ፈልግ

ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች  (AFP or licensors)

ሰሞኑን በስደተኞች ላይ በተከሰተው አደጋ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መጥፋታቸው ተነገረ

አንድ የጣሊያን የእርዳታ ቡድን እንዳስታወቀው በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ በተከሰተው ከባድ አውሎ ንፋስ ወቅት ብዙ ጀልባዎች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር እና በደረሰው አደጋ በርካታ ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ ገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ‘ሳይክሎን ሃሪ’ የተሰኘው አውሎ ንፋስ ባስከተለው ከባድ የአየር ሁኔታ 1,000 የሚደርሱ ስደተኞች መሞታቸው ወይም መጥፋታቸው እየተነገረ የሚገኝ ሲሆን፥ ‘ሜዲቴራኒያ ሴቪንግ ሂውማንስ’ የተሰኘ የጣሊያን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከአደጋው የተረፉት ሰዎችን ምስክርነት እና ይፋዊ ማስጠንቀቂያዎችን በማጣቀስ ሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ አውሎ ነፋሱ አካባቢው ላይ ባደረሰው አደጋ በርካታ ጀልባዎች መስመጣቸውን ገልጿል።

የእርዳታ ቡድኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት ላውራ ማርሞራሌ የአየር ሁኔታው በተከሰተበት ወቅት ለፍለጋ እና ለነፍስ አድን ፍላጎቶች በቂ ምላሽ አልሰጡም በሚል የጣሊያንን እና የማልታ ባለስልጣናትን አጥብቀው ያወገዙ ሲሆን፥ ድርጅቱ የጠፉትን ሰዎች አሃዝ ግምቱን የገለፀው በሊቢያ እና በቱኒዝያ ከሚገኙ የስደተኞች ትስስር በኩል በሁለቱም ሀገራት ከሚገኙ የስደተኛ ማህበረሰቦች ባሰባሰበው አዳዲስ ምስክርነቶች እንደሆነ ገልጿል።

እነዚህ ዘገባዎች የአውሮፓ ባለሥልጣናት እስካሁን ካወጡት የበለጠ አስቸጋሪ ሁኔታን መኖሩን ያመለክታሉ የተባለ ሲሆን፥ አውሎ ነፋሱ በአካባቢው ላይ ጉዳት ባደረሰበት ወቅት በርካታ ጀልባዎች ከቱኒዚያ ስፋክስ ከተማ ለቀው መውጣታቸውን እና በርካቶቹ ወደ መድረሻቸው ሳይደርሱ እንደጠፉ ተገልጿል።

ሃሪ የተሰኘው አውሎ ነፋስ ማዕከላዊ ሜዲትራኒያንን በመታበት ወቅት የተለያዩ ጀልባዎች ጉዞ ላይ እንደነበሩ እና አውሎ ንፋሱ በሰዓት ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ ፍጥነት እንደነበረው፣ እንዲሁም ከሰባት ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸውን ማዕበሎች መከሰታቸውን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።

የሮማ የባህር ላይ የህይወት አድን ማስተባበሪያ ማዕከል በላከው ይፋዊ መረጃ መሰረት እስከ ጥር 16 ድረስ ቢያንስ 380 ሰዎች በባህር ላይ መጥፋታቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ይህ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የአውሮፓ የባህር ኃይል ባለስልጣናት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት ተጨማሪ ይፋዊ መግለጫዎችን እንዳልሰጡ አስታውቋል።

በጣም አስከፊ ገጽታ
ከዚህም በተጨማሪ ይህ መንግስታዊ ያልሆነ የህይወት አድን ድርጅት እንደገለጸው አኃዙ በግል ምስክርነቶች እና በመካሄድ ላይ ያሉ ምርመራዎች የተገለጠውን እውነታ በእጅጉ አሳንሶ እንደሚያሳይ የጠቆመ ሲሆን፥ በርካታ ጀልባዎች ያለምንም ዱካ በተሰወሩበት በአሁኑ ወቅት ቤተሰቦች የጠፉባቸውን ሰዎች እየፈለጉ እንደሆነ ተነግሯል።

አንድ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ግለሰብ እያንዳንዳቸው ከ50 እስከ 55 የሚደርሱ ተሳፋሪዎችን የያዙ አምስት ጀልባዎችን ልኮ እንደነበር መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ከቱኒዚያዋ ስፋክስ ከተማ በስተደቡብ ከሚገኙ አከባቢዎች በርካታ ሰዎች ተነስተው እንደነበር እና አብዛኛዎች እንደጠፉ ከአከባቢው ማህበረሰብ የተገኙ ምንጮች ማመላከታቸው ተገልጿል።

ጥር 14 አንድ ጀልባ ብቻ አንድ ሬሳ ይዛ ወደ ላምፔዱሳ ወደብ መድረሷ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው መንትያ ህፃናት በባህር ላይ መጥፋታቸው እና በቅርብ ቀናት ውስጥ የማልታ ባለሥልጣናት እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ አስከሬኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ ማግኘታቸው ተገልጿል።

ሰብዓዊነት ላይ የሚሰሩ አካላት ሁኔታውን "ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አሳዛኝ" ክስተት በማለት የገለጹት ሲሆን፥ የሰብዓዊ ተቋማቱ እውነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቀው፥ የፍለጋ እና የማዳን ስራዎችን ለማሻሻል እና ተጨማሪ የህይወት መጥፋትን ለመከላከል ውጤታማ ምላሾችን ለማረጋገጥ ባለስልጣናት አፋጣኝ የሆነ ወሳኝ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

04 Feb 2026, 13:32