ከዩክሬን እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ግጭቱ እየተባባሰ መምጣቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዚህ ዓመት በዩክሬን፣ ሊባኖስ፣ ጋዛ እና ኢራን የተነሱት ግጭቶች የአውሮፓዊያኑ የበጋ ወቅት ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የመቀነስ ምልክት እንዳላሳየ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ሩሲያ እና ዩክሬን እርስ በርስ የሚሰነዛዘሩት ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ ይሄንን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ሞስኮ በሰሜን ኮሪያ የተመረቱ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን በመጠቀም በዛፖርዢያ ግዛት ላይ ባደረገችው ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን፣ 19 ሰዎች ደግሞ መቁሰላችውን ተከትሎ ሩሲያን መክሰሳቸው ተነገሯል።
“ሞስኮ በሰሜን ኮሪያ የተመረቱ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን በመጠቀም በዩክሬን ከተሞችና ሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እያደረሰች ትገኛለች” በማለት የሚከሱት ዘለንስኪ፥ ሩሲያ እነዚህን ሚሳይሎች የምትጠቀመው የገጠማትን የጦር መሣሪያ እጥረት ለመሙላት እና የዩክሬንን የፀረ-አውሮፕላን መከላከያ ዘዴዎችን ለማዳከም እንደሆነ ገልጸዋል።
በቅርቡ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ዛፖሪዢያ እና ዋና ከተማዋ ኪየቭን ጨምሮ በርካታ ከተሞች በሰሜን ኮሪያ በተመረቱ ሚሳኤሎች መደብደባቸው የተነገረ ሲሆን፥ ሰሜን ኮሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአርቲለሪ ጥይቶችን ለሩሲያ ማቅረቧ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
የዩክሬን የራዳር ሥርዓቶች እንደመዘገቡት ጥቃቱ በሰሜን ኮሪያ ሰራሹ KN-23 ወይም KN-24 ሚሳይል አማካኝነት ከሩሲያ ብሪያንስክ ክልል የተተኮሰ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፥ ይህ ጥቃት ሩሲያ ከፒዮንግያንግ አዲስ የጦር መሣሪያ አቅርቦት ማግኘቷንና ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ትብብራቸውን ማጠናከራቸውን ያሳያል ተብሏል።
ይሄንን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ ሞስኮ ከፒዮንግያንግ ተጨማሪ ሚሳይሎችንና የጦር መሣሪያዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እያገኘች መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በዋና ከተማዋ ኪየቭ በተሰነዘረ የሚሳይል ጥቃት የአንድ ሕፃናት ሆስፒታል ግቢ የተመታ ሲሆን፥ በሆስፒታሉ ህንፃ ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስም ነገር ግን ሕፃናትና ሠራተኞች መጠለያ ውስጥ ስለነበሩ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተገልጿል።
በምዕራብ ሩሲያ በምትገኘው ቮሮኔዝ ከተማ ደግሞ ትልቁ የኦንላይን መሸጫ ድርጅት የሆነው የዋይልድ-ቤሪ መጋዘኖች በዩክሬን መመታታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ የሩሲያ አማዞን በመባል የሚታወቀው ይህ ኩባንያ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በተደጋጋሚ ዒላማ መደረጉ ተነግሯል።
ጥቃቶቹ የተከሰቱት፣ ከዩክሬን ድንበር ከ1,100 ኪ.ሜ. በላይ ርቀት ላይ በምትገኘው የታታርስታን ሪፐብሊክ በዩክሬን ድሮን በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሕፃንን ጨምሮ ቢያንስ 13 ሰዎች ከተገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ ሲሆን፥ ዜሌንስኪ ሰኞ ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ "ለመጀመሪያ ጊዜ" ሩሲያ "ከሰሜን ኮሪያ ድጋፍ ውጭ ጦርነት ልታውጅ እንደማትችል” ጠቁመው፥ "የሰሜን ኮሪያ ጥቃቶች በዩክሬን፣ እንዲሁም በአውሮፓም በጨመሩ ቁጥር ሚሳዔሎቻቸውና ወታደሮቻቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ ድክመቶቻቸውንና ክፍተቶቻቸውን የበለጠ ይሸፍናሉ" በማለት፣ ይህ ደግሞ ለተቀረው ዓለም አደጋ እንደሚፈጥር አክለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ቀጣይ ወረራ ሲቪሎችን ለተደጋጋሚ ገዳይ ጥቃቶች እንዳጋለጣቸው የገለጸ ሲሆን፥ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች እና መሠረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረግ ተጠናክሮ መቀጠሉን ይፋ አድርጓል።
በዩክሬን የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ አስተባባሪ የሆኑት ቶቢ ፍሪከር ድርጅታቸው በሁሉም አካባቢዎች ከሚገኙ አጋሮች ጋር በመተባበር ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ ወዲያውኑ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፥ “ቤቶቻቸው የወደሙ ወይም የተጎዱ ወይም በጦርነቱ ቀጠና የሚገኙ ህፃናት እና ቤተሰቦቻቸው የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል።
መካከለኛው ምስራቅ
ይህ በእንዲህ እያለ የእስራኤል ጦር ከራማላህ በስተሰሜን ምስራቅ የምትገኘውን እና በዌስት ባንክ የመጨረሻዋ ሙሉ በሙሉ የክርስቲያን መንደር የሆነችውን ታይቤህ መንደርን "ዝግ የተደረገ ወታደራዊ ቀጠና" በማለት ማወጁ የሚታወስ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ሰሞኑን 13 ፍልስጤማውያንን ማሰሩ ተነግሯል።
በሌላ ዜና በደቡባዊ ሊባኖስ ናባቲህ አካባቢ የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን በሄዝቦላህ ስር በሚንቀሳቀሰው የእስላማዊ ጤና ድርጅት የአምቡላንስ እና የህክምና ቡድኖች ላይ ድብደባ የፈጸመ ሲሆን፥ ይህ ጥቃት የተፈጸመው የህክምና ባለሙያዎቹ ቀደም ሲል በሌላ ጥቃት የቆሰለ ሰውን በድንገተኛ አምቡላንስ እያነሱ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ተነግሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር ላይ ጉዳዮች ኤጀንሲ በቅርቡ ያወጣቸው ዋና ዋና ማስጠንቀቂያዎች እና መግለጫዎች በዋናነት በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በኦማን ባህረ ሰላጤ አካባቢ በተከሰቱት የጸጥታ ስጋቶች እና የመርከቦች ጥቃት ላይ ያተኮሩ ሲሆን፥ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሁኑ ጊዜ ለንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛ መሆኑን አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተከሰቱት ጥቃቶች ሳቢያ የሲቪል መርከበኞች ህይወት እያለፈ እና ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ የውጥረት እሽቅድምድም በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶሪያ ፍርድ ቤት ከስልጣን የተወገዱትን የቀድሞውን ያሃገሪቷ ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድን በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው በሚል በሌሉበት የሞት ፍርድ የፈረደባቸው ሲሆን፥ የሶሪያ አራተኛው የወንጀል ችሎት ውሳኔውን ያስተላለፈው ነሐሴ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት እንደሆነ እና የተከሰሱባቸው ወንጀሎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ በአገሪቱ ለ14 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት፤ ታስቦበት በተፈጸመ የሰዎችና የሕፃናት ግድያ፣ ማሰቃየት፣ ሕገ-ወጥ እስራት እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ከባድ የጦር ወንጀሎች መሆኑ ተነግሯል።
ነገር ግን የሶሪያ አዲሱ መንግስት አል-አሳድን ከሩሲያ ወደ ሶሪያ እንዲመለሱ እና ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ መቻሉ ወይም አለመቻሉ እስካሁን ግልጽ አይደለም ተብሏል።