ፈልግ

በጋዛ ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ ህንጻ ላይ እስራኤል ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ የሲቪል መከላከያ ሰራተኞች የነፍስ አድን ሥራ ሲሰሩ በጋዛ ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ ህንጻ ላይ እስራኤል ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ የሲቪል መከላከያ ሰራተኞች የነፍስ አድን ሥራ ሲሰሩ  

የጋዛ ሲቪሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ ከዘጠኝ ወራት በኋላም መገደላቸው እንደቀጠለ ተነገረ

ከዘጠኝ ወራት በፊት በአሜሪካ ድጋፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ በጋዛ ሰርጥ ላይ በሚፈጸሙት ተከታታይ ገዳይ ጥቃቶች መካከል፣ ማክሰኞ ዕለት በተፈጸመ የእስራኤል የአየር ጥቃት የአንድ ቤተሰብ ስድስት አባላት መገደላቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ቤታቸውን በእሳት ጋይቶ የሞቱት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አባት፣ እናት እና አራቱ ልጆቻቸው በጥቃቱ ወቅት በሳብራ ሰፈር በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተኝተው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር ጥቃቱን እንደፈጸመ በማረጋገጥ፥ ዒላማው የሃማስ ታጣቂ ቡድን እንደነበር እና ስለ ጥቃቱ ውጤቱን እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

“ምንም ዓይነት አንጻራዊ መረጋጋት እና ከጥቃቱ ለመሸሽ የምንሄድበት አስተማማኝ ቦታ የለም” በማለት በጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡ ልጆች አያት በምሬት የተናገሩ ሲሆን፥ ጥቃቱ ሲፈጸም ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ወይም የማስጠንቀቂያ ምልክት እንዳልነበረ ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የፍልስጤም የህክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት ሃምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ የእስራኤል መከላከያ ኃይል (IDF) በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ ውስጥ አንድ ተሽከርካሪ ላይ ኢላማ በማድረግ በፈጸመው ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸውን ይፋ አድርገዋል።

በጋዛ የጤና ባለሙያዎች መረጃ መሰረት በእስራኤል እና በሃማስ ታጣቂዎች መካከል በጥቅምት ወር የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ በእስራኤል ጥቃቶች ከተገደሉት አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ ከ1,160 በላይ ፍልስጤማውያን በተጨማሪ እነዚህ አዳዲስ የሞት ክስተቶች አሃዙን ከፍ ማድረጋቸው ተነግሯል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ መጠነ ሰፊውን ውጊያ ቢያቆምም፥ በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ የሚፈጸሙት የእስራኤል ጥቃቶች ግን እንዳልቆሙ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ እስራኤል በበኩሏ ታጣቂዎችን ኢላማ እያደረገች እንደሆነ ትገልጻለች።

ግብጽ፣ ኳታር፣ ቱርክ እና አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አደራዳሪ ሃገራት የሃማስን ትጥቅ መፍታት እና የእስራኤል ኃይሎችን ከአከባቢው ማስወጣትን የሚጠይቀውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ያለውን ግጭት ለማስቆም ያዘጋጁትን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፥ ነገር ግን በእነዚህ ጥረቶች ላይ ብዙም መሻሻል እንዳልታየ ተገልጿል።

የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት የተጀመረው በሃማስ የሚመሩ ታጣቂዎች በደቡባዊ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽመው 1,200 ሰዎችን ገድለው፣ ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ ታጋች አድርገው በመውሰዳቸው እንደሆነ የሚታወስ ሲሆን፥ በጋዛ የጤና ባለሙያዎች መረጃ መሰረት ከዚያ በኋላ እስራኤል በወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ከ73,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ይገለፃል።

በአሁኑ ወቅት፣ የጋዛ 2 ሚሊዮን ህዝብ ማለት ይቻላል ሁሉም በባህር ዳርቻው ላይ በሚገኝ ጠባብ የመሬት ክፍል ውስጥ፣ በአብዛኛው ጊዜያዊ ድንኳኖች ወይም በጦርነቱ ምክንያት በወደሙ ህንጻዎች ውስጥ እንደሚኖሩ እና አስከፊ የሆነ የሰብዓዊ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

23 Jul 2026, 15:42