ፍልስጤማዊያን ህሙማን ለህክምና ወደ ግብፅ ለመጓዝ ሲዘጋጁ ፍልስጤማዊያን ህሙማን ለህክምና ወደ ግብፅ ለመጓዝ ሲዘጋጁ   (ANSA)

በጋዛ የሚገኘው የራፋህ መሸጋገሪያ መንገድ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደተከፈተ ተነገረ

እስራኤል የጋዛን ሰርጥን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘውን የራፋህ መሸጋገሪያ መንገድን ክፍት እንዳደረገች ቢነገርም አሁንም ድረስ የተወሰኑ እገዳዎች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፥ መሻገሪያ መንገዱ በከፊል የተከፈተው በእስራኤል እና በሀማስ መካከል የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩን ተከትሎ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ ሰርጥ እና በግብፅ መካከል ያለው የራፋህ ድንበር ጥር 24 ቀን 2018 ዓ.ም. "ለሙከራ" እንደገና መከፈቱን የእስራኤል ባለስልጣናት ያስታወቁ ሲሆን፥ በዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ የሲቪል አስተዳደርን የሚቆጣጠረው የእስራኤል ወታደራዊ ክፍል የሆነው ኮጋት (COGAT) እንደገለጸው መንገዱ የተከፈተው በአሜሪካ አሸማጋይነት በእስራኤል እና በፍልስጤም እስላማዊ ቡድን ሃማስ መካከል የተደረገው ሁለተኛ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት አካል ሆኖ እንደሆነ ገልጿል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የቆመው እና ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት፣ ውድመትን ብቻ ሳይሆን፥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ሕይወት መቅጠፉ የሚታወቅ ሲሆን፥ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው በርካታ ህሙማን መካከል የተወሰኑት በጎረቤት ሀገራት ህክምና ለማግኘት እና የተሻሉ ቀናትን ተስፋ በማድረግ የጋዛን ድንበር እያቋረጡ እንደሚገኝ ቢገለጽም፥ ማን እና በምን ምክንያት ጋዛን ለቆ ወደ ግብፅ ሊጓዝ እንደሚችል ለመረዳት አሁንም አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል።

መሸጋገሪያ መንገዱ "ለሰዎች የተወሰነ እንቅስቃሴ ብቻ" የተከፈተ መሆኑንም ጭምር ኮጋት የገለጸ ሲሆን፥ ወታደራዊ ክፍሉ በኋላ ላይ ባወጣው መግለጫ የመሸጋገሪያ መንገዱ መከፈት የ"ሙከራ" ሂደት መሆኑን እና ከሰኞ ጀምሮ መንገዱ ክፍት እንደሚሆን ገልጿል።

የጋዛን ዕለታዊ ጉዳዮች የሚያስተዳድረው አዲሱ የፍልስጤም ኮሚቴ ኃላፊም የመሸጋገሪያ መንገዱ ከሰኞ ጀምሮ በሁለቱም አቅጣጫዎች እንደሚከፈት የተናገሩ ሲሆን፥ በደቡባዊ ጋዛ የምትገኘው ራፋህ ሰዎች እስራኤልን ሳያቋርጡ ከጋዛ ሰርጥ መውጣት እና መግባት የሚችሉበት ብቸኛ መሸጋገሪያ እንደሆነ ይታወቃል።

መሻገሪያ መንገዱ ከሁለት ዓመታት በላይ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፥ ሁለቱም መግለጫዎች የመንገዱ መከፈት ዓለም አቀፍ እርዳታን ስለመጨመሩ እና መሸጋገሪያ መንገዱ በይፋ ለሰብአዊ ጉዳዮች ክፍት መሆኑ የተነገረ ቢሆንም፥ ነገር ግን በተናጠልም ሆነ በቡድን ጋዛን ለቀው መውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች ምንም የተባለ ነገር እንደሌለ ተገልጿል።

አሁንም ድረስ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች
ሌላው ትልቁ ጉዳይ ደግሞ "የሰብአዊ ጉዳዮች" ተብለው ያልተጠቀሱ የሌሎች ሰዎች ጉዳይ ሲሆን፥ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች በእስራኤል ባለስልጣናት በኩል መልስ ያላገኙ እንደሆነ ተነግሯል።

ባለስልጣናቱ እንደገለጹት የመሻገሪያ መንገዱ በቀን ከስድስት ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ ክፍት እንደሚሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜ 150 ሰዎች ብቻ ከጋዛ ሰርጥ መውጣት እንደሚፈቀድላቸው እና ከግብፅ በኩል ግን ወደ ጋዛ መሻገር የሚችሉት ሃምሳ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ተገልጿል።

በጋዛ ከተማ የሚገኘው የአል-ሺፋ ሆስፒታል ኃላፊ ዶክተር መሃመድ አቡ ሳልሚያ ወደ ሃያ ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን አስቸኳይ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹ ሲሆን፥ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በቀን 50 ታካሚዎች ከጋዛ እንዲወጡ ይፈቀድላቸዋል ብለዋል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት የጋዛን የጤና አገልግሎት ስላወደመው እና በአሁኑ ወቅት 4500 የሚሆኑ ህፃናት በአስቸኳይ ከጋዛ ወጥተው ህክምና ማግኘት ስለሚገባቸው ይህ አሃዝ ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጸው፥ ይህ በመሆኑ ምክንያት በየቀኑ 50 ታካሚዎችን ብቻ ማስወጣት የተፈናቀሉትን ህዝቦች ፍላጎት እንደማያሟላ ዶክተር ሳልሚያ አሳስበዋል።

በግብፅ አምቡላንሶች ተሰልፈው እየጠበቁ ነው
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ታካሚዎች ብቻ ከሀገር እንዲወጡ መፍቀድ አሁን ያለውን ሁኔታ የማያሻሽል መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የእስራኤል ባለስልጣናት የህክምና አቅርቦቶችን እና ተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ጋዛ እንዲገቡ ቢፈቅዱም ነገር ግን ይህ በቂ እንዳልሆነ እየተገለጸ ይገኛል።

በሌላኛው በኩል በግብፅ ግዛት ውስጥ ለጋዛ ህሙማን ህክምና ለመስጠት አምቡላንሶች በብዛት ተሰልፈው እየተጠባበቁ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የግብፅ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከጋዛ የታመሙ እና የቆሰሉትን ለማከም 12 ሺህ ዶክተሮች መመደባቸውን እንዲሁም የራፋህ መሸጋገሪያ መንገድ ላይ ድንገተኛ ህክምና የሚሰጡ 30 ቡድኖችን መመደባቸውን የግብፅ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

03 Feb 2026, 14:19