ፈልግ

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት 

ጉቴሬዝ ‘የስልጣን ህግ የህግ የበላይነትን የሚተካ ከሆነ ዓለም የተረጋጋች አትሆንም’ ማለታቸው ተነገረ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከጣሊያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ በሆነው ‘ላ ሪፐብሊካ’ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ያደረጉ ሲሆን፥ ጉተሬዝ በቆይታቸው ዓለማችን አሁን ያለችበትን አሁናዊ ጉዳዮች በማንሳት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የስልጣን ህግ የህግ የበላይነትን ሲተካ ውጤቶቹ በጣም አሳሳቢ ናቸው” ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጡት መላውን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሳበውን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መክፈቻ ላይ ለመገኘት ጣሊያንን በጎበኙበት ወቅት ከላ ሪፐብሊካ ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ሲሆን፥ ይህ የኦሎምፒክ ውድድር በታሪክ የውይይት፣ የመደመር እና የሰላም ዕድል ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፥ ነገር ግን ጉተሬዝ በጎረጎሳዊያኑ 2026 ቅድሚያ በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ‘በግጭት፣ ጥፋተኛን ያለመቅጣት፣ የእኩልነት መጓደል እና ሊተነበይ የማይቻልበት ዓለም ውስጥ ነን’ ማለታቸው ይታወሳል።

እራስን የሚከላከል ጂኦፖለቲካዊ መለያየት ያለበት ዓለም የዓለም አቀፍ ህግን በጅምላ በመጣስ እና የልማት እና የሰብአዊ እርዳታ ጥረቶችን ማስቆም ሲሆን፥ እነዚህ ሃይሎች እና ሌሎችም አካላት የዓለም አቀፋዊ ትብብርን እና የድጋፍ መሰረቱን እየፈተኑት እንደሆነ ይታወቃል፥ ዓለም አቀፍ ትብብር በጣም በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት ይሄንን ለመጠቀም እና ኢንቨስት ለማድረግ በጣም ትንሽ ዝንባሌ ያለን ስለሚመስል በእርሳቸው አስተያየት የዚህ አዝማሚያ ዋና መንስኤዎች እና መፍትሄዎቹ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የተጠየቁት ጉተሬዝ፥ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኦሎምፒክ ሰላምን እና የዓለም አቀፍ ህግን እንዲሁም የዓለም አቀፍ ትብብርን የሚያመለክት ጥሩ ወቅት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ጣሊያን የጥንቱን የኦሎምፒክ ስምምነትን እንደ ሃይለኛ የሰላም ምልክት አድርጋ በማደስ ላሳየችው መሪነት ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል።

ለጣሊያን አነሳሽነት ምስጋና ይግባውና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በሚላን-ኮርቲና በተካሄደው የ2026 ኦሎምፒክ እና ፓራኦሊምፒክ የክረምት ጨዋታዎች ወቅት ሀገራት የኦሎምፒክ የሰላም ስምምነትን እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወሱት ጉተሬዝ፥ ይህ በመከፋፈል ጊዜ እንኳን የሰው ልጅ በጋራ እሴቶች ዙሪያ ሊተባበር እንደሚችል የሚያሳይ ጠንካራ ማሳሰቢያ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ስፖርት መለያየት ባለበት ስፍራ ድልድይ ለመሆን እና ትብብርን ለማነሳሳት ልዩ ችሎታ እንዳለው እና በዘንድሮው ጨዋታዎች ጣሊያን ይህንን መንፈስ በመቀበሏ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እነዚህ ተግዳሮቶች እርስ በርስ ተያያዥነት ካላቸው በርካታ ነገሮች ላይ የተመሰረቱ እንደሆኑ የጠቀሱት ሃላፊው፥ ዛሬ በምንገኝበት ጂኦፖለቲካ ውስጥ የግድየለሽነት እርምጃዎች አደገኛ የሆኑ ምላሾችን እንደሚያስነሱ የገለጹ ሲሆን፥ ያለመከሰስ መብትን እንደሚያባብስ፣ የእኩልነት መጓደል ማህበረሰቦችን እንደሚያናጋ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን፣ ሰደድ እሳትን እና የባህር ከፍታ መጨመርን እንድሚያስነሳ ብሎም መቆጣጠሪያ ዘዴ ከሌለው ቴክኖሎጂ አለመረጋጋትን እንደሚያስከትል ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የዓለም አቀፍ ህግጋትን እና ደንቦችን መጣስ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ተአማኒነት እንደሚያዳክም፥ ይህም ጉልበት ያላቸው አካላት ህገወጥ የሆነ ድርጊትን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የሚያሳይ አደገኛ ምልክት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ለልማት እና ለሰብአዊ እርዳታ የሚውለው መዋዕለ ንዋይ መቀነስ እነዚህን ቀውሶች የበለጠ በማዋሃድ ህዝቡን ለረሃብ፣ ለመፈናቀል እና ለግጭት እንደሚያጋልጥ ጠቁመዋል።

የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የአየር ንብረት ቀውስን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ልዩ መድረክ እንደሆኑ የጠቆሙት ጉተሬዝ፥ የአየር ንብረት ለውጥ የመጪውን የክረምት ስፖርቶች በቀጥታ አደጋ ላይ እንደሚጥል፥ አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ በአሁኑ ወቅት የክረምት ዝግጅቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችሉ ከ 90 በላይ የሆኑ አካባቢዎች በጎረጎሳዊያኑ 2080 ወደ 30 ሊወርድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የስፖርትን እና የምድራችንን የወደፊት ሁኔታ ለመጠበቅ ከፓሪስ ስምምነት፣ ከ2030 አጀንዳ እና ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በሚስማማ መልኩ የሙቀት መጨመርን ለመገደብ ሁሉም መንግስታት ቆራጥ የሆነ የጋራ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ሃላፊው፥ ውድድሩ መንግስታትን፣ አትሌቶችን እና ዜጎችን ሊያንቀሳቅስ እንደሚችል እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ለሰላም ጥረቶች እና ለአየር ንብረት ለውጥ እውነተኛ ውጤቶችን እንደሚያመጣ ጠቅሰው፥ ኦሎምፒክ ሰላምን፣ ዓለም አቀፍ ህግን ማክበርን እና ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚያመላክት ጥሩ ማሳያ እንደነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ጉተሬዝ በቅርቡ “የህግ የበላይነት በስልጣን ህግ መተካት አለበት ብለው የሚያምኑ አሉ” ማለታቸውን ተከትሎ ምን ማለት ፈልገው እንደሆነ ለቀረበላቸው እና ማንኛውም ሰው ዩናይትድ ስቴትስ አሁን የምትከተለውን ፖሊሲ ሲመለከት የባለብዙ ወገን መፍትሄዎች አግባብነት እንደሌለው እና ዋናው ነገር የስልጣን አጠቃቀም እንደሆነ እንደሚረዳ፥ እንዲሁም ይህ ባህሪ ለዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት የሚያስከትለው መዘዝ እና አደጋ ምን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ የተረጋጋ ዓለም እንዲኖረን ከፈለግን ብሎም ሰላም የሰፈነበት፣ ልማት የተስፋፋበት እና የጋራ እሴቶቻችን የሚጠበቁበት ዓለም ለመገንባት በግጭት ሳይሆን በትብብር ላይ የተመሰረተ ብዝሃነትን መደገፍ እንደሚገባ መክረው፥ የስልጣን ህግ የህግ የበላይነትን ሲተካ ውጤቶቹ የከፉ እንደሆነ አመላክተዋል።

ያለመከሰስ መብት ግጭቶችን እንደሚያስነሳ እና አለመተማመንን እንደሚያሰፋ፥ ይህም አጥፊዎች ውጥረቶችን እንዲጠቀሙ እና ያለ ተጠያቂነት እርምጃ እንዲወስዱ እንደሚያስችላቸው ጠቅሰው፥ የባለብዙ ወገን ትብብር መዳከሙን እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለችግሮች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት መቸገራቸውን አመላክተዋል።

ኃያላን መንግሥታት ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ይልቅ ተፅዕኖን ሲያስቀድሙ፣ ሕግን መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ሥርዓትን ተአማኒነት እንደሚያሳጡ የገለጹት ጉተሬዝ፥ ይህም መመሪያዎች እና ደንቦች ሊጣሱ እንደሚችሉ አደገኛ መልእክት እንደሚያስተላልፍ እና በአገሮች መካከል መተማመንን እንደሚያስወግድ፣ የአንድ ወገን እርምጃዎችን እንደሚያበረታታ እንዲሁም ግጭትን፣ አለመረጋጋትን እና የሰዎችን ስቃይ እንደሚጨምር አብራርተዋል።

ጉተሬዝ ዓለም አቀፍ ህግ እንዲሁም ሊተነበይ የሚችል ባህሪ እና የጋራ ትብብር ከሌለ ዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት ሊመጣ እንደማይችል አመልክተው፥ ጠንካራ፣ አካታች፣ በጋራ ኃላፊነት እና እሴቶች ላይ የተመሰረቱ የባለብዙ ወገን ተቋማት ግጭቶችን ለመቆጣጠር፣ የኢፍትሃዊነት ችግሮችን ለመፍታት፣ ለሰብአዊ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የተባበሩት መንግስታት ቻርተርን መርሆዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

በጎረጎሳዊያኑ 2026 ዓመት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ጉተሬዝ ባደረጉት ንግግር የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ምዕራፍ ሁለት መጀመሩን በደስታ መቀበላቸውን፥ ነገር ግን ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች የተቋቋመውን የሰላም ቦርድን ለተባበሩት መንግስታት ቀጥተኛ ፈተና አድርገው እንደሚመለከቱት፥ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ትራምፕ እራሳቸው ይህ የሰላም ቦርድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ሊተካ ይችላል ማለታቸውን ተከትሎ በዚህ ጉዳይ ያላቸውን ሃሳብ የተጠየቁት ጉተሬዝ፥ የፀጥታው ምክር ቤት በተለይ ከጋዛ ጋር የተያያዘውን የውሳኔ አንቀጽ 2803 ን ማጽደቁን አስታውሰው፥ ይህ የውሳኔ ሃሳብ የሰላም ቦርዱን እና ሌሎች አካላትን ጨምሮ በርካታ ሚናዎችን እና ኃላፊነቶችን ያስቀመጠ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆኑ አስፈላጊ እንደሆነ እና ሁሉም ወገኖች እንዲታዘዙት መክረው፥ ሁሉም ጥረቶች በተባበሩት መንግስታት ውሳኔዎች እና በዓለም አቀፍ ህግ መመራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በጋዛ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቆይ እና በቆራጥነት ወደ ምዕራፍ ሁለት እንዲሸጋገር ያላቸውን ፍላጎት የገለጹት ሃላፊው፥ ይህ ማለት የሁለት-መንግስታት የመፍትሄ ሃሳብን ጨምሮ የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ ከአከባቢው መውጣት፣ የታጠቁ ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታትን እና ግልጽነት ያለው የፖለቲካ አድማስን መፍጠር እንደሚያካትት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ግዴታዎችን አስመልክቶ ባለው ነገር ግልጽ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ አስታውሰው፥ ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት እንዲሰፍን ሀላፊነት ያለበት የተባበሩት መንግስታት እና በሥሩ የሚገኘው የፀጥታው ምክር ቤት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ምክር ቤቱ ብቻ ሁሉንም አባል ሀገራት ወክሎ የመንቀሳቀስ፣ አስገዳጅ ውሳኔዎችን የመቀበል እና በዓለም አቀፍ ህግ የኃይል አጠቃቀምን የመፍቀድ ስልጣን እንዳለው ጠቅሰዋል።

“ይሄንን ሚና ሌላ አካል ወይም ተነሳሽነት ሊተካው አይችልም” ያሉት የተባበሩት መንግስታት ሃላፊው፥ የፀጥታው ምክር ቤትን ማጠናከር እና ማሻሻያ ማድረግ ጠቃሚ የሚሆነው ለዚህ ነው ብለዋል።

በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምሩም፥ ነገር ግን አሁንም በቂ እንዳልሆኑ ጠቅሰው፥ ከምግብ በተጨማሪ፣ በጤና አጠባበቅ፣ በመጠለያ፣ በውሃ እና በንፅህና አጠባበቅ ስርዓቶች ላይ እጅግ በጣም ብዙ ፍላጎቶች እንዳሉ የገለጹ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት የህይወት አድን እርዳታ በጣም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲደርስ እንቅፋቶችን ለማሸነፍ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስጋት ላይ መሆኑን የሚያሳውቅ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት አምባሳደሮች መላኩ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ የሆነበት ምክንያት እና ይሄንን ችግር ለማስቀረት አባል ሀገራት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተጠየቁት ጉተሬዝ፥ ይህ የተለመደ የገንዘብ ፍሰት ችግር እንዳልሆነ ማሳሰባቸውን ጠቅሰው፥ ምንም እንኳን የተባበሩት መንግስታት ከዚህን በፊት ያልተከፈሉ መዋጮዎችን ለማስከፈል አስቸጋሪ ጊዜያትን ቢያሳልፍም፥ አሁን የተከሰተው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ ለአባል ሀገራት ግልፅ ማድረጋቸው ተናግረዋል።

ከፀደቀው መደበኛ በጀት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻን የሚሸፍኑ የተወሰኑ መዋጮዎችን በጊዜ አለመክፈልን አስመልክቶ የተለያዩ ውሳኔዎች ይፋ እንደተደረጉ ገልጸው፥ ይህ መዋቅራዊ ቀውስን እንደሚፈጥር እና በነባር የፋይናንሺያል ሕጎች መሠረት ገንዘቦች በጊዜ ካልተከፈሉ ድርጅቱ ሕጋዊ ግዴታዎች ሙሉ በሙሉ ሊተገበሩ በማይችሉበት ጊዜም እንኳ ‘ሥራ ላይ ያልዋሉ’ የገንዘብ መጠኖችን መመለስ እንዳለበት የጠቆሙ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ውጤቱ ዘላቂነት የሌለው የጥርጣሬ ዑደትን፣ የፕሮጄክቶች መዘግየትን እና አባል ሀገራት ራሳቸው ባፀደቁት ትዕዛዞች ላይ የአቅርቦት መቀነስ እንዲከሰት ያደርጋሉ ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ለመዋቅራዊ የፋይናንስ አደጋ ተጋላጭ ስለሚያደርገው አሁን ያለው አካሄድ ሊቀጥል እንደማይችል የገለጹት ሃላፊው፥ አባል ሀገራት የተባበሩት መንግስታት የፋይናንስ ህጎችን ለማሻሻል መስማማት እንዳለባቸው ወይም ደግሞ የገንዘብ እጥረቱ የሚያስከትለውን አደጋ መቀበል አለባቸው ብለዋል።

በቅርቡ አቡ ዳቢ በዩክሬን፣ በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል የመጀመሪያውን የሶስትዮሽ ድርድር ማስተናገዷን፥ ነገር ግን ከደህንነት ዋስትና ጋር የተያያዘው ቅድመ ሁኔታ ዩክሬን የተለያዩ ግዛቶችን የመልቀቅ ሃሳብን እንድትቀበል እና ይህ ለፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ተቀባይነት ያለው መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት ጉተሬዝ፥ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት ሁሉንም ጥረቶች በደስታ እንደሚቀበሉ እና የተባበሩት መንግስታት መሰል ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ይሁን እንጂ ስለ ዩክሬን ሲነሳ መሰረታዊ የሆኑ መርሆችን ማስታወስ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ መጀመሪያ ላይ ዩክሬንን የወረረችው ሩሲያ እንደሆነች እና ለዚህ ወይም ለማንኛዉም ግጭት መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች በዓለም አቀፍ ህግ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መርሆች ላይ የተመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ጉተሬዝ ሁለቱ ወገኖች ከተስማሙ እና ተቋማቸው ጣልቃ እንዲገባ ከተጠየቀ የተባበሩት መንግስታት የሰላም ሂደትን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ውሳኔዎች በተባበሩት መንግስታት ላይ የተመሰረቱ ሳይሆኑ በፓርቲዎች ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የሩስያ ፌደሬሽን ሙሉ በሙሉ በዩክሬን ላይ ወረራ ከጀመረ አራት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ያስታወሱት ሃላፊው፥ ሞትና ውድመትን ያስከተለው ጦርነት፣ ከሁለቱም ሀገራት ቁጥራቸው የማይገመት የሰው ህይወት የቀጠፈ እንዲሁም በአውሮፓ ሰላምና ደህንነት ላይ ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሰረታዊ እና ወሳኝ መርሆች ላይም ትልቅ ስጋት መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በቅርብ ወራት ውስጥ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ ድግሪ ሴንቲግሬድ በታች እየቀነሰ በሄደበት ወቅት በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የደረሱት ስልታዊ ጥቃቶች አስከፊ ሰብዓዊ መዘዞችን ማስከተሉን ያስታወሱት አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ በእነዚህ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን መብራት፣ ማሞቂያ እና ውሃ ማጣታቸውን ጠቁመው፥ የትም ቢሆን በሰላማዊ ዜጎች እና በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ብሎም ፍትሃዊ እንዳልሆኑ እና በአስቸኳይ መቆም እንዳለባቸው አሳስበው፥ “ይህ በፍፁም መጀመር ያልነበረበት ጦርነት በአስቸኳይ ማብቃት አለበት” በማለት አጠቃለዋል።

06 Feb 2026, 13:44