ኢኳቶሪያል ጊኒ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ጉብኝት በተስፋ ስትጠብቅ እንደነበር ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በምዕራብ አፍሪካ ከምድር ወሽመጥ በስተሰሜን፣ በጊኒ ባሕረ ሰላጤ ሞቃታማ አከባቢ በእሳተ ገሞራ በተከበበው ውሃ ዳር የቢዮኮ ደሴት ላይ የምትገኘው ኢኳቶሪያል ጊኒ አብዛኛው መልክአ ምድሯ በተራሮች እና በሞቃታማው ዝናባማ ደን የተሸፈነ ሲሆን፥ የኢኳቶሪያል ጊኒ ጥንታዊ ከተማ እና እስከ ባለፈው ታህሳስ ወር ድረስ የደሴቱ ዋና ከተማ ማላቦ መሆኑ ይታወቃል።
ማክሰኞ ሚያዚያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአራት የአፍሪካ ሃገራት እያደረጉት ለሚገኘው ሃዋሪያዊ ጉብኝታቸው አራተኛ መዳረሻ እና የመጨረሻ ወደሆነችው የኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ እንደሚገቡ የሚታወቅ ሲሆን፥ ሃገሪቷ እ.አ.አ. ከ1982 ወዲህ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመጨረሻ ጊዜ ከተጎበኘች ወዲህ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት በሃገሪቷ ውስጥ በመገኘቱ በብዙ መልኩ አጠቃላይ ለውጥ ያመጣች ሀገር ሆና እንደምትጠብቃቸው ተነግሯል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ በነፍስ ወከፍ ገቢ ከአፍሪካ እጅግ ባለጸጋ ከሚባሉት ሃገራት አንዷ መሆኗ የሚነገር ሲሆን፥ ይህ አዲስ የተገኘው የነዳጅ ሀብት ያመጣው ለውጥ ማላቦ ከተማ በሚገኘው ከፍተኛ ውበት ባለው እና በዘመናዊው አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ፥ በቅርቡ ለብፁዕነታቸው ሃዋሪያዊ ጉብኝት ክብር ሲባል ‘ሊዮ 14ኛ ዩኒቨርሲቲ’ ተብሎ እስከተሰየመው ከፍተኛ የትምህርት ተቋምን ጨምሮ በከተማው ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ውበት የሚገለጽ መሆኑ ይነገራል።
በሌላ መልኩ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በኢኳቶሪያል ጊኒ ጉብኝታቸውን ካደረጉ በኋላ ሃገሪቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣች መሆኑ የሚነገር ሲሆን፥ በኢኳቶሪያል ጊኒ የተገኘው የነዳጅ ዘይት ሀብት እጅግ በጣም ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ እንደሚከፋፈል እና ድህነት አሁንም ድረስ በእጅጉ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
በማላቦ ሃገረ ስብከት የሃዋሪያዊ ሥራዎች አስተባባሪ የሆኑት አባ ጆሴ ንዶንግ በአከባቢው በርካታ ችግሮች መኖሩን ገልጸው፥ ነገር ግን “የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት እኛ እንደ ክርስቲያኖች እንድንቀጥል የተወሰነ ድፍረት እና ጥንካሬ ይሰጠናል” ብለዋል።
አባ ጆሴ ከድህነት፣ ከፖለቲካዊ ችግሮች እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የበርካታ ብሄረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ አንዳንድ ጊዜ ህዝቡን ግጭት ውስጥ ከሚያስገባው ከ“ጎሳ ተኮር” አስተሳሰቦች ችግር በተጨማሪ፥ የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን እና ምዕመናንን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚያፈናቅለውን መመሠረታዊውን የ“መናፍቃን” አስተሳሰብ ያስከተለውን ጉዳት በአጽንዖት ገልጸዋል።
ሆኖም ግን አብዛኛው የኢኳቶሪያን ጊኒ ህዝቦች የካቶሊክ እምነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም በማዕከላዊ ማላቦ በሚገኘው በቅድስት ኤልሳቤጥ ካቴድራል በቅዳሴ፣ በአምልኮና በዝማሬ፣ በኋላም ምሽት ላይ በተደረገው የቅዱስ ቁርባን ስግደት እምነታቸውን በገሃድ ማሳየታቸው ተገልጿል።
“በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚታየው ሃይማኖታዊ ሕይወት በጣም ግልጽ ነው” ያሉት በክላሬት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና መምህር የሆኑት አባ ዳዮስዳዶ ሎሬንሶ በበኩላቸው፥ “በአገልግሎቶች ጊዜ ሰዎች ደስታቸውን፣ ሀዘናቸውን፣ መከራቸውን፣ ተስፋቸውን ከጌታ ጋር ለመካፈል ዝግጁ መሆናቸውን” አስረድተዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉብኝትን አስመልክቶ ከማላቦ ነዋሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት ለመጨረሻ ጊዜ በብዛት የተሰማው ቃል ‘ተስፋ’ የሚል መሆኑን ያስታወሱት ካህኑ፥ ሃገሪቷ ውስጥ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም፥ ነገር ግን “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች፣ እምነታችንን እና ተስፋችንን ልናጣ አይገባም” ያሉ ሲሆን፥ በመጨረሻም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ይሄንን ተስፋ ለመጠበቅ እንደሚረዳ በመግለጽ አጠቃለዋል።