ፈልግ

ሴት ልጆች በአፍጋኒስታን ትምህርት ቤት ውስጥ ሴት ልጆች በአፍጋኒስታን ትምህርት ቤት ውስጥ   (ANSA)

እ.አ.አ. ከ 2021 እገዳ ጀምሮ ከ 1 ሚሊዮን በላይ የአፍጋኒስታን ልጃገረዶች ትምህርት መከልከላቸው ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት - ዩኒሴፍ አዲስ ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው በአፍጋኒስታን በልጃገረዶች ላይ የተጣሉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እገዳዎች እ.አ.አ. በ 2030 ከ2 ሚሊዮን በላይ ሴት ህፃናትን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሚያስቀር ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ ይህም ለሀገሪቱ የጤና ዘርፍ፣ የሰራተኛ ሃይል እና የወደፊት የኢኮኖሚ እድገት ላይ አስከፊ መዘዞች እንደሚያስከትል አክሎ ገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ባለፉት አምስት ዓመታት ቢያንስ 1 ሚሊየን ልጃገረዶች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ በተደረጉ እገዳዎች በቀጥታ ተጎጂ መሆናቸውን በመግለጽ፥ አሁን ያሉት የእገዳ ድንጋጌዎች በሥራ ላይ ውለው ከቀጠሉ ይህ ቁጥር እ.አ.አ. በ 2030 ከ2 ሚሊዮን ሊበልጥ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ዩኒሴፍ “በአፍጋኒስታን በሴቶች ትምህርት እና የሴቶች የሠራተኛ ኃይል ተሳትፎ ላይ የተጣለው እገዳ የሚያስከፍለው ዋጋ” በሚል ርዕስ አዲስ ባወጣው ትንታኔ መሠረት እ.አ.አ. በ 2021 በሃገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እገዳ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ልጃገረዶች የመማር መብታቸውን እንደተነፈጉ የገለጸ ሲሆን፥ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “የሃገሪቱ የመንግስት ባለስልጣናት የልጃገረዶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እገዳን እንዲያነሱ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሴቶችን የመማር መብት ለመደገፍ ቁርጠኛ ሆኖ እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።

አሳዛኝ እይታዎች
በልጃገረዶች ትምህርት እና በሴቶች የሥራ ስምሪት ላይ የተጣለው እገዳ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገር እ.አ.አ. በ 2030 ከ25,000 በላይ ሴት መምህራንን እና የጤና ዘርፍ ሰራተኞችን ሊያሳጣ እንደሚችል ዩኒሴፍ ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ በ 2023 እና በ 2025 መካከል ባሉ ዓመታት ብቻ በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የሴቶች ውክልና ከ21 በመቶ ወደ 17.7 በመቶ ዝቅ ማለቱን የመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲ ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች የሰለጠኑ የሴት ባለሙያዎች ቁጥር መቀነስ የህፃናትን የመማር፣ የጤና ሁኔታ እና የወደፊት እድሎችን እንደሚጎዳ አስጠንቅቋል።

ከዚህም ባሻገር ሪፖርቱ ሴቶች እንዲሰሩ ከተፈቀደላቸው እና በጣም አስፈላጊ ከሆኑባቸው የሥራ መስኮች መገለል በቀጥታ ህፃናት ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ ይህም ሴቶች ከትምህርት ገበታ እንዲቀንሱ እንዲሁም የሴቶች እና ህፃናት እንክብካቤ እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አመላክቷል።

በእናቶች፣ በጨቅላ ህፃናት እና ታዳጊ ልጆች የጤና አገልግሎቶች ላይ ያለው ተጽእኖ
የሴት ጤና ሰራተኞች ቁጥር ማሽቆልቆል የእናቶች፣ የጨቅላ ህፃናት እና ታዳጊ ልጆችን የጤና አገልግሎቶች በቀጥታ የሚገድብ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፥ ከዚህም ባለፈ በማህበራዊ ተለምዶ ሴቶች ከወንዶች የሚያገኙትን የህክምና አገልግሎት የሚያሳጣቸው መሆኑን ዩኒሴፍ ገልጿል።

የዩኒሴፍ ዳይሬክተሯ እንደገለጹት አፍጋኒስታን ወደፊት አስፈላጊ የአገልግሎት ዘርፎችን የሚደግፉ መምህራንን፣ ነርሶችን፣ ዶክተሮችን፣ አዋላጆችን እና ማህበራዊ ሰራተኞችን ማጣት እንደማይገባት ጠቁመው፥ ‘ልጃገረዶች ከትምህርት ገበታ መገለላቸው ከቀጠለ ይህ እውነታ ይሆናል’ በማለት አሳስበዋል።

ሌላ በእውቀት የተካኑ የባለሙያዎችን ትውልድ ማጣት
የሠለጠኑ ሴት ባለሙያዎችን በማጣት መጪው ትውልድ እንዳይተካቸው እየተደረገ ባለው አሳሳቢ ተግባር ላይ ትኩረት የሰጠው የዩኒሴፍ ሪፖርት፥ ልምድ ያካበቱ ሴቶች ጡረታ ሲወጡ ወይም ሥራ ሲያቆሙ ልጃገረዶች ትምህርታቸውን እንዳይቀጥሉ እና ወደ እነዚህ ሚናዎች እንዳይገቡ እገዳ ተጥሎባቸዋል በማለት አስጠንቅቋል።

ይሄንን ችግር ለመቅረፍ እርምጃ ሳይወሰዱ ዓመታት ባለፉ ቁጥር አፍጋኒስታንን ሌላ በእውቀት የተካኑ የባለሙያዎችን ትውልድ የማጣት ዋጋ እንደሚያስከፍል ያስጠነቀቀው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ሪፖርት፥ ይሄንን ተግዳሮት ለመጋፈጥ ዩኒሴፍ የሴቶችን የሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርት መብቶች ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና በአፍጋኒስታን የጤና፣ የትምህርት እና ኢኮኖሚያዊ የወደፊት ጊዜ ውስጥ ጉልህ ሚና ባለው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ እንዲቻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህም ባለፈ በሪፖርቱ የአፍጋኒስታን ልጃገረዶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዳይማሩ መከልከሉ ልጃገረዶችን፣ ቤተሰባቸውን እና ማህበረሰባቸውን ወደ ድህነት በመግፋት፣ የጤና ዘርፍ ግብዓቶችን በማዳከም እና የተማረ የሴቶች ትውልድ ሊያቀጣጥል የሚችለውን የኢኮኖሚ ሞተር ጸጥ በማድረግ የመላውን ሃገር አቅም እንደሚያሳጣ ተገልጿል።

የዩኒሴፍ ቁርጠኝነት
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ኤጀንሲ ዩኒሴፍ የእያንዳንዱን ህፃን መብት በሁሉም ቦታ በተለይም በጣም የተቸገሩ ህፃናትን እና ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ በሆኑባቸው ከ190 በላይ በሆኑ ሀገራት እና ግዛቶች ውስጥ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ምንም እንኳን የተለያዩ እገዳዎች ቢኖሩም የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲው በአፍጋኒስታን የህፃናትን ትምህርት መደገፉን እንደቀጠለ ተገልጿል።

እ.አ.አ. በ 2025 ዓ.ም. ብቻ ከ 3.7 ሚሊዮን በላይ በህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ህፃናት የአደጋ ጊዜ ድጋፍ ማግኘታቸው እና 66 በመቶዎቹ ሴቶች የሆኑበት 442,000 ህፃናት በማህበረሰብ አቀፍ የመማር ማስተማር ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸው እንዲሁም 232 ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው ተገልጿል።

30 Apr 2026, 13:04