በኢንዶኔዥያ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 38 ሰዎች መሞታቸው እና ሊካሄድ የነበረ የካቶሊክ ፌስቲቫል መሰረዙ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በኢንዶኔዥያ ፍሎሬስ ደሴት አቅራቢያ ቅዳሜ ነሐሴ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በሬክተር ስኬል 7.7 ማግኒቲዩድ የሆነ እጅግ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተከትሎ ቢያንስ 38 ሰዎች መሞታቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።
የሀገሪቱ የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፣ በማውሜሬ ወደብ አካባቢ የደረሰው ጠንካራ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከሰው ህይወት በተጨማሪ በአካባቢው በሚገኙ ሕንፃዎች እና በወደቡ ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን አስታውቋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው የፍልሰታ ማሪያም በዓል ላይ መሆኑ
ኢንዶኔዥያ የሜትሮሎጂ፣ የአየር ንብረት እና የጂኦፊዚክስ ኤጀንሲ በበኩሉ የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ቅዳሜ ማለዳ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 11፡58 ላይ እንደሆነ እና የንዝረቱ መነሻ የምስራቅ ኑሳ ተንጋራ ግዛት በሆነችው ኢንዴ ከተማ 68 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እና 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ውስጥ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ ከዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ በግማሽ ሰዓት ጊዜ ውስጥ 5.9፣ 5.6 እና 6.1 ማግኒቲዩድ ያላቸው ሶስት ተከታታይ አነስተኛ ንዝረቶች መከሰታቸውን ገልጿል።
አደጋውን ተከትሎ የኢንዶኔዥያ የሚቲዎሮሎጂ፣ ክላይማቶሎጂ እና ጂኦፊዚክስ ኤጀንሲ የሱናሚ (የባህር ላይ ማዕበል) ማስጠንቀቂያ ያወጣ ሲሆን፥ ነዋሪዎች ከባህር ዳርቻዎች እና ወንዞች አካባቢ ርቀው ወደ ከፍተኛ ቦታዎች እንዲሸሹ አሳስቧል።
የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት አብዱል ሙሃሪ ህብረተሰቡ ከባህር ዳርቻ ቢያንስ ሁለት ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ እንዲገባ ወይም ከ10 ሜትር በላይ ከፍታ ወዳላቸው ተራራማ ቦታዎች በመሄድ ራሱን እንዲያድን ጥሪ አቅርበዋል። በአንጻሩ የአውስትራሊያ የሱናሚ ማስጠንቀቂያ ማዕከል አደጋው በአውስትራሊያ ላይ ምንም አይነት ስጋት እንደማይፈጥር አረጋግጧል።
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው በፍሎሬስ የሚገኙ ካቶሊካዊያን የቅድስት ድንግል ማርያምን የፍልሰታ በዓል ለማክበር እየተዘጋጁ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በሲካ ከተማ በሚገኘው የሪታፒሬት ንዑስ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት የሚገኙ የክህነት ተማሪዎች፣ ካህናት እና ገዳማዊያት ሕንፃው በአደጋው ምክንያት ሲናወጥ እና አንዳንድ የሕንፃው ክፍሎች ሲፈርሱ መሸሻቸው እና ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንድ ካህን ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ዘለው እግራቸው እንደተሰበረ ተገልጿል።
በሌዳሌሮ ከቤት ውጭ የሚከበሩ የመጨረሻ ቃለ መሃላዎች
የመሬት መንቀጥቀጡ በሌዳሌሮ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ንዑስ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ውስጥ የ ‘ድቫይን ዎርድ’ ማኅበር አባላት የሆኑ 27 የክህነት ተማሪዎች በፍልሰታ ማሪያም በዓል ላይ ሊያደርጉት የነበረውን የመጨረሻ ቃለ-መሐላ መርሃ ግብር በሚያሳዝን ሁኔታ ያስቀረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ከቀደሙት ዓመታት በተለየ መልኩ፣ ክብረ በዓሉ በጸሎት ቤት ውስጥ ሊከናወን እንዳልቻለ እና ጸሎት ቤቱ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የጣሪያው ክፍል ከወደቀ በኋላ ጥቅም ላይ እንዳይውል መደረጉ ተነግሯል።
በዚህም ምክንያት፣ የቅዱስ ቁርባን ስግደት ከአዳራሹ ፊት ለፊት በሚገኘው፣ ጊዜያዊ ድንኳን ውስጥ እንዲደረግ መወሰኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በድንኳኑ ውስጥ መደረጉ ተጨማሪ የመሬት መንቀጥቀጥ ምልክት ቢኖር እንኳን ማህበረሰቡ ንቁ ሆኖ እንዲቆይ የሚያስችል መሆኑ እንዲሁም ጥዋት 2፡30 ላይ ሊደረግ የታቀደው መስዋዕተ ቅዳሴ ሁኔታውን ለመገምገም እና አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ በሚል ወደ 3፡30 መሸጋገሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ምንም እንኳን የቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓቱ ከመከናወኑ በፊትም ሆነ በኋላ ተጨማሪ የመሬት መንቀጥቀጦች ሊኖሩ እንደሚችል ሪፖርት ቢደረግም፣ በበዓሉ ወቅት ምንም ዓይነት ተከታይ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልተከሰተ ተዘግቧል።
ምንም እንኳን መስተጓጎልና እርግጠኛ ያለመሆን ሁኔታ ቢኖርም፣ ለፍሎሬስ ህዝብ አስቸጋሪ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የሚስዮናዊነት ጥሪያቸውን ለእግዚአብሔር አደራ በመስጠት 27ቱ የክህነት ተማሪዎች የመጨረሻ ቃለ-መሐላቸውን መፈጸማቸው የተነገረ ሲሆን፥ በደሴቲቱ ላይ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የመሬት መንቀጥቀጡን አደጋን እየተጋፈጠች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ክብረ በዓሉ ጠንካራ የእምነት እና የጽናት ምልክት መሆኑ ተነግሯል።
ማህበረሰቡ በመርሃ ግብሩ ወቅት ለፍሎሬስ ሕዝብ፣ በተለይም ለአደጋው ሰለባዎች፣ የሚወዷቸውን ሰዎች ላጡ እና በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ላጡ ሰዎች መጸለዩ ተገልጿል።
ሀገረ ስብከቱ የጎሎ ኮኢ ፌስቲቫልን መሰረዙ
ከዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ባሉት ሰዓታት ውስጥ የላቡዋን ባጆ ሀገረ ስብከት የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ፣ የኮንሰርት እና የባህል ትርኢቶችን የሚያካትተውን የጎረጎሳዊያኑን የ 2026 ዓ.ም. የጎሎ ኮኢ ፌስቲቫል ቀሪ ዝግጅቶች መሰረዛቸውን ያስታወቀ ሲሆን፥ የሃገረ ስብከቱ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ማክሲመስ ሬጉስ ውሳኔው የተወሰደው ለአደጋው ምላሽ እና ለሕዝብ ደህንነት ስጋቶች ተብሎ እንደሆነ ገልጸው፥ “ከአደጋው ሰለባዎች ጋር በአንድነት ለመቆም እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያጋጠሟቸው ካሉት ጋር ለመሆን በዓሉን ላለመቀጠል ወስነናል” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጳጳሱ ካቶሊካዊያን እንዲረጋጉ፣ ይፋዊ መመሪያዎችን እንዲከተሉ እና የበዓሉን መንፈስ ወደ ተጨባጭ የርህራሄ ተግባራት እንዲቀይሩ አሳስበው፥ “በዓሉ ሊቆም ይችላል፥ ነገር ግን የወንድማማችነት፣ የአብሮነት እና የእንክብካቤ መንፈስ መቀጠል አለበት” ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓሉን ወደ አብሮነት ለውጣለች
አምስተኛ ዓመቱን የያዘው የጎሎ ኮኢ ፌስቲቫል ከምሥራቃዊ ኢንዶኔዥያ ጉልህ ካቶሊካዊ እና ባህላዊ በዓላት ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ “አብሮ መጓዝ፣ ምድርን መፈወስ” የሚለው የዘንድሮው መሪ ቃል ሊደረጉ የነበሩ የታቀዱት በዓላት በአደጋው ምክንያት ለጸሎት እና ለአንድነት ስሜት ቦታቸውን በመልቀቃቸው ይበልጥ ጥልቅ የሆነ ትርጉም ማግኘቱ ተገልጿል።
አሁን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እ.አ.አ. በ 1992 ዓ.ም. በፍሎሬስ ደሴት የተከሰተውን እና ወደ 2500 የሚጠጉ ሰዎች የሞቱበትን አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሱናሚ የሚያስታውስ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የነፍስ አድን እና የሰብአዊ እርዳታ ሥራዎች በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት፣ በፍሎሬስ ዙሪያ የሚገኙ መላው የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች ለደህንነት፣ ለጸሎት እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አጋርነትን ለማሳየት ቅድሚያ እንዲሰጡ ተበረታተዋል።
የአከባቢው ባለስልጣናት ነዋሪዎች ንቁ ሆነው እንዲቆዩ፣ ከፈራረሱ ሕንፃዎች ሥር እንዲርቁ እና ተጨማሪ የመሬት መንቀጥቀጦች የመከሰት እድል ስላለ ኦፊሴላዊ መረጃዎችን እንዲከተሉ ያሳሰቡ ሲሆን፥ በፍሎሬስ የሚገኙ የካቶሊክ ማህበረሰብ የእመቤታችን የፍልሰታ በዓል በዚህ ዓመት መጀመሪያ ታቅዶ በነበረው መልኩ ሳይሆን ያከበሩት፥ ነገር ግን ወደ እምነት፣ ወደ ጽናት እና መከራ ከሚደርስባቸው ሰዎች ጋር ወደ መተባበር በሚደረግ የታደሰ ጥሪ አማካይነት መከበሩ ተገልጿል።