የ 2027ቱ የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት ለእጩዎች ክፍት መደረጉ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሕዝቦች መካከል ሰላማዊ አብሮ መኖርን ለማስፋፋት ለሚሰሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እውቅና የሚሰጠው የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት ስምንተኛ ዙር እጩዎችን የመቀበል ሂደት በይፋ የተጀመረ መሆኑ ተገልጿል።
የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት የተቋቋመው እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. በአቡ ዳቢ በአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል-ጣይብ እና በነፍስሄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መካከል የተደረገውን ታሪካዊ ስብሰባ ተከትሎ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህ ስብሰባ ወቅት ሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች “ለዓለም ሰላም እና አብሮ መኖር የሰው ልጅ ወንድማማችነት” በሚል ስያሜ በወጣው ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
በጎረጎሳዊያኑ ለ 2027 ዓ.ም. የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት የሚቀርቡ እጩዎች እስከ መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ በዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት ይፋዊ ድህረ-ገጽ በኩል ሊቀርቡ ይችላሉ ተብሏል።
የሼክ ዛይድ የስነ ምግባር ቅርስ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መስራች በሆኑት በሟቹ ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ስም የተሰየመው ይህ ሽልማት 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ሽልማትን እንደሚያካትት የተነገረ ሲሆን፥ ሽልማቱ የሼክ ዛይድን የስነ ምግባር ቅርስ፣ ሰብዓዊነት እና ለሌሎች ያላቸውን ክብር፣ እንዲሁም ሃይማኖት፣ ጾታ፣ ዘር ወይም ዜግነት ሳይለዩ ሰዎችን ለመርዳት የነበራቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያንፀባርቅ እና ተቋሙ በየዓመቱ ለውይይት እና ለአብሮነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና እንደሚሰጥ ተነግሯል።
ሰብዓዊ ጥረቶችን ማክበር
የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት ዋና ጸሐፊ ዳኛ መሐመድ አብደልሳላም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‘ለዚህ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ሽልማት ስምንተኛ ዙር የእጩዎች ጥሪ መከፈቱ፣ ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ እና የሰው ልጅ ወንድማማችነት እሴቶችን በዓለም ዙሪያ የሚያራምዱ ጉልህ ሰብአዊ ጥረቶችን የማጉላት እና የማክበር ተልዕኮውን ቀጣይነት ያሳያል’ ብለዋል።
ዳኛ አብደልሰላም አክለውም ሽልማቱ "ታሪካዊውን የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሰነድ መርሆዎች ወደ ተግባራዊ ፕሮግራሞች በመቀየር በዓለም ዙሪያ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ዘላቂ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ተነሳሽነቶች መደገፉን ይቀጥላል ያሉ ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅ ወንድማማችነት እሴቶችን ለማራመድ ትርጉም ያለው አስተዋጽዖ ለሚያበረክቱ ግለሰቦች እና አካላት በዚህ ዓመት አዳዲስ እጩዎችን ለመቀበል በጉጉት እንጠብቃለን ብለዋል።
እ.አ.አ. ከ 2019 ዓ.ም. ወዲህ ያሉ ሃያ ተሸላሚዎች
የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት ሰባተኛ ዙር አሸናፊዎች ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም. አቡ ዳቢ በሚገኘው ለመስራቹ መታሰቢያነት በተገነባው ህንፃ ውስጥ በተደረገ ሥነ-ሥርዓት ላይ እውቅና እንደተሰጣቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ በአዘርባጃን እና በአርሜኒያ መካከል ለተደረገው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት፣ 'ታዎን' (Taawon) ለተባለው የፍልስጤሙ የሰብዓዊ ድርጅት እንዲሁም ለአፍጋኒስታኒቷ የሴቶች መብት ተሟጋች ዛርቃ ያፍታሊ የተሰጠው የ 2026 የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት፤ ተቋማቱ እና ግለሰቦቹ ለሰላማዊ አብሮ መኖር፣ ለሰብዓዊ እርዳታ እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ ትምህርት በማስፋፋት ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽዖ እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ተነግሯል።
የዛይድ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ሽልማት እ.አ.አ. ከ 2019 ዓ.ም. ጀምሮ በጤና፣ በትምህርት፣ በዘላቂ ልማት፣ በስደተኞች ድጋፍ፣ በማህበረሰብ ልማት፣ በምግብ እርዳታ እንዲሁም በወጣቶችና በሴቶች አቅም ግንባታ ዘርፎች አስተዋጽኦ ላበረከቱ ከ20 ሀገራት ለተውጣጡ 20 ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና መስጠቱ ተገልጿል።