ፈልግ

በደቡብ ሊባኖስ በምትገኘው ዛውታር አል-ጋርቢያ መንደር በተካሄደው የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት ምክንያት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ የደረሰ ጉዳት በደቡብ ሊባኖስ በምትገኘው ዛውታር አል-ጋርቢያ መንደር በተካሄደው የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት ምክንያት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ የደረሰ ጉዳት   (AFP or licensors)

በሮም የተካሄደው የሊባኖስ እና የእስራኤል የሰላም ውይይት ‘በጎ እድገት’ ማሳየቱ ተነገረ

በጣሊያን መዲና ሮም የተካሄደው የእስራኤል እና የሊባኖስ 7ኛው ዙር የሰላም ውይይት በድንበር እና በእስረኞች ልውውጥ ጉዳዮች ላይ “በጎ እድገት” ማሳየቱን የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ገልጸዋል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአሜሪካ አገናኝነት የተመቻቸው ይህ የሶስት ቀናት የቴክኒክ ድርድር በዋናነት የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ ማድረግና የእስራኤል ጦር ከደቡብ ሊባኖስ የሚወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ ያተኮረ እንደሆነ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ተናግረዋል።

ውይይቱ በደቡብ ሊባኖስ ያሉ የሙከራ ቀጠናዎችን ማስፋፋት፣ የድንበር ውዝግቦችን መፍታት፣ የእስረኞች ልውውጥ እና ዘላቂ የሰላምና የደህንነት ስምምነት ላይ መድረስ የሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተጠቁሟል።

በታቀደው ማዕቀፍ መሠረትም የእስራኤል ጦር ከደቡብ ሊባኖስ በቀስታ እንዲወጣ እና የሊባኖስ መንግሥት ጦር በአካባቢው እንዲሰፍር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ውይይቱ እንደሚደረግ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ የሚካሄደው ውይይት በእስራኤልና በሊባኖስ መካከል ያለውን የደህንነት ውጥረት ለማርገብ የተደረገ አዲስ ሙከራ እንደሆነ ተገልጿል።

በድንበር እና በእስረኞች ጉዳይ ላይ "አዎንታዊ እድገት" መመዝገቡን የገለጹት ፕረዚዳንቱ፥ ተጨባጭ እርምጃዎችም ይወሰዳሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት ከሆነ፣ ውይይቱ በተኩስ ማቆም እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸው፤ በቅርቡ ተግባራዊ እርምጃዎች ይታያሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን፥ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ውይይቱን "ፍሬያማ" ሲል ገልጾታል።

ይሁን እንጂ በደቡብ ሊባኖስ የእስራኤል ጥቃት አሁንም የቀጠለ ሲሆን፤ በሜይስ አል-ጀበል፣ ቢንት ጅቤል እና አል-ማንሱሪ በተፈጸሙ የመድፍና የድሮን ጥቃቶች በውሃ መስመር ጥገና ላይ የነበሩ ሰራተኞች እንዲሁም አንድ የሊባኖስ ወታደር መቁሰላቸው ከአከባቢ የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ባለፈው ወር፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተመደቡት ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች፣ ሲቪሎች "አውዳሚ እና ከመጠን ያለፈ ጉዳት" እየደረሰባቸው መሆኑን አስጠንቅቀው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በርካታ ቤቶች መውደማቸው፣ ከተሞች ከተደራሽነት መነጠላቸው፣ እንዲሁም በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ በርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ መድረስ እንዳልተቻለ ተገልጿል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው በግጭቱ ወቅት 392 ሴቶች እና 253 ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 4,333 ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።

10 Aug 2026, 15:33