የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታወቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ ውሳኔው በገዢው የሌበር ፓርቲ ውስጥ ከተፈጠረ ጫና እና የፖለቲካ ድጋፍ መቀነስ በኋላ የተወሰደ መሆኑ ተገልጿል።
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታርመር ከተረከቡት የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን መንበር እና ከፓርቲ መሪነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በድንገት ያስታወቁ ሲሆን፥ ይህ ያልተጠበቀ ውሳኔ በብሪታኒያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን እና መነጋገርያን ቢፈጥርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራቸውን የለቀቁበትን ዝርዝር ምክንያት በሚመለከት በቅርቡ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል ።
ስታርመር አዲስ የሌበር ፓርቲ መሪ እስኪመረጥ ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን፥ አዲሱ መሪ ከመስከረም 2019 ዓ.ም. በፊት እንደሚመረጥ ይጠበቃል።
ስታርመር 2016 ዓ.ም. በተካሄደ ምርጫ የሌበር ፓርቲን ወደ ታላቅ ድል የመሩ ቢሆንም፥ በቅርብ ወራት የኢኮኖሚ ችግሮች፣ የህዝብ ቅሬታዎች እና የፓርቲ ውስጣዊ ተቃውሞዎች ግፊት ምክንያት ድጋፋቸው ቀንሶ እንደነበር ይገለፃል።
በአሁኑ ወቅት የማንቺስተር ከንቲባ የሆኑት አንዲ በርንሃም ስታርመርን ሊተኩ የሚችሉ ቀዳሚ እጩ መሆናቸው የተለያዩ ዘገባዎች እያሳዩ የሚገኝ ሲሆን፥ ትክክለኛው ተመራጭ መጪው መስከረም በሚካሄድ ምርጫ እንደሚታወቅ ተነግሯል።
ባለፈው ሳምንት አንዲ በርንሀም በግሬተር ማንችስተር ምርጫ ማሸነፋቸው የሌበር ፓርቲ መሪ በመሆን ስታርመርን እንዲገዳደሩ መንገድ ከፍቶላቸዋል እየተባለ ይገኛል።
ኪር ስታርመር በሰጡት አጭር መግለጫ ሀገራቸውንና ፓርቲያቸውን በታማኝነት ማገልገላቸውን ገልጸው አሁን ግን ለአዳዲስ መሪዎች መንገዱን መልቀቅ ተገቢ ሆኖ ማግኘታቸውን የጠቆሙ ሲሆን፥ ውሳኔውን ተከትሎ የሌበር ፓርቲ በአስቸኳይ አዲስ ሊቀመንበር እና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ የውስጥ ሂደቶችን የሚጀምር ሲሆን አዲስ መሪ እስኪሰየም ድረስም በጊዜያዊነት ሀገሪቱን ማን እንደሚመራ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ስታርመር ወደ ፖለቲካ የገቡት የሚሊዮኖችን ሕይወት በተሻለ ሁኔታ ለመለወጥ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን፥ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2024 ሌበር ፓርቲ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ባደረጉት ንግግር ይህንኑ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
የባለፈው ሳምንት የምርጫ ውጤት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንዲ በርንሀም መንገድ እንዲያመቻቹ ከሚኒስትሮቻቸው ጫና እንደበረታባቸው የሚነገር ሲሆን፥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ጫና የበረታባቸውን ኪር ስታርመር “ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ይለቃሉ” በማለት በኃላፊነት የነበራቸውን ቆይታ መተቸታቸው ይታወሳል።
ስታርመር በተገቢው መንገድ ሥልጣን እንደሚያስረክቡ ገልጸው ለቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጸው፥ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው አንጻር "ጠንካራ የሆነ እና ፍትሕ የሰፈነበት አገር" እንደሚረከቡ ማወቅ አለባቸው ካሉ በኋላ፥ ከጎናቸው የነበሩ ጓደኞቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸውንም አመስግነዋል።