ፈልግ

በምስራቅ ኑሳ ቴንጋራ በሚገኘው የማውሜሬ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ፣ ህጻናት ከከባድ የስነ-ልቦና ጉዳት የመዳን መርሃ ግብር ላይ ሲሳተፉ በምስራቅ ኑሳ ቴንጋራ በሚገኘው የማውሜሬ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ፣ ህጻናት ከከባድ የስነ-ልቦና ጉዳት የመዳን መርሃ ግብር ላይ ሲሳተፉ   (AFP or licensors)

በኢንዶኔዥያ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ከ8,000 በላይ የሚሆኑ ህጻናት ትምህርት እንደተቋረጠባቸው ተነገረ

ቅዳሜ ነሐሴ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በሬክተር ስኬል 7.7 ማግኒቲዩድ የሆነ እጅግ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በኢንዶኔዥያ፣ የፍሎሬስ ደሴት ላይ መከሰቱን ተከትሎ 'ሴቭ ዘ ችልድረን' የተሰኘው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት እንዳስታወቀው፣ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል ህጻናት በጣም ተጋላጭ ቡድን መሆናቸውን በመጥቀስ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ እስካሁን በተረጋገጠ መረጃ መሰረት የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 68 መድረሱን፣ 213 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው፤ እንዲሁም ወደ 13,000 የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል መገደዳቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በፍሎሬስ ደሴት በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ቢያንስ 68 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፥ ከ213 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው፣ ወደ 13,000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል እንደተገደዱ የተገለጸ ሲሆን፥ የመሬት መንሸራተት በተከሰተባቸው እና ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነታቸው በተቋረጠባቸው አካባቢዎች የነፍስ አድን ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

የኢንዶኔዥያ የጂኦፊዚክስ ኤጀንሲ እንደገለጸው፣ ነሃሴ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ማለዳ ከሱማትራ የባህር ዳርቻ ባሻገር፣ በ29 ኪሎ ሜትር (18 ማይል) ጥልቀት ላይ ተጨማሪ 6.1 ማግኒትዩድ ያስመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ይፋ አድርጓል።

የህጻናት ሁኔታ ስጋት ፈጥሯል
ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ በህጻናት የደህንነት ሁኔታን በተመለከተ ልዩ ስጋት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፥ እንደ ሴቭ ዘ ችልድረን ሪፖርት መሰረት፣ በምስራቅ ኑሳ ተንጋራ ግዛት ውስጥ ከ8,000 በላይ ህጻናትና ታዳጊዎች ትምህርት ቤት መሄድ እንዳልቻሉ እና ለደህንነታቸው የሚያሰጋ አደጋ እንደሚገጥማቸው የተጠቆመ ሲሆን፥ ከ900 በላይ መኖሪያ ቤቶች በመሬት መንቀጥቀጡ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ከዚህም በተጨማሪ ቢያንስ 87 ትምህርት ቤቶች እና 18 የጤና ማዕከላት ከተጎዱት መሠረተ ልማቶች መካከል እንደሚገኙ ይፋ ተደርጓል።

ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ቀድሞውኑ ከኤል ኒኖ ክስተት ጋር በተያያዘ ከድርቅ ጋር እተጋፈጡ የሚገኙትን እንዲሁም ከሌዎቶቢ ተራራ ጋር በተያያዘ ደግሞ የእሳተ ገሞራ አደጋ ባጋጠማቸው ማህበረሰቦች ላይም ተጨማሪ ተፅዕኖ ማሳደሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በልጆች ጤና፣ ትምህርት እና የስነ-ልቦና ደህንነት ላይ ያለውን ተጽእኖ አባብሶታል ተብሏል።

"ህጻናት ልጆች በጣም ለአደጋ ከተጋለጡት መካከል ናቸው"
ሴቭ ዘ ችልድረን የተሰኘው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ኤጀንሲ የኢንዶኔዥያ ሃገር በቀል ድርጅት ከሆነው ‘ሲአይኤስ - ቲሞር’ ከተሰኘው ተቋም ጋር በመሆን የእርዳታ ጥረቶችን ለመጀመር የአከባቢው ቤተሰቦች ቀዳሚ ፍላጎቶችን እየገመገመ የሚገኝ ሲሆን፥ ድርጅቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች መካከል የትምህርት ተደራሽነትን ወደነበረበት መመለስ እና የቤተሰብን ኑሮ መደገፍ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

“ህጻናት ልጆች ለአደጋ ከተጋለጡት መካከል ናቸው” ያሉት በሴቭ ዘ ችልድረን ኢንዶኔዥያ የሰብአዊ ምላሽ እና የአቅም ግንባታ ክፍል ዳይሬክተር ፋድሊ ኡስማን፥ አፋጣኝ ምላሹ፤ የንብረት መጥፋትን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን፣ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን፣ ያለዕድሜ ጋብቻን እና ሌሎች ህጻናትን ከአደጋ የመጠበቅ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከሚወሰዱ የረጅም ጊዜ እርምጃዎች ጋር አብሮ መሄድ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።

ካሪታስ ሌሎች ተቋማትን እያስተባበረ ይገኛል
ካሪታስ ኢንዶኔዥያ በመሬት መንቀጥቀጡ በተጎዱ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰብዓዊ ድጋፍ ትስስሮችን እያስተባበረ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ በተለይም የሩቴንግ፣ ላቡዋን ባጆ፣ ኩፓንግ፣ ማውሜር እና ኢንዴ ሃገረ ስብከቶችን በማስተባበር የተለያዩ የድጋፍ እንቅስቃሴዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

ከዚህም ባሻገር የተለያዩ በጎ ፈቃደኞች እና ከሀገረ ስብከቱ የተወጣጡ ቡድኖች ህዝቡን በመርዳት እንዲሁም ሰዎችን ከስጋት ቀጠና የማስወጣት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፥ ቁምስናዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ አስቸኳይ ፍላጎቶች በተመለከተ መረጃ እየሰበሰቡ እንደሆነ፥ ከእነዚህም በጣም አስቸኳይ ፍላጎቶች መካከል የመጠጥ ውሃ፣ ምግብ፣ መጠለያ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የጤና እንክብካቤ እንዲሁም በተለይም ህጻናትን፣ አረጋውያንን፣ ነፍሰ ጡር ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ ድጋፍ መሆናቸውን ካሪታስ ኢንዶኔዥያ ለይቶ አውጥቷል።

ይህ የአደጋ ጊዜ ምላሽ “አንድ ቤተክርስቲያን፣ አንድ ምላሽ” በሚለው የካሪታስ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የካሪታስ ኢንዶኔዥያ ዳይሬክተር አባ ፍሬዲ ራንቴ ታሩክ ይሄንን አስመልክተው እንደገለጹት፥ በዚህ መርህ አማካኝነት ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች፣ በጎ ፈቃደኞች እና የቤተክርስቲያኗ የተለያዩ መዋቅሮች "ለሰብዓዊ ሁኔታው ፈጣን እና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት" እንዲሁም እርዳታው ለተጎዱት ማህበረሰቦች መድረሱን ለማረጋገጥ በትጋት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

20 Aug 2026, 15:23