በኢራን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በኢራን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች  

አሜሪካ ለዘጠኝ ተከታታይ ምሽቶች ኢራንን መደብደቧ ተነገረ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት እንደተነገሩት አሜሪካ ሰሞኑን ኢራን ላይ ያደረሰችው ጥቃቶች ሃገሪቷ ላይ “ከፍተኛ” የሆነ ጉዳት ማድረሱን ያስታወቁ ሲሆን፥ ይሄንን ጥቃት የፈጸሙት በቅርብ ቀናት ውስጥ በክልሉ ለተገደሉት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ክብር እንደሆነ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራን ላይ የፈጸሙት ጥቃት በጣም “ጠንካራ” እንደነበር እና ይህም ሰሞኑን ለተገደሉ ሦስት አሜሪካውያን ወታደሮች “ክብር” ሲባል የተፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።

ሦስቱ ወታደሮች የተገደሉት ኢራን በዮርዳኖስ እና በኢራቅ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የሦስቱ አሜሪካውያን ወታደሮች መገደልን ተከትሎ ኢራን ለድርጊቷ “እጥፍ ድርብ” ዋጋ እንደምትከፍል ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር እና የጦር አዛዦች የተሰጣቸውን ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተቀብለው፤ በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ የንግድ መርከቦችን አደጋ ላይ የሚጥሉ የኢራን ወታደራዊ አቅሞችን ማዳከማቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) አስታውቋል። ይህንን ተከትሎ በቴህራን እና በበርካታ የኢራን ከተሞች ፍንዳታዎች እንደተሰሙና ኢራንም በበኩሏ በባህሬን እና ኩዌት በሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች ላይ የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ማድረሷን አስታውቃለች።

ጥቃቱ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት እንደቀጠለ እና እሁድ ምሽት አዲስ ጥቃት እንደተከፈተ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) የገለጸ ሲሆን፥ በመላው ኢራንም ከፍተኛ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተነግሯል።

ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው አሜሪካ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ታብሪዝ፣ ቻባሃር፣ ኮናራክ፣ ባንዳር ባንዳር ማህሻህር እና ባንዳር ኢማም ኻሜኒን ጨምሮ በርካታ ከተሞች መመታታቸውን ይፋ አድርጓል።

ሦስቱ የአሜሪካ ወታደሮች ሕይወታቸውን ያጡት በኢራን እና አሜሪካ መካከል በተቀሰቀሰው ቀጣናዊ ግጭት ወቅት ሲሆን፤ ሁለቱ ወታደሮች የሞቱት በዮርዳኖስ በሚገኘው "ታወር 22" በተሰኘ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ በደረሰ የኢራን ባላስቲክ ሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ሲሆን፥ ሦስተኛው ወታደር ደግሞ በሰሜን ኢራቅ ወድቆ የነበረን የኢራን ጥቃት አድራሽ ድሮን በማምከን ላይ እያለ በደረሰ ፍንዳታ እንደሆነ ተነግሯል።

አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካስታወቀች በኋላ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩዌት እና በባህሬን ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን ያስታወቀ ሲሆን፥ ዘቡ ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ ሠራዊት ይዞታ ላይ በፈጸመው የአጸፋ የድሮን ጥቃት “የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የራዳር ሥርዓትን” ጨምሮ የተለያዩ ዒላማዎችን ማጥቃቱን እና “የጠላት የራዳር ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ” ማውደሙን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ እዚያው ኩዌት ውስጥ አሊ አል-ሳሌም ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት የድሮኖች መጠለያን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ዒላማ ማድረጉን ያመላከተ ሲሆን፥ በሌላ በኩል የኩዌት ኃይሎች በርካታ የኢራን ድሮኖች ወደ አየር ክልላቸው ሲገቡ ማምከናቸውን ዘግበዋል።

በሌላ በኩል ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወሽመጡን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ፍንዳታ እንዳጋጠማቸው የኢራን መገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን፥ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ይሄንን አስመልክቶ መርከቦቹ “ደኅንነቱ ባልተጠበቀ እና አደገኛ በሆነው ደቡባዊ መስመር እየተጓዙ ሳሉ ፍንዳታ እንዳጋጠማቸው” ቢገልጽም፥ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ግን ኢራን ስለመርከቦቹ ያቀረበችውን ማብራሪያ አስተባብሏል።

21 Jul 2026, 15:27