በሁለት ዓመታት የእስራኤል ጥቃት በካን ዮኒስ የወደሙ የመኖሪያ ሕንፃዎች ፍርስራሽ እይታ በሁለት ዓመታት የእስራኤል ጥቃት በካን ዮኒስ የወደሙ የመኖሪያ ሕንፃዎች ፍርስራሽ እይታ 

የተባበሩት መንግስታት እና የአውሮፓ ህብረት ግምገማ ጋዛ 77 ዓመታትን ወደ ኋላ መቅረቷን ገለጹ

የተባበሩት መንግስታት እና የአውሮፓ ህብረት በጋራ ባወጡት መግለጫ በጋዛ ዙሪያ ያለው ሰብዓዊ እድገት በአስደናቂ ሁኔታ ለ 77 ዓመታት ወደኋላ መቅረቱን በማሳሰብ ይፋ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት በጋራ ባወጡት አዲስ የጋራ ማስጠንቀቂያ መሰረት በጋዛ ውስጥ ያለው የሰው ልጅ እድገት በግምት 77 ዓመታት ወደ ኋላ መቅረቱን እና እንደገና ለመገንባት በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከ 71 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር አጋርነት ያለው የዓለም ባንክ ‘የመጨረሻ የጋዛ ፈጣን ጉዳት እና የፍላጎት ዳሰሳ’ በሚል ባወጣው ጥናታዊ ዳሰሳ በመጀመርያዎቹ 18 ወራት ውስጥ 26.3 ቢሊዮን ዶላር አስፈላጊ አገልግሎቶችን ወደነበረበት ለመመለስ፣ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን እና ኢኮኖሚያዊ ግንባታዎችን ለመደገፍ እንደሚያስፈልግ ያለውን ግምት አስቀምጠዋል።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሃማስ የሚመሩ ታጣቂ ቡድኖች በደቡባዊ እስራኤል ላይ ካደረሱት ጥቃት በኋላ ጦርነቱ ተባብሶ ከቀጠለበት ጊዜ ወዲህ በጋዛ የደረሰው ቁሳዊ ጉዳት 35.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፥ ተጨማሪ 22.7 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ኪሳራ መድረሱን ጥናቱ ገልፆ፥ የመኖሪያ ቤቶች፣ የጤና ጥበቃ አገልግሎት፣ ትምህርት፣ ንግድ እና ግብርና በጣም ከተጎዱት ዘርፎች መካከል እንደሆኑ አመላክቷል።

ከ 371,000 በላይ ቤቶች መውደማቸውን ወይም መጎዳታቸውን፣ በአከባቢው ከሚገኙ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸው እና እያንዳንዱ ትምህርት ቤት በሚባል ደረጃ ጉዳት እንደደረሰበት ብሎው አጠቃላይ ኢኮኖሚው በ84 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።

የሰው ልጅ ሞትም እንዲሁ ከባድ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፥ የአካባቢው ባለስልጣናት ከ71,000 በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን እና ከ171,000 በላይ መቁሰላቸውን ይፋ እንዳደረጉ ጠቅሶ፥ በርካቶች አሁንም ድረስ በፈራረሱ ህንፃዎች ስር ጠፍተው እንዳልተገኙ ገልጿል።

ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ቤት አልባ መሆኑን እና 1.9 ሚሊዮን ሰዎች በተደጋጋሚ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የጠቀሰው ጥናቱ፥ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና ቀድሞውንም ለችግር የተጋለጡ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸው አመላክቷል።

ይህ ሪፖርት የቅድመ ማገገም እና የረጅም ጊዜ የመልሶ ግንባታ እቅድን ለመምራት ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር በጋዛ እና በዌስት ባንክ ከአደጋ ጊዜ እፎይታ ወደተሻለ የማገገሚያ ጊዜ ለመሸጋገር የሚያስችል ሽግግርን ለማረጋገጥ ከተከታታይ ሰብዓዊ ተግባራት ጎን ለጎን መልሶ ግንባታው መቀጠል እንዳለበት አበክሮ አሳስቧል።

29 Apr 2026, 15:50