነት የሚያደርጉት አጃቢነትም እንዲሁ ነው” ስትል ገልጻለች።

በዛሬው ዓለም ተግዳሮቶች መካከል ኤልሳቤጥ የወንድሟ ምስክርነት ይህን ግብዣ በትክክል እንደሚያቀርብ በማመን ለሕይወት ትርጉም ሊሰጥ የሚችለውን ለማወቅ ከሕመም እና ከችግሮች አሻግራ መመልከት እንደሚገባ አስረድታለች።

ዛቪየር በ29 ዓመቱ አረፈ፤ እህቱ ታሪኩን ማካፈልዋን ለመቀጠል ወስናለች፤ አሁን ያ ምስክርነት ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዘንድ ደርሷል።

 

 

20 Aug 2026, 17:30