በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ህፃናት እየተጎዱ መሆኑን ዩኒሴፍ ገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባቀረበው ጥሪ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረው ግጭት እንዲቆም ግፊት ማድረግ እንደሚገባ፥ እንዲሁም በኢራን እና በሊባኖስ ለተፈናቀሉ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ህፃናት አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲው ምክትል ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ቴድ ቻይባን ይሄንን አስመልክቶ እንደተናገሩት፥ ‘በመካከለኛው ምስራቅ አንድ ትውልድ ወደ ከፍተኛ ቀውስ መግባቱን’ ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት "አስከፊ ዋጋ" እየከፈለ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ወላጆች፣ አያቶች፣ መምህራን እና መላው ቤተሰብ
ዩኑሴፍ ሰኞ ዕለት ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባቀረበው አጭር መግለጫ ላይ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከሶስት ሳምንታት በፊት ጀምሮ በኢራን ውስጥ የተገደሉትን 206 ህፃናት እንዲሁም በሊባኖስ ደግሞ 118 ህፃናትን ጨምሮ ከ2,100 በላይ ህፃናት መሞታቸው ወይም መቁሰላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፥ ቴድ ቻይባን በመግለጫው ጦርነቱ እያስከተለ ያለውን የሰብአዊ ጉዳት አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ “ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ወላጆች፣ አያቶች፣ መምህራን፣ ወንድሞች እና እህቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም ምክንያት የአከባቢው ማህበረሰቦች፣ ከተሞች እና ሃገራት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መኖራቸውን አመላክተዋል።
“ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ወላጆች፣ አያቶች፣ መምህራን፣ ወንድሞች እና እህቶች አሉ። ማህበረሰቦች፣ ከተሞች እና ሃገራት በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ናቸው”
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች
ከሞቱት እና ከቆሰሉት ሰዎች በተጨማሪ ‘ባለማቋረጥ በሚፈጸመው የቦምብ ድብደባ’ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁሉም የከተማ አከባቢዎች እየተሰደዱ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው፥ ይሄንን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር እንደገለጹት በኢራን 3.2 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፥ ከእነዚህም ውስጥ 864,000 የሚደርሱ ህፃናት እንደሚገኙበት የገለጹ ሲሆን፥ በሊባኖስ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን፤ ከእነዚህም ውስጥ 370,000 የሚጠጉ ህፃናት እንደሚገኙበት አመላክተዋል። ከዚህም ባሻገር ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 90,000 የሚጠጉ የሶሪያ ስደተኞች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን ወደ ሶሪያ ለመመለስ መገደዳቸውን ጠቅሰው፥ ይህ ግጭት ከመባባሱ በፊት በመካከለኛው ምስራቅ ወደ 44.8 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ይኖሩ እንደነበር እና አሁን እየተከሰተ ያለው ነገር ለህፃናቱ አስከፊ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ክፍተትን ማጥበብ
የዩኒሴፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚው በመግለጫው የተለያዩ ህፃናት የሚረዱባቸው በርካታ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መጎዳታቸውን ወይም መውደማቸውን ገልጸው፥ ምንም እንኳን በምግብ፣ በውሃ እና በመድኃኒት እንዲሁም በጤና አገልግሎት አቅርቦት ላይ እየተከናወ ያለ የሰብዓዊ ምላሽ ቢኖርም፥ አሁን ያለው የእርዳታ ግብአት በፍጥነት እያደጉ ያሉትን ፍላጎቶች ለማሟላት በቂ እንዳልሆነ አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ በተለይም በአደጋ ጊዜ ጥሪው ውስጥ ያለው የገንዘብ ድጋፍ ክፍተት 86 በመቶ መድረሱ አሳሳቢ መሆኑን አስረድተዋል።
አስቸኳይ የተግባር ጥሪዎች
አቶ ቴድ ቻይባን በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ለደረሰባቸው ህፃናት ሲባል አስቸኳይ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲደረግ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት እንዲኖር እና ተጨማሪ አደጋን ለመከላከል የእርዳታ ጥረቶችን ለማገዝ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እ.አ.አ. በ1946 ዓ ም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ህፃናት እና እናቶች የሰብአዊ እና የልማት እርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ሲሆን፥ በህፃናት ጤና፣ በአመጋገብ፣ በትምህርት እና በሰብዓዊ ጥበቃ ላይ በማተኮር ከ190 በላይ በሆኑ ሃገራት ውስጥ እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።