የሆርሙዝ ቀውስ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ድህነት ሊያስገባ እንደሚችል ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ እየጨመረ የመጣው ቀውስ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ድህነት ሊያስገባ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ረሃብ እንዲስፋፋ እና ዓለምን ወደ ድህነት ሊመራት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሐሙስ ሚያዝያ 22/2018 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት አስጠንቅቀዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት፥ በስትራቴጂያዊ ነፃ መተላለፊያ የውሃ መስመር ላይ የተጣሉ ገደቦች የነዳጅ፣ የጋዝ፣ የማዳበሪያ እና ሌሎች ወሳኝ ሸቀጦች አቅርቦትን እያደናቀፉ እንደሚገኙ እና ይህም ቀድሞውኑ ደካማ በሆነው ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ጫናውን እያባባሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ትንበያ መሠረት የመርከብ እና የንግድ መስተጓጎሎች ወዲያውኑ ቢቆሙም የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ለማስተካከል ወራትን እንደሚጠይቅ ታውቋል።
ዓለም አቀፍ ዕድገት ከ3.4% ወደ 3.1% እንደሚቀንስ፥ የዋጋ ግሽበት ወደ 4.4% እንደሚያድግ፣ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ፥ ከወረርሽኙ እና ከዩክሬን ጦርነት እያገገሙ ባሉ ኢኮኖሚዎች ላይ ጫና እንደሚጨምርም ታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ቀውሱን ለማርገብ እየሞከሩ ነው
የተባበሩት መንግሥታት የፕሮጀክት አገልግሎት ኃላፊው ለቀውሱ ምላሽ ሊሆኑ የሚችሉ የምርት ማጓጓዣ ኮሪደሮችን የሚያስስ ግብረ ኃይልን እየመሩ ሲሆን፥ ዓለም አቀፉ የባሕር ኃይል ድርጅት ደግሞ ደህንነቱ የተጠበቀ የመተላለፊያ መስመር ማግኘት ከተቻለ መርከቦችን እና ሠራተኞችን ለማሰማራት ዕቅዶችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ ታውቋል።
የኢራን ጥቃቶች፣ ዛቻዎች እና የአሜሪካ የኢራን ወደቦች እገዳ እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ከቀጠለ ችግሮች በእጅጉ እንደሚባባሱ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ግምቶች እንደሚያሳዩት፥ 32 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ድህነት ሕይወት ሊገቡ እንደሚችሉ፣ የማዳበሪያ እጥረት የሰብል ምርትን ሊቀንስ እንደሚችል፣ 45 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ እና ለዓመታት ያህል የልማት ዕድገቶች ሊቋረጡ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ዓመቱን በሙሉ የሚዘልቅ ከባድ መስተጓጎል፥ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ተፅእኖዎችን በማሳደር የኢኮኖሚ ውድቀት አደጋን እንደሚጨምር ታውቋል።
የተባበሩት መንግሠታት ዋና ኃላፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደተናገሩት፥ ችግሩ የሚያስከትለው ተጽእኖ እየተባባሰ እንደሚገኝ እና ረጅም ገደቦች ጉዳቱን አስቸጋሪ እንደሚደርጉት አስጠንቅቀዋል።
ሁሉም ወገኖች የመርከብ ጉዞ መብቶችን ወደ ነበሩበት እንዲመልሱ እና ዓለም አቀፍ የአቅርቦት መስመሮችን ለማረጋጋት የባሕር ወሽመጥን እንዲከፍቱ አሳስበዋል።
ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ቀድሞውኑ እየተስፋፋ ይገኛል
መንግሥታት የነዳጅ እና የጋዝ እጥረት እንዳለባቸው ከተናገሩ በኋላ ሐሙስ ዕለት የወጣው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 118 ዶላር አካባቢ መድረሱ ሲነገር፥ በዚህም የመጀመሪያ ተጎጂዎች ደቡብ ምሥራቅ እና ደቡብ እስያ እንደሆኑ እና የአውሮፓ አሽከርካሪዎችም ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል።
በተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓ የኢኮኖሚ ኮሚሽን፥ ቀውሱ በቅሪተ አካል ነዳጆች ላይ የተመሠረቱ ኢኮኖሚዎች ተጋላጭነትን እንደሚያጎላ ገልጾ፥ በዚህም ምክንያት አገራት ብክነትን እንዲቀንሱ፣ በተለይም በነዳጅ እና በጋዝ ተቋማት በኩል በስፋት የሚወጣው ሚቴን በመቀነስ ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረውን ሽግግር ለማፋጠን እያበረታታ እንደሚገኝ እና ይህም የአካባቢ እና የደህንነት ጥቅሞችን እንደሚሰጥ ተናግሯል።