በደቡብ ሱዳን ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት በምግብ እጥረት ስጋት ውስጥ መሆናቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት - ዩኒሴፍ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ተጠናክሮ በቀጠለው ግጭት ምክንያት ከ450,000 በላይ ህፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የገለጸ ሲሆን፥ በጆንግሊ ግዛት በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የጅምላ መፈናቀል እና ወሳኝ የጤና እና የአመጋገብ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ማድረጉን ተቋሙ አመላክቷል።
ለህፃናት አደገኛ ሁኔታ
ዩኒሴፍ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ከጎረጎሳዊያኑ 2026 መጀመሪያ ጀምሮ በጆንግሌይ ግዛት ውስጥ እየተባባሰ በመጣው ግጭት ምክንያት ወደ 250,000 የሚጠጉ ሰዎች በተለይም ከሰሜን እና መካከለኛው የግዛቱ ክፍሎች መፈናቀላቸው ተገልጿል።
በሀገሪቱ የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ኖአላ ስኪነር በጥቃቱ በቀጥታ ለተጎዱ ሴቶች እና ህፃናት ድርጅታቸው ያለውን ጥልቅ ስጋት ገልጸው፥ በእነዚህ አካባቢዎች በህፃናት ላይ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መኖሩን እንደሚያውቁ የጠቀሱ ሲሆን፥ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናት ምንም ዓይነት ህክምና ካልተደረገላቸው የመሞት እድላቸው በ 12 እጥፍ እንደሚጨምር እናውቃለን ሲሉ ስኪነር ተናግረዋል።
የዩኒሴፍ ተወካይዋ ባለድርሻ አካላት ግጭቱን እንዲያቆሙ እንዲሁም “ፈጣን፣ እንቅፋት የሌለበት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የሰብአዊ እርዳታ እና ሰራተኞች በጣም ተጋላጭ የሆኑ ተፈናቃይ ቡድኖች ጋር እንዲደርሱ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።
አፋፍ ላይ ያለ ሥርዓት
ከዚህም በላይ ግጭቱ የአደጋ ጊዜ ዕርዳታ አቅርቦትን በእጅጉ የገደበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በወንዝ፣ በአየር እና በመንገድ ላይ በሚደረጉ የጉዞ ገደቦች ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን መድረስ እንዳልቻሉ ተነግሯል።
በጆንግሌይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ስድስት አውራጃዎች የምግብ አቅርቦት እንዳለቀባቸው ወይም እያለቀባቸው እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፥ እነዚህ የምግብ አቅቦቶች በአከባቢው ለሚገኙ በርካታ የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው ህፃናት እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ተገልጿል።
ዩኒሴፍ በሪፖርቱ በመላ ሀገሪቱ ወደ 17 የሚጠጉ የጤና ተቋማት በመዘጋታቸው ምክንያት ተጓዳኝ የአመጋገብ አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጉን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በጆንግሌይ ግዛት እና በተለያዩ አከባቢዎች 10 የጤና እና የምግብ አቅርቦት ተቋማት መዘረፋቸው ተገልጿል።
ዩኒሴፍ በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፍ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለመድረስ አስቸጋሪ ቢሆንም የውሃ ማጣሪያ መሳሪያዎችን፣ ባልዲዎችን እና ሳሙናዎችን ወደ ጁንግሌይ ግዛት፣ ዱክ አውራጃ በመላክ ለችግሩ ምላሽ እየሰጠ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር የኮሌራ ወረርሽኝ ስጋት መኖሩ እና በጆንግሌይ ግዛት አኮቦ ከተማ ከ10,000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የወባ ህክምና መድሀኒቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው ህፃናት ምግብ እና የአደጋ ጊዜ የጤና ቁሳቁሶችን ወደ አከባቢው መላኩ ተገልጿል።