አሜሪካ እና ኢራን ጦርነትን ለማስቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ ዘላለም ኃይሉ
ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ ያደረገችው ፓኪስታን፥ የስምምነት ፊርማውም አርብ ዕለት በስዊዘርላንድ እንደሚካሄድ የገለጸች ሲሆን፥ አሸማጋይ ሃገራት ይህ ስምምነት ለወራት ከቆዩ ጥረቶች እና ጅምሮች በኋላ ወደ ሰላም ለማምጣት የተደረገ እጅግ በጣም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት ይህ ስምምነት ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዋሽንግተን ቁልፍ ፍላጎት የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንደገና መከፈትን እንደሚያካትት የገለጹ ሲሆን፥ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት ከምንጊዜውም በላይ መቃረቡን ቀደም ሲል መግለጻቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ሁለት ዋና ዋና ምዕራፎች እንዳሉ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ጦርነቱ በአስቸኳይ የሚቆምበት እና ጥቃቶች ዳግም እንዳይከፈቱ ዋስትና የሚሰጥበት እና ለሃገሪቱ ትልቅ ድል የሆነ የመግባቢያ ሰነድ መሆኑን ገልጸው፥ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ዕጣ ፈንታ የማዕቀቦች መነሳት እና የታገዱ የኢራን ሃብቶች በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ የሚደረግ ዝርዝር ድርድር መሆኑን አመልክተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱ ስምምነት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሊፈረም እንደሚችል የጠቆሙ ቢሆንም፥ በኢራን በኩል ግን ሰነዱ ወደ ፊርማ ከማምራቱ በፊት በጦር ኃይሉ፣ በፓርላማው እና በጠቅላይ መሪው በኩል ታይቶ ሀገራዊ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ስለሚያስፈልግ ሂደቱ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተዘግቧል።
እሑድ መገባደጃ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ያሳወቀችው ፓኪስታን ስምምነቱ “ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም አከባቢዎች የሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ያስቆማል” ያለች ቢሆንም፥ እስራኤል በበኩሏ እስካሁን ይፋዊ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን፥ ይሁን እንጂ የሃገሪቷ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በሊባኖስ ውስጥ ያለውን ቆይታ ያለ ምንም ገደብ ለማቆየት እንዳሰበ መግለጻቸው ሰፋ ያለ የተኩስ አቁም ማዕቀፍ ቢኖርም የእስራኤል ጥቃቶች እንደሚቀጥሉ ያመለክታል ተብሏል።
የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ቅዳሜ ማለዳ እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እና ቁልፍ የአመራር እና ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ጦርነቱን እንደጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፥ በመጀመሪያው ዕለት በኢራን ላይ በተፈጸሙት የተቀናጁ የአውሮፕላን እና የሚሳዔል ጥቃቶች የእስላማዊቷን አብዮታዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የበላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወቃል።
ይሄንን ተከትሎ ለዘመናት የገነባቻቸው ዘመናዊ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎቿን በመጠቀም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ የአሜሪካ አጋር ሃገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ለቀናት በማካሄዷ ግጭቱ በፍጥነት መስፋፋቱ ይታወቃል።
በጦርነቱ ወቅት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ በኢራን ሚሳኤሎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፥ የአካባቢው ባለስልጣናት ሳይቀር ግጭቱ በድርድር እንዲቆም ለሳምንታት ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነቱን በመካከለኛው ምስራቅ እና በአከባቢው የነበረው “ደህንነት እና መረጋጋት” ወደነበረበት ለመመለስ ይረዳል በማለት ስምምነቱን “ጉልህ የሆነ እድገት” የታየበት ስትል ጠርታዋለች።
የአውሮፓ ሃገራት ስለድርድር ማዕቀፍ ስምምነቱ ዜና አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ የአውሮፓ አክሲዮኖች ሰኞ ዕለት ዋጋቸው ከፍ ማለት እንደጀመሩ እና የጀርመኑ ‘ዳክስ’ እና የፈረንሳይ ‘ሲኤሲ 40’ ወደ 1.7 በመቶ መጨመራቸው ተገልጿል።