የሐምሌ ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሙቀት መጠን የተመዘገበበት ወር መሆኑ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. የ 2026 ዓ.ም. የበጋ ወቅት በተከታታይ የከባድ ሙቀት ማዕበሎች የታጀበ እንደሆነ ከአከባቢው የሚወጡ ዘገባዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ እንደ የአሜሪካ ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር ዘገባ መሰረት ያሳለፍነው የሐምሌ ወር እ.አ.አ. ከ 1850 ዓ.ም. ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበ እጅግ ሞቃታማ ወቅት እንደነበር አመላክቶ፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ ህዝቦች እና ማህበረሰቦች የዚህ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ጭማሪ ያደረሰው ውጤት ሰለባዎች እንደሆኑም ጭምር አመላክቷል።
በጃፓን፣ ሀገሪቱ እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ ረጅሙ የሆነውን የ40 ዲግሪ ሴልሺየስ ወይም 104 ዲግሪ ፋራናይት የሙቀት መጠን ተከታታይ ቀናት እያሳለፈች ባለችበት ወቅት፣ አሁንም ድረስ የሙቀት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ የተነገረ ሲሆን፥ በሰሜን አፍሪካም በተመሳሳይ መልኩ የሙቀት መጠኑ ወደ 49 ዲግሪ ሴልሺየስ ወይም 120 ዲግሪ ፋራናይት እየተጠጋ በመምጣቱ ህዝቡ ከፍተኛ የሙቀት መጠንን እየተጋፈጠ እንደሚገኝ፣ ከዚህም በተጨማሪ ሆስፒታሎች እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስርዓቶችም የመስተጓጎል ስጋት እንደተጋረጠባቸው ተነግሯል።
አውሮፓ በበኩሏ አስደንጋጭ ውጤቶችን ያስከተለውን በታሪኳ ሁለተኛውን እጅግ ሞቃታማ የሐምሌ ወር ያሳለፈች ሲሆን፥ በአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ መሰረት በፈረንሳይ፣ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸው ቀናት ብዛት ምክንያት ከ7,300 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ተዘግቧል።
የምዕራብ አውሮፓ ሃገራትም ከፍተኛ ድርቅ እና ሰደድ እሳት ያስከተሉ በሰኔ እና በሐምሌ ወራት በተደጋጋሚ የተከሰቱ ከፍተኛ የሙቀት ማዕበሎች እስካሁን ካጋጠሙት ሁሉ እጅግ ሞቃታማ የሆነ የበጋ ወቅት መግቢያን ያስመዘገቡ ሲሆን፥ ቤልጂየም፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ እና ጣሊያን በእነዚህ ወራት ከፍተኛ የሰደድ እሳት ከደረሰባቸው ሀገራት መካከል እንደነበሩ ተገልጿል።
አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ላይ የሚነሱ የሰደድ እሳቶች፣ ምንም እንኳን ፕላኔቷን ከሙቀት መከላከል የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም፣ በአውሮፓ ውስጥ ተጨማሪ 39 በመቶ የሚሆነውን መሬት እንደሚያወድሙ ያለውን ግምት ያስቀመጠ ሲሆን፥ ይህ አሃዝ ሊለወጥ የሚችለው እሳቱን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር ከባድ እርምጃዎች ከተወሰደ ብቻ እንደሆነ አመላክቷል።
ከአነስተኛ እሳቶች ወደ አደገኛና ግዙፍ የሰደድ እሳት ነበልባሎች
የአውሮፓ የሰደድ እሳት መረጃ አገልግሎት ባወጣው መረጃ መሰረት፣ እ.አ.አ. በ2026 ዓ.ም. በአውሮፓ የተከሰተው የሰደድ እሳት አደጋ ወቅት፣ ከ 2025 እና ከ 2022 ዓ.ም. በመቀጠል በታሪክ ሦስተኛው አስከፊ ወቅት እየሆነ መምጣቱ የተመላከተ ሲሆን፥ የካርቦን ብክለት የሙቀት መጠንን በመጨመሩ ምክንያት፥ ሞቃታማ፣ ደረቅ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በመባባሱ፥ ትናንሽ እሳቶች ወደ አደገኛ እና ግዙፍ የእሳት ቃጠሎዎች እንዲለወጡ ማድረጉን መረጃው አመላክቷል።
ተመራማሪዎች እንደገለጹት፥ በጣም በከፋ ሁኔታ፣ የዓለም ሙቀት መጠን ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ከነበረው ደረጃ በ3.6 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመው፥ ይህ ሁኔታ ከተከሰተ፣ በሰደድ እሳቱ የሚቃጠለው ቦታ መጠን ወደ ሦስት እጥፍ ገደማ እንደሚጨምር ገልጸዋል።
የእሳት አደጋ አስተዳደርን ማሻሻል የሙቀት መጨመርን ከ 70 በመቶ በላይ እንዳይጨምር ለመገደብ ቢረዳም፣ ዳሩ ግን እነዚህ ማሻሻያዎች ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንደማያስወግዱት ጥናቶች ያሳያሉ ተብሏል።
በፖትስዳም የአየር ንብረት ተጽዕኖ ምርምር ተቋም ውስጥ የስነ-ምህዳር ተመራማሪ እና የጥናቱ መሪ የሆኑት ደራሲ ማይክ ቢሊንግ ይሄንን አሰልክተው እንደተናገሩት፥ ‘ከፍተኛ የልቀት መጠን በሚያስከትል አካሄድ ብንቀጥል... በሰደድ እሳት የሚጎዳው ቦታ ስፋት አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል አመላክተው፥ የእሳት አደጋ አስተዳደር የአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ እርምጃዎችን ሊተካ አይችልም ብለዋል።
ከሰል፣ ጋዝ እና ነዳጅን መተው
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ሲሞን ስቲል በበኩላቸው “የአየር ንብረት አደጋ ማስጠንቀቂያዎች ከሁሉም አቅጣጫ በኃይል እየተሰማ ነው” በማለት ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ የሰው ልጅ ለድንጋይ ከሰል፣ ለነዳጅ እና ለጋዝ አጠቃቀም ያለው ሱሰኝነት የሚያስከትለው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ እና “እንደ ቅዠት ሊቆጠሩ የሚችሉ አስከፊ አደጋዎች” እየገጠሟት መሆኑን አስረድተዋል።
የለውጥ ጥሪ የተደረገው ከዓመታት በፊት ቢሆንም፥ ነገር ግን ወደ ተጨባጭ ተግባር የሚደረገው ሽግግር ማለትም ከቅሪተ አካል ነዳጅ አጠቃቀም ወደ ታዳሽ ኃይል እንዲሁም በደን እና በውቅያኖሶች ጥበቃ ላይ ትኩረት ማድረግ በበቂ ፍጥነት እየተከናወነ አለመሆኑም ጭምር ተነግሯል።
‘ሰደድ እሳት፣ ድርቅ፣ ከፍተኛ ሙቀት እና የመሳሰሉት ከአሁን በኋላ ንድፈ ሐሳቦች ብቻ ሳይሆኑ፤ ይልቁንም በፍጥነት እየሞቀች ባለው ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ተጨባጭ የሕይወት እውነታ ሆነዋል’ ያሉት ዋና ጸሃፊው፥ ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው ‘ከሰልን፣ ነዳጅንና ጋዝን በፍጥነት በመተው፥ ታዳሽ ኃይልን በስፋት መጠቀም እና ጉዳቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየደረሰባቸው ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎችን መታደግ እንደሆነ አስረድተዋል።ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 2015 ዓ.ም. በጻፉት ላውዳቶ ሲ በተሰኘው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ላይ እንደገለጹት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታን ለመፍታት እና ለማስተካከል አሁንም ጊዜ እንዳለ ጠቁመው፥ “የሰው ልጅ የጋራ መኖሪያችንን በመገንባት ረገድ አሁንም ቢሆን በጋራ የመስራት አቅም አለው” ያሉ ሲሆን፥ በእውነት ብዙ ነገር ሊደረግ ይችላል! በማለት ተስፋ እንዳለ ጠቁመዋል።
ይህ ሰነድ የታተመበትን 10ኛ ዓመት ለማክበር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በካስቴል ጋንዶልፎ በተካሄደው “ተስፋን ማጎልበት” በተሰኘው ጉባኤ ላይ ለተሳታፊዎች ንግግር ባደረጉበት ወቅት፥ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማምጣት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ እንዲሰራ ጥሪ በማቅረብ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሃሳብ በድጋሚ አንጸባርቀዋል።
“በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና ተሟጋች ቡድኖች አማካኝነት፣ መንግስታት የበለጠ ጥብቅ ደንቦችን፣ ሂደቶችን እና ቁጥጥሮችን እንዲያዘጋጁ እና እንዲተገብሩ ጫና ማድረግ እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ የሚቻለው ዜጎች በብሔራዊ፣ በክልል እና በአካባቢ ደረጃ በፖለቲካዊ ውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ ንቁ ሚና መጫወት ሲችሉ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመጨረሻም አሁን፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ በላውዳቶ ሲ ውስጥ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ተገቢ መሆናቸው እና አስቸኳይ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ ተመላክቷል።