የፍልስጤም እና የእስራኤል ግጭት የፍልስጤም እና የእስራኤል ግጭት   (AFP or licensors)

በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ዓለም አቀፍ ቀውሶች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነገረ

ግጭቶች እና ድንገተኛ ሰብዓዊ አደጋዎች በመካከለኛው ምስራቅ፣ በዩክሬን እና አፍሪካ ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተለያዩ ግጭቶች እና ሰብዓዊ ድንገተኛ አደጋዎች በመላው መካከለኛው ምስራቅ፣ ዩክሬን እና አፍሪካ ሃገራት ውስጥ እየተባባሱ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የአሜሪካ እና የኢራን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ዓለም በጉጉት እየተጠባበቀ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አካባቢ ያሉ መስተጓጎሎች ዋነኛ አሳሳቢ ጉዳይ ሆነው መቀጠላቸው እየተነገረ ይገኛል።

የተባበሩት መንግስታት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የዓለም የነዳጅ እና የማዳበሪያ ክምችት በአደገኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ይህም የምግብ ምርት የመቀነስ አደጋን እንደሚፈጥር ተነግሯል።

እ.አ.አ. ከ 1980 ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ቁጥር በማስመዝገብ ስትራቴጂካዊ የነዳጅ ክምችት በቀን ወደ 357 ሚሊዮን በርሜል መውረዱ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ከኤልኒኖ ጋር የተገናኘው የሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ዓለም አቀፋዊ ውጥረትን ከፍ ማድረጉን ጨምሮ ማንኛውም በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የሚደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ የከፋ ዓለም አቀፍ ውጥረትን ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል።

በሌላ በኩል አራት ወራትን ያስቆጠረው ጥቃት እና መፈናቀል በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወሊድና የስነ-ተዋልዶ ጤናን እንዲሁም የወጣቶችን እና የሴቶችን መብት ለማረጋገጥ የሚሰራው የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድ (UNFPA)  እንደዘገበው ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 20 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ማለትም በ16,000 የሚገመቱ ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ ከ 1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ተፈናቅለው እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል።

በጤና ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የእናቶች እና የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት ተደራሽነትን እየገደበ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በሰው ብዛት የተጨናነቁት መጠለያዎችም በርካታ ሴቶች የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ መከልከሉ ይገለፃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ምንም ዓይነት የመቀነስ አዝማሚያ አለማሳየቱ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ አራት ዓመታትን ያስቆጠረውን ጦርነት እንዲያስቆሙ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ጫናው እየበረታ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ዩክሬን ሰኞ ዕለት በሞስኮ ላይ ሌላ ጥቃት መሰንዘሯ ተነግሯል።

የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ ዩክሬን ባለፈው ሳምንት በዓይነቱ ትልቅ የተባለ ጥቃት በመፈጸም የሩሲያ ዋና ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ በሰው አልባ አውሮፕላን መምታቷ የተነገረ ሲሆን፥ በሌላ በኩል በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ብቻ በአራት ዓመታት ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጉዳት መመዝገቡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቆጣጣሪዎች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በሱዳን በጦር ኃይሉ እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መካከል የተነሳው ከባድ ውጊያ አራተኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን፥ በዚህ ጦርነት ስልታዊ የሆነ ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የጣሱ ወንጀሎች መፈፀማቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በበኩሉ ሁለቱም ወገኖች በሰው አልባ አውሮፕላኖች ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ማውደማቸውን ጨምሮ በቅርቡ ደግሞ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኙ ሲቪሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረሳቸውን ይፋ አድርጓል።

በያዝነው ዓመት ከጥር እስከ ግንቦት ወር ባሉት ጊዜያት ብቻ ከ1,000 በላይ ንፁሀን ዜጎች በድሮን ጥቃቶች የተገደሉ ሲሆን፥ ይህም እስካሁን ከግጭት ጋር በተያያዙ በንጹሃን ዜጎች ላይ ከደረሱ ሞቶች መካከል በዚህ ዓመት የደረሰው 80 በመቶውን ድርሻ ይይዛል ተብሏል።

 

 

25 Jun 2026, 15:34