ኢራን እና አሜሪካ የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የመጨረሻውን ውይይት ሊያደርጉ እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከሳምንታት ውይይት በኋላ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የፊታችን አርብ በስዊዘርላንድ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።
ይሄንን ተከትሎ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አገራቸው ከኢራን ጋር ከመግባባት ላይ የደረሰችበትን ባለ 14 ነጥብ ሰነድ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ ስምምነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እንደሚያደርግ እንዲሁም አራት ወራት የሞላውን የሁለቱን አገር ጦርነት ያስቆማል የሚል እምነት ማሳደራቸው ተገልጿል።
የትራምፕ አስተዳደር ባለ 14 ነጥቡ ስምምነት ‘በአፈጻጸም ላይ የተመሠረተ’ መሆኑን ተናግረው፥ ኢራን ልትጠቀም የምትችለው ስምምነቱን የምታከብር ከሆነ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን፥ ትራምፕ በቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ስምምነቱን ሲፈርሙ የኢራኑ ፕሬዚዳንትም ፊርማቸውን ማኖራቸውን ቴህራን አስታውቃለች።
ባለ አስራ አራት ነጥቡ የሰላም ስምምነት
የተፋላሚዎቹ ሀገራት አጋሮች በሊባኖስም ሆነ በሁሉም ግንባሮች ጦርነትንና ወታደራዊ ጥቃቶችን በአስቸኳይና በቋሚነት ለማቆም፣ ዳግም ጥቃት ላለመሰንዘር፣ እንዲሁም የሊባኖስን ሉዓላዊነት ለማክበር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሁለቱ ሀገራት የሌላኛውን ወገን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማክበር፣ እርስ በእርስ በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት ለመቆጠብ ቃል ይገባሉ።
በጋራ ስምምነት ሊራዘም በሚችል ቢበዛ በ60 ቀናት ውስጥ ለመደራደርና የመጨረሻውን ስምምነት ለማሳካት ቁርጠኝነታቸውን ይገልጻሉ።
አሜሪካ ስምምነቱ በተፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ በኢራን ላይ የጣለችውን የባሕር ላይ ከበባ ሙሉ በሙሉ ለማንሳትና የመጨረሻው ስምምነት ሲደረስ ጦሯን ከኢራን አቅራቢያ ለማስወጣት ቃል ትገባለች።
ኢራን ለንግድ መርከቦች ለ60 ቀናት ነፃና ደህንነቱ የተጠበቀ የባሕር ላይ ጉዞ በማመቻቸት፣ ፈንጂዎችንና እንቅፋቶችን በማስወገድ በ30 ቀናት ውስጥ እንቅስቃሴውን ወደነበረበት ትመልሳለች፤ ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ የወደፊት አስተዳደር ከኦማንና አጎራባች ሀገራት ጋር ትመክራለች።
አሜሪካ ለኢራን መልሶ ግንባታ እና የኢኮኖሚ ልማት የሚውል 300 ቢሊዮን ዶላር ከቀጠናው አጋሮች ጋር ለማዘጋጀትና አስፈላጊ የሆኑ የፋይናንስ ፈቃዶችን በመስጠት አተገባበሩን በ60 ቀናት ውስጥ አጠናቃ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
አሜሪካ በኢራን ላይ የተጣሉትን ሁሉንም አይነት ማዕቀቦች (የተመድን እና የራሷን ጨምሮ) በተስማሙበት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሙሉ በሙሉ ለማንሳት ቃል ስትገባ፥ ሁለቱም ሀገራት ይህንን ጉዳይ በድርድሩ ቅድሚያ ሰጥተው በአስቸኳይ ለመፍታት ተስማምተዋል።
ኢራን የኑክሌር መሳሪያ ላለማምረት በድጋሚ ስታረጋግጥ፥ ሁለቱ ሀገራት የተከማቸውን የበለጸገ የኑክሌር ማዕድን በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቁጥጥር ስር ለማቅለጥና ስለወደፊቱ የኢራን የኑክሌር ማበልጸግ ፍላጎቶች ዙሪያ በጋራ ለመወያየት ተስማምተዋል።
የመጨረሻው ስምምነት እስኪደረስ ድረስ ሁለቱም ሀገራት ነባራዊ ሁኔታቸውን ለመጠበቅ ተስማምተዋል። በዚህም ኢራን የኑክሌር ፕሮግራሟን አሁን ባለበት የምታቆይ ሲሆን፥ አሜሪካ ደግሞ አዲስ ማዕቀብ ላለመጣልና በቀጠናው ተጨማሪ ጦር ላለማሰማራት ተስማምታለች።
አሜሪካ ማዕቀቦቹ ሙሉ በሙሉ እስኪነሱ ድረስ ለኢራን የነዳጅ ምርቶች ኤክስፖርት እንዲሁም ለተያያዥ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ከቅጣት ነፃ የሚያደርጉ ፈቃዶችን ለመስጠት ቃል ትገባለች።
አሜሪካ የታገዱ የኢራን ገንዘቦችና ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ተለቅቀው በኢራን ማዕከላዊ ባንክ አማካኝነት ለተፈለገው አገልግሎት (ክፍያ) እንዲውሉ አስፈላጊውን ፈቃድ ሁሉ ለመስጠት ቃል ገብታለች።
አሜሪካና ኢራን የስምምነቱን አፈፃፀምና የቀጣይነት ተገዢነት የሚከታተል አስፈፃሚ አካል (አሠራር) ለማቋቋም ተስማምተዋል።
አንቀጽ 1፣ 4፣ 5፣ 10 እና 11 በተግባር ላይ መዋል ሲጀምሩ አሜሪካ እና ኢራን በቀሪዎቹ አንቀጾች ላይ ብቻ በማተኮር የመጨረሻውን ስምምነት ድርድር ይጀምራሉ።
የመጨረሻው ስምምነት አስገዳጅ በሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ይጸድቃል የሚሉ ናቸው።
ዋሽንግተን፣ ኢስላማባድ እና ቴህራን ሰኞ ማለዳ የመግባቢያ ሰነዱ ከሳምንታት ውይይት በኋላ መጠናቀቁን እና አርብ በስዊዘርላንድ እንደሚፈረም አረጋግጠው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ነገር ግን የፋይናንሺያል ታይምስ እንደዘገበው የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መከፈትን በማስመልከት ወዲያው ተግባራዊ ይሆናል ወይ የሚለው ጥያቄ መልስ አጠራጣሪ እንደሆነ ያለውን ስጋት ገልጿል።
የሊባኖስ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት እንደገለጸው የእስራኤል ጄቶች ናባቲህ አል ፋውቃ አካባቢ እና በአቅራቢያው በሚገኘው ክፋር ቴብኒት ዳርቻ ላይ ጥቃት መድረሳችውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በደቡባዊ ሊባኖስ የነበረው ቀውስ ሁለቱ ሃገራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ከተገለጸ በኋላ በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል ያለውን ጦርነት ይቆማል ተብሎ ተስፋ ተደረጎ የነበረ ቢሆንም፥ የእስራኤል ወታደሮች ረቡዕ ዕለት በደቡባዊ ሊባኖስ አዲስ ጥቃቶችን መፈጸማቸው እና ስምምነቱ ይፋ ከሆነ በኋላ በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።