በሆርሙዝ ባህር ዳርቻ አከባቢ በሚገኘው የባንደር አባስ ወደብ ላይ የቆሙ መርከቦች በሆርሙዝ ባህር ዳርቻ አከባቢ በሚገኘው የባንደር አባስ ወደብ ላይ የቆሙ መርከቦች  

የኢራን ግጭትን የሚያስቆም ስምምነት ተፈረመ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡበትን ግጭት ያስቆማል የተባለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አሜሪካ እና ኢራን  የገቡበትን ጦርነት ለማቆም ያለመ የመግባቢያ ስምምነት ረቡዕ ዕለት መፈራረማቸውን ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረውን የባሕር ላይ መተላለፊያ ማዕቀብ ያነሳች ሲሆን፥ ውሳኔው የተላለፈው “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት” እንደሆነ የገለጸው ማዕከላዊ ዕዙ፤ ሆኖም ግብ የአሜሪካ መርከቦች “በአካባቢው እንደሚቆዩ” አስታውቋል።

አሜሪካ እና ኢራን ከሦስት ወራት በላይ የቆየውን የባሕረ ሰላጤው ጦርነትን የሚያስቆመው የመግባቢያ ስምምነት ስዊትዘርላንድ ውስጥ እንደሚፈርሙ እና በዚያውም ቀጣይ ንግግር እንደሚያካሂዱ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በቅድሚያ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት በሚል ምክንያት የጊዜ ሰሌዳው ወደቀጣይ ቀናት መሸጋገሩ ተገልጿል።

የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት ኢራን እና አሜሪካ ስምምነቱን በርቀት ፈርመው ይፋ ስላደረጉት በጄኔቫ ሊካሄድ የነበረው የፊርማ ሥነ ሥርዓት መሰረዙን ገልጸዋል።

ሃሙስ ዕለት በተለቀቀው ጽሁፍ መሰረት ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኢራን እና አጋሮቻቸው በሊባኖስ እየተካሄደ የሚገኘውን ጥቃት ጨምሮ ጦርነቱን ለማቆም እና ሁሉንም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ እና በቋሚነት ለማቆም ተስማምተዋል።

ተዋዋይ ወገኖች የወደፊት ጠላትነትን ላለመፍጠር፣ ማስፈራሪያዎችን ወይም ሃይልን ላለመጠቀም እና የሊባኖስን ግዛታዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል።

ኢራን ከአሜሪካ ጋር የደረሰችበት የመግባቢያ ሰነድ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ማድረግን እና የግዛት ሉዓላዊነት ማስጠበቅን እንደሚያካትት ያስታወቀች ሲሆን፥ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በስምምነቱ መሠረት “ሊባኖስ ውስጥ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ማድረግን ጨምሮ በሁሉም የውጊያ አውድማዎች የተኩስ አቁም እንደሚተገበር እንጠብቃለን” ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ተሰልፋ ኢራንን የወጋቻት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የደረሱትን ስምምነት ውድቅ እንዲያደርጉ ከተቃዋሚዎቻቸው ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ ተዘግቧል።

የሰላም ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ የነዳጅ ዋጋ የቀነሰ ሲሆን፥ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል 1.5 በመቶ በመቀነስ ወደ 78 ዶላር ዝቅ ብሏል።

የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ቅዳሜ ማለዳ እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እና ቁልፍ የአመራር እና ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ጦርነቱን እንደጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፥ በመጀመሪያው ዕለት በኢራን ላይ በተፈጸሙት የተቀናጁ የአውሮፕላን እና የሚሳዔል ጥቃቶች የእስላማዊቷን አብዮታዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የበላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወቃል።

ይሄንን ተከትሎ ለዘመናት የገነባቻቸው ዘመናዊ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎቿን በመጠቀም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ የአሜሪካ አጋር ሃገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ለቀናት በማካሄዷ ግጭቱ በፍጥነት መስፋፋቱ ይታወቃል።

በሌላ ዜና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር ሃሙስ ዕለት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ሀላፊ ካጃ ካላስ እስራኤልን ከደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ሥርዓት ጋር በማመሳሰል መናገራቸው መዘገቡን ተከትሎ ከሃላፊዋ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያቋርጥ ገልጸዋል።

19 Jun 2026, 15:14