ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ የሚጠቀሙበት ከጎማ የሚሰራ ጀልባ - የማህደር ምስል ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ የሚጠቀሙበት ከጎማ የሚሰራ ጀልባ - የማህደር ምስል  

በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ሲጓዙ በነበሩ ስደተኞች ላይ በደረሰ አደጋ የህፃናት ህይወት ማለፉ ተነገረ

በሊቢያ ባህር ዳርቻ 55 ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችው አነስተኛ የስደተኞች ጀልባ ሰጥማ ሁለት ህፃናትን ጨምሮ 53 ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው የሞቱ ወይም ጠፍተዋል የተባለውን ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር መረጃ ይፋ ማድረጉ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሊቢያ የህይወት አድን እና ፍለጋ ሰራተኞች ሁለት ናይጄሪያውያን ሴቶች ብቻ የተረፉ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ከተረፉት ሴቶች መካከል አንዷ ባሏን በአደጋው እንዳጣች እና ሁለተኛዋ ሴት ደግሞ ሁለት ህፃናት ልጆቿን ማጣቷ ተነግሯል።

የሰጠመው አነስተኛ የስደተኞች ጀልባው ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ሰዓታት በኋላ የሊቢያ የባህር ዳርቻ ከተማ በሆነችው ዙዋራ ሲደርስ መገልበጡ እና ወዲያውኑ በውሃ መወሰዱ ተገልጿል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በጥር ወር ብቻ በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ በተከሰተው ከባድ የአየር ጠባይ ምክንያት በርካታ “ያልታዩ” የጀልባ መስጠም አደጋዎችን ተከትሎ በትንሹ 375 ስደተኞች መሞታቸው ወይም መጥፋታቸው እና ያልተመዘገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የአደጋው ሰለባ እንደሆኑ ይታመናል ተብሏል።

እነዚህ ተደጋጋሚ ክስተቶች አደገኛውን የባህር ክልል ለመሻገር በሚሞክሩ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ላይ የሚደርሰውን ዘላቂ እና ገዳይ የሆኑ አደጋዎች ያሳያሉ የተባለ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአውሮፓዊያኑ 2025 ብቻ በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከ1,300 የሚበልጡ ስደተኞች መጥፋታቸውን የገለጸ ሲሆን፥ የመጨረሻው አደጋ ከተከሰተበት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በጉዞ ላይ እያሉ መሞታቸው ወይም መጥፋታቸው የተገለጸው የስደተኞች ቁጥር ቢያንስ 484 መድረሱ ተነግሯል።

ግጭት እና ድህነትን ሸሽተው ወደ አውሮፓ ለመግባት ከሚሞከርባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የሊቢያ መስመር እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በረሃውን እና የሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ መሞከር በአደጋ የተሞላ ጉዞ እንደሆነም ይነገራል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ‘ስደተኞች ወንድሞችና እህቶች ናቸው’ ማለታቸው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መስከረም ወር ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት በርካታ የስደተኞች ጀልባዎች በሚያርፉባት የላምፔዱዛ ደሴት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ስደተኞችን ለመቀበል ያሳዩት ተግባር ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ተምሳሌት በመሆኑ አመስግነው፥ “ስደተኞች ጠላቶች ሳይሆኑ ወንድሞች እና እህቶች ናቸው” ያሉ ሲሆን፥ ክርስቲያኖች ያለ ርህራሄ ፍትህ እንደሌለ፥ የሌሎችን ህመም ሳያዳምጡ ህጋዊ መሆን እንደሌለ መናገራቸውን አጥብቀው መቀጠል እንዳለባቸው መምከራቸው ይታወሳል።

11 Feb 2026, 14:35