የኢራንን  የኢስፋሃ ኒውክሌር ማበልጸጊያ ጣቢያን የሚያሳይ የካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የተለቀቀ የሳተላይት ምስል የኢራንን የኢስፋሃ ኒውክሌር ማበልጸጊያ ጣቢያን የሚያሳይ የካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የተለቀቀ የሳተላይት ምስል  

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በዋሽንግተን ስለ ኢራን የኒውክሌር ስምምነት መወያየታቸው ተነገረ

የእስራኤል - ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም እስራኤል ጋዛ ላይ በምትፈጽመው ጥቃት በርካቶች እየሞቱ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ስለሚኖረው ስምምነት ለመወያየት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን ዋይት ሀውስ ጋብዘው መወያየታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋይት ሀውስ መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፥ የእስራኤሉ መሪ አስተዳደራቸው ከኢራን ጋር ጠንከር ያለ ስምምነት እንዲፈጽም ፍላጎቱ እንዳላቸውም ተገልጿል።

የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለስልጣናት እንዳሉት ኔታንያሁ የኢራንን የዩራኒየም ማበልጸጊያ ከማስቆም ባለፈ የባለስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሟን እና እንደ ሃማስ እና ሂዝቦላ ላሉ ቡድኖች የምትሰጠውን ድጋፍ የሚገድብ ስምምነት እንዲደረግ ትራምፕ ላይ ጫና ያሳድራሉ ተብሎም ሲጠበቅ እንደነበረ ይታወቃል።

ኢራን የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ከመፈለግ አንፃር የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን ለመገደብ ፈቃደኛ መሆኗን ብታሳይም ሰፋ ያሉ ገደቦችን ግን ውድቅ ማድረጓ ተነግሯል።

ይህ ጉብኝት ትራምፕ ወደ ስልጣን ዳግመኛ ከተመለሱ በኋላ ኔታንያሁ ወደ አሜሪካ ያደረጉት ስድስተኛ ጉዞ እንደሆነ ተነግሯል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ የቅርብ አጋር የሆኑት ኔታንያሁ ኢራን ለእስራኤል የህልውና ስጋት እንደሆነች ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን፥ ዋሽንግተን ቴህራን ላይ ተጽእኖ እንድታሳድር ደጋግመው መጠየቃቸውም ይታወቃል።

ዌስት ባንክ እና ጋዛ
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ደካማ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም ባለፉት ሳምንታት በጋዛ በደርዘን የሚቆጠሩ ሲቪሎች መሞታቸውና መቁሰላቸው፣ በዌስት ባንክም መፈናቀሉ መቀጠሉን የሰብዓዊ ኤጀንሲዎች አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ማህበረሰቦች የአደጋ ጊዜ ቡድኖችን ማግኘት እንዳልቻሉ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከጥር 12 እስከ 25 ባሉት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ 50 በላይ ጥቃቶች መሰንዘራቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዌስት ባንክ ውስጥ የእስራኤል ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመሩ እና ጥቃቱ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ውድመት ማስከተሉ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) እንደገለጸው ከ900 በላይ ፍልስጤማውያን በጎረጎሳዊያኑ 2026 መጀመሪያ ጀምሮ በሰፋሪዎች ጥቃት እና የመግቢያ ገደቦች ምክንያት ከቤታቸው ወይም ከማህበረሰባቸው ለመሰደድ እንደተገደዱ ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ማስተባበሪያ ቢሮው ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት በደረሰው ጉዳት እና ሰብአዊ ፍላጎቶች ላይ ቅድመ ግምገማ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

13 Feb 2026, 13:53