ፈልግ

ታዎን ፍልስጤማውያንን በተለይም ወጣቶችን የሚደግፉ ከ8,200 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጓል ታዎን ፍልስጤማውያንን በተለይም ወጣቶችን የሚደግፉ ከ8,200 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጓል  ( TAAWON.ORG)

የዛይድ ሽልማት ‘ታዎን’ የተሰኘውን የፍልስጤም ድርጅት ሶስተኛው ተሸላሚ አድርጎ መሰየሙ ተገለጸ

የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት ‘ታዎን’ (Taawon) የተሰኘው የፍልስጤም ሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት በክልሉ ውስጥ ለአስርት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ወቅት ባከናወነው የሰብዓዊ እና የልማት ሥራዎች እውቅና በመስጠት በሰባተኛው ዙር የሽልማት ሥነ ስርዓት በሶስተኛው ደረጃ የክብር ተሸላሚ አድርጎ መሰየሙ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ‘ታዎን’ የተሰኘው የፍልስጤም የበጎ አድራጎት ድርጅት የሰባተኛው ዙር ሶስተኛው የክብር ተሸላሚ እንደሚሆን ይፋ አድርጓል።

በተቋሙ ይፋዊ መግለጫ መሰረት የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚከበረው የዓለም አቀፍ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ቀን አቡ ዳቢ በሚገኘው እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን መታሰቢያ በተሰራው ሐውልት እና የጎብኚዎች ማዕከል ውስጥ በሚከበረው ሥነ ስርዓት ከአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተሸላሚዎች ጎን ለጎን በ 1983 ዓ.ም. ለተቋቋመው ለዚህ ድርጅትም በሦስተኛ ደረጃ እንደሚሰጥ ጭምር ተገልጿል።

ታዎን የተሰኘው ይህ የፍልስጤም ድርጅት በዌስት ባንክ፣ በጋዛ እና በሊባኖስ በሚገኙ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የሚያግዝ ልዩ የሰብዓዊ እና የልማት ሥራው እውቅና ለመስጠት መመረጡ ተነግሯል።

ታዎን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በትምህርት፣ ወጣቶችን በማብቃት፣ ለወላጅ አልባ ህፃናት በሚያደርገው እንክብካቤ፣ የባህል ፕሮጀክቶች፣ ታሪካዊ ከተሞችን መልሶ ማቋቋም እና የማህበረሰብ ልማትን ጨምሮ ለጤና፣ ግብርና እና ድንገተኛ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉ ተገልጿል።

ድርጅቱ ፍልስጤማውያንን በተለይም ወጣቶችን የሚደግፉ ከ 8,200 በላይ ፕሮጀክቶችን በመተግበር የመቋቋም አቅምን በማጠናከር፣ የሥራ እድሎችን በማሳደግ እና ማህበረሰቦችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በባህል ዘርፍ ለማገዝ፥ በተመሳሳይ ሁኔታ የፍልስጤማዊያንን ቅርስ በመጠበቅ፣ ዘላቂ ልማትን በማበረታታት እንዲሁም ስልጣኔን እና አዳዲስ ፈጠራን በማበረታታት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።

የታዎን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ናቢል ቃዱሚ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድንን ያቀፈው የሽልማቱ የዳኞች ኮሚቴ ባሳየው የውይይት እና ተቻችሎ አብሮ የመኖር ዘይቤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ባለፈው ሳምንት የዛይድ ሽልማት ዳኞች በአዘርባጃን ሪፐብሊክ እና በአርሜኒያ ሪፐብሊክ መካከል ለተደረገው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት የመጀመሪያ ደረጃ ክብር፥ ለአፍጋኒስታዊዋ ተሟጋች ዛርቃ ያፍታሊ በሁለተኛ ደረጃ መሰየሙ ይታወሳል።

የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ እና የአርሜኒያ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን በካውካሰስ ክልል ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ባደረጉት የጋራ እውቅና የተሰማቸውን ኩራት መግለፃቸው ተነግሯል።

እ.አ.አ. ከ 2019 ጀምሮ ሽልማቱ በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅ ወንድማማችነትን እሴቶችን በማስተዋወቅ እና በማሳደግ ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ግለሰቦች እውቅና በመስጠት ከ20 ሀገራት የተውጣጡ 20 ተሸላሚዎችን መሸለሙ ይታወቃል።

27 Jan 2026, 15:16