የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል መርከብ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የባህር ላይ እገዳን ተግባራዊ እያደረገ የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል መርከብ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የባህር ላይ እገዳን ተግባራዊ እያደረገ 

የሆርሙዝ ውዝግብ ተጠናክሮ መቀጠሉ እና የዓለም የንግድ ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱ ተነገረ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን እና በአሜሪካ የባህር ኃይል መካከል ሁለቱ ወገኖች እርስ በርስ የሚወነጃጀሉበት በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ግጭት ቢፈጠርም አሁንም ድረስ ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ውይይቱ እንደቀጠለ የገለጹ ሲሆን፥ ይህ በእንዲህ እንዳለ የባህር ወሽመጡ መዘጋት በፈጠረው መጠነ ሰፊ መስተጓጎል ዓለም አቀፉ ንግድ ከፍተኛ ተግዳሮት ውስጥ እንደገባ እየተገለጸ ይገኛል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ፕረዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሄንን ይበሉ እንጂ ባለፈው አርብ ዕለት በፓኪስታን አደራዳሪነት እየተካሄደ የሚገኘው የተኩስ አቁም ውይይቱን መስተጓጎል የሚያሳይ ተጨማሪ ምልክት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የአየር መከላከያዎቿ ከኢራን የሚወነጨፉ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች ራሷን ለመጠበቅ በንቃት እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግራለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋት በፈጠረው መጠነ ሰፊ መስተጓጎል የዓለም አቀፉ ንግድ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደገባ የተነገረ ሲሆን፥ ጦርነቱ ከተጀመረበት የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሞከሩ 26 የነዳጅ እና ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ እና የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የዴንማርክ ግዙፉ የመርከብ ማጓጓዣ ድርጅት የሆነው ሜይርስክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቪንሰንት ክሌርክ በኢራን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የዓለም ንግድ ስርዓትን እያስተጓጎለ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ከፍተኛ ገንዘብ ለደንበኞቹ እየከፈለ መሆኑን ጠቅሰው፥ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት የእቃ ማጓጓዣ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የጠቆሙ ሲሆን፥ ወሽመጡ ዳግም በአስቸኳይ ቢከፈት እንኳን የተጠራቀመው ችግር በቀላሉ እንደማይፈታ ወይም ወደ መደበኛ ሥራዎች በቀላሉ መመለስ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የመርከቦች እንቅስቃሴ የመሻሻል ሁኔታ ቢያሳይም የመድህን ዋስትና ሰጪ ኩባኒያዎች አካባቢውን በከፍተኛ የአደጋ ስጋት ደረጃ መድበው እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ ማለት ደግሞ በርካታ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፋቸውን እንደሚያቆሙ እና የጭነት ዋጋ ከፍ እንዲል ብሎም የነዳጅ ገበያዎች እንዲያሻቅቡ ማድረጉ ተገልጿል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ በየቀኑ ወደ 20 በመቶ የሚጠጋውን የዓለም ድፍድፍ ነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ በባሕር የሚያስተላልፍ እጅግ ወሳኝ የነዳጅ መተላለፊያ መስመር እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ የአሜሪካ እና የእስራኤል ሃይሎች ኢራንን ማጥቃት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በኢራን ወታደራዊ ሃይል መዘጋቱ እና ዩናይትድ ስቴትስም በበኩሏ በኢራን ወደቦች ላይ የራሷን እገዳ በመጣሏ በደርዘን የሚቆጠሩ መርከቦች ተይዘው እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው።

ምንም እንኳን አሜሪካ እና ኢራን በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ኢራን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጨምሮ በባህረ ሰላጤው ሀገራት ላይ የምትሰነዝረውን የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት የሚያስቆመውን የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን ቢያስታውቁም፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መርከቦች ብቻ የባህር ወሽመጡን ማለፍ እንደቻሉ ይገለፃል።

11 May 2026, 15:47