እህት ፔትሪኒ 'የወደፊት የሥራ እድል በማሽን ላይ ሳይሆን በሰው ልጅ የሞራል ውሳኔ ላይ ነው' ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ይህ ቁልፍ የሆነ ማሳሰቢያ የተገለጸው የቫቲካን ከተማ ጠቅላይ ግዛት ፕሬዝዳንት እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ ማክሰኞ ማለዳ ሮም በሚገኘው ጳጳሳዊ የግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲ ‘ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የወደፊት የሥራ ዕድል’ በሚል ጭብጥ በተካሄደው የውይይት መርሃ ግብር ወቅት በደረጉት ንግግር እንደሆነ ተገልጿል።
በቅድስት መንበር የአሜሪካ ኤምባሲ የተዘጋጀው እና በቅድስት መንበር የአውስትራሊያ፣ የብሪታንያ፣ የካናዳ፣ የጃፓን፣ የታይዋን እና የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደሮች የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ከጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ፣ ከካቶሊክ የቴክኖሎጂ ተቋም እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥናት ማዕከል ከሆነው ሊዮነም የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ድንበሮችን እና የሥራ እድልን በመቃኘት መሪ ድምጾችን ማሰባሰቡ ተነግሯል።
ውይይቱ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን፣ የሃይማኖት ምሁራንን፣ የስነ-ምግባር ባለሙያዎችን፣ ተቆጣጣሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ምሁራንን እና የሲቪል ማህበረሰብን አንድ ላይ በማሰባሰብ ስለ ሰው ሰራሽ አስተሎት እና ስለወደፊቱ የስራ ዕድል እንዲሁም ይሄንን የወደፊት ሁኔታ በመቅረጽ ረገድ ባለው የጋራ ኃላፊነት ላይ ለመምከር የታለመ እንደሆነ ተገልጿል።
እህት ፔትሪኒ አሁን ስላለንበት 'ወሳኙ መስቀለኛ መንገድ'
እህት ፔትሪኒ በንግግራቸው ወቅት አሁን ስላለንበት 'ወሳኙ መስቀለኛ መንገድ' በማንሳት ሰው ሰራሽ አስተውሎት የጋራ ሃላፊነትን የሚፈልግ የለውጥ ሃይል እንደሆነ ጠቁመው፥ ‘በዛሬው ጥልቅ የፈጠራ ዘመን ሰው ሰራሽ አስተውሎት ትልቅ አቅም እንደሚሰጥ፥ ነገር ግን “ወደ ወሳኙ መስቀለኛ መንገድ እንደሚያደርሰን” በአጽንዖት ገልጸዋል።
“ይህ ቴክኖሎጂ የሁሉንም የሰው ልጅ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ለማረጋገጥ ምርጫዎች መደረግ አለባቸው” ያሉት እህት ፔትሪኒ፥ ሁልጊዜም ቢሆን ከምንም በላይ ለሰብዓዊ እና ማህበራዊ እሴቶች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አሳስበው፥ የሥራ ዕድል ከእነዚህ ምርጫዎች አንዱና ዋነኛው ዒላማ መሆኑን አስታውሰዋል።
“የሥራ ዕድል ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጅ በምድር ላይ የመኖር መሠረታዊ ገጽታ እንደሆነ ስለምታምን ብቻ ሳይሆን ከተጨባጭ ይዘቱ ተለይቶ አንድ ሰው ሰብዓዊነቱን እንዲገነዘብ የሚያስችል ልኬት ነው” ያሉት የቫቲካን ከተማ ጠቅላይ ግዛት ፕሬዚደንት፥ በሌላ አነጋገር ሰው እንደ ሰው ጥሪውን እንዲፈጽም የሚያስችለው እንደሆነ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥራን እና ግንኙነትን እንደገና የሚገልጽበት ዘመን ላይ ነን በማለት አብራርተዋል።
የሰው ኃይል ገበያን እንደገና ማሻሻል፣ ዕድሎችን መፍጠር፣ ግን ደግሞ አዳዲስ የማግለል ዓይነቶች
ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት በሚለዋወጠው ዓለም ውስጥ ሰው መሆን ምን ማለት ነው? ብለው የጠየቁት እህት ፔትሪኒ፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በእውነቱ ከመገልገያ መሳሪያ በላይ እንደሆነ እና የለውጥ ኃይል እንደሆነ ጠቅሰው፥ እነዚህን የመገልገያ ስርዓቶች በሙሉ አቅም ጥቅም ላይ መዋል የሰው ኃይል ገበያውን እንደገና በመቅረጽ እና አዳዲስ እድሎችን በመፍጠር አዳዲስ የማግለል ዓይነቶችን ይፈጥራል በማለት አስረድተዋል።
የቫቲካኗ ባለስልጣን “የጤና እና የደህንነት ለውጥ፡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታላይዜሽን ሚና በሥራ ዕድል ላይ” በሚል ርዕስ በዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት ዘገባ ላይ የተገለጸውን የቴክኖሎጂ እድገት አንዳንድ አወንታዊ ለውጦችን በማንሳት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፥ በዚህ ተቋም ጥናት መሰረት አዲስ እየመጣ ያለው ስርዓት ለአደጋ ተጋላጭነትን በእጅጉ ለመቀነስ፣ በሥራ ቦታ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እና አጠቃላይ የሥራ ሁኔታን ለማሻሻል እንደሚያችል ያመላክታል ያሉ ሲሆን፥ ይህም በሥራ ቦታ ደህንነትን እና ጤናን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ክትትል የሚደረግበትን መንገድም ይጨምራል ብለዋል።
ሆኖም ግን ከልክ ያለፈ ክትትል፣ የሥራ መጠናከር፣ እንዲሁም አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ተግዳሮቶችን የመሳሰሉ አደጋዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያስጠነቀቁት እህት ፔትሪኒ፥ ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት እንደነዚህ ያሉ አደጋዎችን ለመቅረፍ ‘ንቁ፣ በማስረጃ የተደገፈ እና አሳታፊ አካሄድ እንዲኖር’ ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሰለጠኑ እና ችሎታ በሌላቸው ሰራተኞች ላይ የቴክኖሎጂ ለውጥ የሚያስከትላቸው ውጤቶች፥ አውቶሜሽን የሚያስከትለውን ውጤት በማሟያነት ወይም በመተካት መልክ ሊታይ እንደሚችል በማንሳት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
ቴክኖሎጂ ሰውን ለማገልገል እንጂ ለመተካት አይደለም
የቴክኖሎጂ ለውጥ በተቋማዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የገለጹት እህት ፔትሪኒ፥ በርካታ ባለሙያዎች አጽንዖት ሰጥተው እንደሚገልጹት ቴክኖሎጂ ሰዎችን ለማገልገል እንጂ እነሱን ለመተካት እንዳልሆነ በመጥቀስ፤ ባለሙያዎቹ በሰዎች እና በቴክኖሎጂ መካከል በሃላፊነት፣ በትብብር እና በትምህርት ላይ የተመሰረተ ጥምረት እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።
“ሰው ሰራሽ አስተውሎት በራዕይ ወይም በመሳሪያ ከተመራ በጣም ጠቃሚ የመማሪያ እና የማስተዋል መንገድ ሊሆን ይችላል” ያሉት እህት ፔትሪኒ፥ የጋራ ኃላፊነትን በሚያመለክት ሁኔታ የሰውን ልጅ ማዕከል ባደረገ ራዕይ የመመራት አስፈላጊነት ጠቁመዋል።
በዚህም ረገድ መንግሥታት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ ቁጥጥሩን እንዲያጠናክሩ፣ ሥነ ምግባርን እንዲያስተምሩ፣ መምህራን እውቀት ያላቸውን ዜጎች እንዲያሠለጥኑ እና እያንዳንዱ ሰው ቴክኖሎጂን በአግባቡ እና በኃላፊነት እንድንጠቀም ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል።
'ሰው ሰራሽ አስተውሎትን መፍራት የለብንም፥ በአንፃሩም በቀላሉ መቀበል የለብንም'
በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ ሁል ጊዜ የማንኛውም ዓይነት ሥራ አካል ነው ብለን ካመንን ቴክኒካዊ ብቻ ሳይሆን ዘላለማዊ የእድገት ራዕይን ለማራመድ ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህ አውድ የቴክኖሎጂ እድገት ብቻውን የሚጓዝ ሳይሆን የሰብዓዊ፣ የባህል እና የመንፈሳዊ እድገትን እንዲያካትት አሳስበዋል።
'ሰው ሰራሽ አስተውሎትን መፍራት የለብንም፥ በአንፃሩም በቀላሉ መቀበል የለብንም' ያሉት እህት ፔትሪኒ፥ ምንም እንኳን አንዳንድ ተመራማሪዎች መተግበሪያ ማሽኖቹ አክባሪ እና ጨዋነት ያለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት እንዲዳብር ከሥነ ምግባራዊ መስፈርቶች ጋር መያያዝ እንዳለባቸው ቢናገሩም ከዚህ የበለጠ እርምጃ መወሰድ እንደሚያስፈልግ ማመናቸውን ገልጸዋል።
“በመጨረሻም መጪው ጊዜ የተመረኮዘው በማሽኖች ላይ ሳይሆን በሰው ልጅ የሞራል ምርጫ ላይ ነው” በማለት አጥብቀው የተናገሩት እህት ፔትሪኒ፥ ይህ አዲስ የቴክኖሎጂ ዘመን በሁሉም መስክ የላቀ የፍትህ እና የአብሮነት ዘመን ወይም አዲስ የእኩልነት ዘመን እንዲያመጣ የመወሰን አቅም እና ሃላፊነት አለብን ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቫቲካን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በትኩረት እያየች ያለበትን ሁኔታ ገልጸው፥ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከሙያዊ እና ከማህበራዊ እይታ አንጻር በሰዎች ድርጊት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን የሚቀጥል እውነታ እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን አካሄዱ አስቀድሞ የተወሰነ ሳይሆን ንድፍ አውጪ እና ተግባራዊ የሆኑትን ምርጫዎች፣ እሴቶች እና ፍላጎቶች የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
የባለሙያዎች፣ መሪዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች ፕሮግራም
የውይይቱ መርሐ ግብር በቅድስት መንበር የአሜሪካ አምባሳደር ላውራ ሆቻላ የተግባር ጥሪ የተከፈተ ሲሆን በመቀጠልም ጳጳሳዊ የግሪጎርያን ዩኒቨርሲቲ ሃላፊ የሆኑር አባ ማርክ ሉዊስ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ የውይይቱ መሪ ሃሳብ በጥልቅ ማሰብና ማሰላሰልን እንደሚጠይቅ አመላክተው፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ ሲውል የሥነ ምግባር እሴቶች ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል።