በሄይቲ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 1.5 ሚሊዮን መፈናቀላቸው እና 1,600 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሄይቲ የሰብዓዊ እና የደህንነት ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ በሄይቲ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ ልዩ መልዕክተኛ ካርሎስ ሩዊዝ ማሲዩ ይሄንን አስመልክተው እንደገለጹት 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በወሮበሎች ጥቃት ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን እና ከዚህም በተጨማሪም ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ቢያንስ 1,600 ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል።
ወንጀለኛ ቡድኖች ዋና ከተማዋን መቆጣጠራቸው
የተባበሩት መንግስታት ልዩ መልዕክተኛው ‘ኢንፎቤይ’ ከተሰኘው የድህረ ገጽ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከ10,000 እስከ 15,000 የሚገመቱ ወንጀለኛ ቡድኖች የሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-ኦ-ፕሪንስን ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚሆነውን ቦታ ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ገልጸው፥ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ለዓለም አቀፍ የደህንነት ድጋፍ ተልዕኮ ድጋፍ ቢያደርግም፣ በሃገሪቱ ውስጥ መረጋጋትን ወደነበረበት ለመመለስ በደህንነት፣ በፍትህ እና በልማት ሥራዎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ተናግረዋል።
ታይቶ የማይታወቅ ግን በአብዛኛው የተረሳ ቀውስ
ሄይቲ ሐምሌ 2013 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞይስ ከተገደሉበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ እንዳጋጠማት የጠቆሙት ካርሎስ ሩዊዝ፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ይዞታቸውን በተከታታይ ጊዜ በማስፋፋት ተቋማትን እና መሠረተ ልማቶችን በማፍረስ እንዲሁም አስፈላጊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ማድረጋቸው ተነግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ የዓለም ባንክ ገለፃ የሄይቲ ኢኮኖሚ እ.አ.አ. በ 2025 ዓ.ም. በተከታታይ ጊዜ ለሰባት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ መውደቁን ጠቁሞ፥ የሀገር ውስጥ ምርት በ 2.7 በመቶ መቀነሱን እና አማካይ የዋጋ ግሽበት ወደ 28.3 በመቶ ከፍ ማለቱን የገለጸ ሲሆን፥ ግማሽ ያህሉ የሃገሪቱ ህዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እንደሚኖር እና በቀን ከሶስት ዩሮ ያነሰ ክፍያ እንደሚያገኝ አመላክቷል።
የአውሮፓዊያኑ የ 2026 ዓ.ም. የኢኮኖሚ ሁኔታ አሁንም እጅግ እርግጠኛ ባልሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የተጠቆመ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሃገሪቱ ኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ 1.7 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖር በመተንበይ፥ የዋጋ ግሽበት ግን በትንሹ እንደሚቀንስ ቢጠበቅም ወደ 23.5 በመቶ ከፍ እንደሚል ያለውን ግምት አስቀምጧል።
እየተባባሰ የመጣው የደህንነት ሁኔታ
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የደህንነት ሁኔታው እየተባባሰ መሄዱ የተገለጸ ሲሆን፥ እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ መሰረት እ.አ.አ. በ 2025 ዓ.ም. ከ 5,500 በላይ ሰዎች ከቡድን ጋር በተያያዙ ጥቃቶች መገደላቸውን፣ ከ2,600 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ያመላከተ ሲሆን፥ በሄይቲ የተባበሩት መንግስታት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባወጣው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት መሠረት፣ በሃገሪቱ ውስጥ ባለው አለመረጋጋት የተነሳ በያዝነው የአውሮፓዊያኑ ዓመት ብቻ ቢያንስ 1,642 ሰዎችን ሕይወት መቀጠፉን እና 745 ሰዎችን ደግሞ መቁሰላቸውን ያመላከተ ሲሆን፥ እነዚህ አሃዞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ዓመፅ ስፋት እና የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ሥርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ ያለባቸውን የቁርጠኝነት ችግር ያሳያሉ ብሏል።
በአውሮፓዊያኑ 2024 ዓ.ም. የተቋቋመው እና በኬንያ የሚመራው ባለብዙ ወገን የደህንነት ድጋፍ ተልዕኮ አንዳንድ ስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ድጋፍ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ወንጀለኛ ቡድኖቹ የሚያካሂዱትን የግዛት ቁጥጥር መቀልበስ አለመቻሉና ይህም ወንጀለኛ ቡድኖቹ የዋና ከተማዋን አብዛኛውን ክፍል በመቆጣጠር ወደ ሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፉ ማስቻሉ ተነግሯል።