በሱዳን የሚገኙ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሱዳን የሚገኙ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች   (AFP or licensors)

የዳርፉር ህፃናት በመተው እና በተስፋ አፋፍ መካከል እንደሚገኙ ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት በሱዳን ዳርፉር ግዛት ውስጥ በአከባቢው እየተስፋፋ በመጣው ግጭት ምክንያት አንድ ህፃን እንኳን መድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን አስጠንቅቋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሱዳን ዳርፉር ክልል ውስጥ በአሸዋማ መንገዶች እየነዱ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልገው አንድ ህፃን እንኳን ለመድረስ የቀናት ድርድር እና በርካታ የፈቃድ ሂደቶችን ሊወስድ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ኤጀንሲ ዩኒሴፍ ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ኢቫ ሂንድስ ለአስር ቀናት ያክል በአከባቢው ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በአከባቢው ያለውን በጥንቃቄ የተሞላ እና እጅግ አስቸጋሪ የሰብአዊ እርምጃዎችን ገልጸዋል።

“በአሁኑ ጉብኝት ያየሁት ነገር ከዚህ በፊት ከነበረው ምንም የተለየ ነገር ዬለም” ያሉት ሃላፊው፥ የመፈናቀሉ መጠን፣ የግጭቱ መበራከት እና የአገልግሎት መስጫ ተቋሞች መፈራረስ እያንዳንዱ ህፃን የሞት አፋፍ ላይ የሚኖርበትን ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመው፥ ተፋላሚ ወገኖች ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ለሦስት ዓመታት ያህል ሲፋለሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በተጀመረው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ሃገሪቷ አስከፊ የሆነ ችግር ውስጥ የገባች ሲሆን፥ ግጭቱ በጎረቤት ሀገራትም ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሱዳን ጦር ሃይሎች (SAF) እና ፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይሎች (RSF) መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ከ150,000 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፥ 10 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን እና በአከባቢው ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዲከሰት ማድረጉ ተገልጿል።

ተቋማቸው ከአደጋ ጊዜ ጋር በተያያዘ የዓመታት ልምድ እንዳለው የገለጹት ወይዘሮ ኢቫ፥ ነገር ግን በሰሜናዊ ዳርፉር በምትገኘው ታዊላ ከተማ ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ እንደሆነ ጠቁመው፥ በችግር፣ በፍርሃት እና በተስፋ መቁረጥ የተነሳ ሙሉ ከተማዋ የፈረሰች እና እንደገና እየተገነባች ያለ ይመስላል በማለት አስረድተዋል።

ከ500,000 እስከ 600,000 የሚደርሱ ሰዎች ወደ ታዊላ ተሰደው የተጠለሉ መሆናቸውን የጠቆሙት ሃላፊዋ፥ ‘በከተማዋ ውስጥ በሚገኘው እጅግ ሰፊ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ መቆየት በጣም የሚያስደንቅ ነበር’ ሲሉ አክለዋል።

"በዓለማችን ትልቁ የሰብአዊ ድንገተኛ አደጋ"
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣኗ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በቆዩባቸው ሁለት ሳምንታት ዩኒሴፍ እና አጋሮቹ ከ140,000 በላይ ለሚሆኑ ህፃናትን ክትባት መስጠቱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ለበሽታ እና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለተጋለጡ ህፃናት ደግሞ ህክምና መስጠታቸውን ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ ተፈናቃዮቹ የመጠጥ ውኃን እንዲያገኙ፣ ጊዜያዊ የትምህርት ተቋማትን ማቋቋማቸውን፣ የምግብ እና የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አንድ ሙሉ ኮንቮይ፣ አንድ ክሊኒክ እና አንድ መማሪያ ክፍል በአንድ ጊዜ ማድረስ በጣም አድካሚ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንደነበር የጠቆሙት ሃላፊዋ፥ ነገር ግን ይህ እርምጃ በዳርፉር ውስጥ ለሚገኙ ህፃናት በመተው እና በመድረስ መካከል ያለ ቀጭን መስመር ነው ብለዋል።

በሴቶች እና ልጃገረዶች ማዕከል ውስጥ እናቶች ለልጆቻቸው የሚሆኑ ምግቦችን፣ ብርድ ልብሶችን ወይም የህፃናት ልብሶችን የመሳሰሉ ችግሮቻቸውን ተካፍለው እንደሚኖሩ ያስታወሱት ወይዘሮ ኢቫ፥ በመጠለያው ውስጥ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ጠቁመዋል።

በስፍራው ካስተዋሉት ሁኔታ አንፃር ሱዳን ከዓለም ትልቁ የሰብአዊ አደጋ የተከሰተባት ሃገር መሆኗን የጠቀሱት ሃላፊዋ፥ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ብዙ ያልታዩ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው፥ በተገደበ ተደራሽነት፣ በውስብስብ ግጭት እና ዓለም አቀፍ ቀውሶች መካከል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ስቃይ ተደብቆ እንደሚገኝ አበክረው ተናግረዋል።

ሰብዓዊ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ እየተከሰተ መሆኑን ያስጠነቀቁት የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊዋ፥ በሱዳን ውስጥ የሚገኙ ህፃናት በአስቸኳይ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እና ወሳኝ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበው፥ ይህ ካልሆነ በህፃናቱ እና በጣም ተጋላጭ በሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ አስከፊ ችግር እንደሚከሰት ተናግረዋል።

02 Feb 2026, 14:56