የአሜሪካ እና ኢራን ውይይት በስዊዘርላንድ መካሄዱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ለ18 ሰዓታት የተካሄደው የአሜሪካና ኢራን ከፍተኛ ደረጃ ውይይት አበረታች እድገት ማሳየቱን አስታራቂ አገራት ፓኪስታንና ኳታር የገለጹ ሲሆን፥ ሁለቱ ወገኖች በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ለመድረስ መስማማታቸውም ተነግሯል።
ይህ ውይይት የተካሄደው ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በኋላ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የኢራን ጦር የሆርሙዝ ባህርን እንደገና ዘግቻለሁ ብሎ ካስታወቀ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
እስራኤል ቅዳሜ ዕለት ባደረገችው ተከታታይ የአየር ጥቃት ቢያንስ 47 ሰዎች መሞታቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የኢራን ዋና ተደራዳሪዎች ውይይቱን አጠናቀው ወደ ቴህራን ሲመለሱ፤ የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በኢስላማባድ መግባቢያ ሰነድ ዙሪያ ድርድሩን እንዲቀጥል በስዊዘርላንድ መቅረታቸው ተገልጿል።
ከዚህ በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለሄዝቦላህ የምትሰጠውን ድጋፍ በመጥቀስ የወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ዛቻ ሲያሰሙ የኢራን ተደራዳሪ መሀመድ ባገር ጋሊባፍ በበኩላቸው አሜሪካ በንግግሯ ጥንቃቄ እንድታደርግ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ እስከሚያስፈልገው ጊዜ ድረስ እንደሚቆይ የገለጹ ሲሆን፥ ሄዝቦላህ በበኩሉ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ የሚደረግን ማንኛውንም ጥሰት እንደሚቃወም አስታውቋል።