ፈልግ

በወሮ፣ ቋራ ግዛት ውስጥ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በፍርስራሹ ውስጥ አንድ የአከባቢው ነዋሪ ቆሞ በወሮ፣ ቋራ ግዛት ውስጥ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በፍርስራሹ ውስጥ አንድ የአከባቢው ነዋሪ ቆሞ   (AFP or licensors)

በመላው ናይጄሪያ የተከሰተው ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነገረ

በናይጄሪያ የተከሰተው ጥቃት በሰሜናዊ ምዕራብ እና ሰሜናዊ ማዕከላዊ ክልሎች ውስጥ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት አስተዋጽዖ ማድረጉ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሰሜን-ማዕከላዊ ናይጄሪያ፣ በቤንዌ ግዛት ውስጥ አርብ ዕለት በማህበረሰብ ገበያ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 13 ሰዎች መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህ በገጠራማ አካባቢዎች ከተፈጸሙት ተከታታይ ጥቃቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

ታጣቂዎች ዒላማ ያደረጉት ምባኪዮር ከተማ፣ በካዋንዴ የአካባቢ አስተዳደር ውስጥ በሚገኘው የአንዋሴ ገበያ ላይ ሲሆን፥ ታጣቂዎቹ የአካባቢው ሴቶችን አግተው ከወሰዱ በኋላ ድንኳኖችን ማቃጠላቸው ተነግሯል።

አንዳንድ የዓይን እማኞች እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ በአቅራቢያው ካለው ተራራማ ስፍራ ውስጥ ወጥተው ጥቃቱን የፈጸሙት የገበያ ቦታው በጣም በተጨናነቀበት ወቅት እንደነበረ የገለጹ ሲሆን፥ ታጣቂዎቹ የገበያ ቦታውን ከመቆጣጠራቸው በፊት ወደ ላይ ሲተኩሱ እንደነበርም ገልጸዋል።

ይህ ጥቃት የተከሰተው ከሁለት ቀናት በፊት በአባንዴ ማህበረሰብ ላይ በተፈፀመው ከባድ ጥቃት በትንሹ 17 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ እንደሆነ እና ይህም በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል።

የክልሉ እና የፌደራል ባለስልጣናት የጸጥታ ስራዎችን እንዲያጠናክሩ እና የገጠር ሰፈራዎችን ከተደጋጋሚ ጥቃት እንዲጠብቁ ነዋሪዎች ደጋግመው ማሳሰባቸው ተነግሯል።

ባለፈው ወር መገባደጃ ጥር 26 ላይ የታጠቁ ቡድኖች በኳራ ግዛት ውስጥ ባሉ ሁለት መንደሮች ላይ ጥቃት ሰንዝረው በርካታ ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ አስከሬኖች በመገኘታቸው ምክንያት የሟቾች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

ብዙ ተጎጂዎች በቅርብ ርቀት ላይ በጥይት እንደተመቱ እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችና ሱቆች በመቃጠላቸው ነዋሪዎች በአካባቢው ወደሚገኝ ጫካ ለመሸሽ እንደተገደዱ ተገልጿል።

በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምዕራብ እና ሰሜን ማዕከላዊ ክልሎች ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት መስፋፋት ለከፋ ሰብአዊ ቀውስ አስተዋጽዖ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች እንዲፈናቀሉ እንዲሁም ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት እንዲጨምር ማድረጉ ተገልጿል።

09 Feb 2026, 14:26