የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሃላፊ በአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ሊጠበቅ እንደሚገባ አሳሰቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ማስፈጸሚያ ኤጀንሲ (ICE) ባወጣው ይፋዊ መረጃ መሰረት የታሰሩት ሰዎች ቁጥር በጎረጎሳዊያኑ 2025 ከታሰሩት ሰዎች ቁጥር 65 በመቶ መጨመሩን እና በታህሳስ ወር መጨረሻ 70,000 ገደማ መድረሱን ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ባለስልጣን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉ ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ የእስረኞች ቁጥር ጭማሪ በማንሳት ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በአሁኑ ጊዜ በስደተኞች እና ፍልሰተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እና ንቀት እንዳሳሰባቸው ጠቁመው፥ “ለስደተኞቹ ክብር እና ለጋራ ሰብዓዊነታችን መጨነቅ የት ገባ?” በማለት ጠይቀዋል።
የወከባው ውጤት
ጥር 15 በታተመው ዜናዊ መግለጫ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ እንደገለጹት ሰነድ የሌላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንደ ሆስፒታሎች፣ የአምልኮ ቦታዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ገበያዎች እና የግል ቤቶች በመሳሰሉ አከባቢዎች እንዴት ኃይል በተሞላበት ሁኔታ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ እና እንደሚታሰሩ ገልጸው፥ ቱርክ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ባለስልጣናት እየወጡ ያሉ በርካታ የስደት ፖሊሲዎች እንዳሉ አሳስበዋል።
ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በአይሲኢ ተይዘው ከታሰሩ ሰዎች መካከል ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ወንጀለኞች እንዳልሆኑ ወይም የዜግነት ማመልከቻቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ እና የወንጀል ክስ ያልተከሰሱ መሆኑን አሃዛዊ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱ መግለጫው ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ሃላፊው በአሁኑ ጊዜ በስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ባለው ግፍ እና ንቀት መደነቃቸውን ገልጸው፥ ይህም በህዝቡ ዘንድ ፍርሃትን መፍጠሩን የገለጹ ሲሆን፥ በዚህም ስጋት ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት እና ከህክምና ቀጠሮዎች እያስቀሩ እንደሆነ አብራርተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ሃላፊ እንዳስታወቁት ሁኔታው በስደተኞች ወይም በፍልሰተኞች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፥ ጉዳዩን በሚቃወሙ ሰዎች ላይም ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በህጉ ማዕቀፍ ውስጥ
አሜሪካ እንደ ሀገር የስደት ፖሊሲዎችን የመተግበር እና የማስፈፀም መብት ቢኖራትም፥ መንግስት ጉዳዩን በህግ በተደገፈ መልኩ ሊተገብር እንደሚገባ
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ሃላፊው አሳስበዋል።
“እርምጃው ተገቢውን ሂደት ካልተከተለ በይበልጥ የህዝብን አመኔታ ይሸረሽራል” ያሉት ቱርክ፥ ይህም በሂደት የህግ የበላይነት እንደሚቀንስ፣ ተቋማዊ ህጋዊነትን እንደሚያዳክም እና የግለሰቦችን መብት እንደሚጥስ አስጠንቅቀዋል።
አላስፈላጊ ወይም ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል በተደጋጋሚ ሲተገበር በማየታቸው እንዳሳዘናቸው የገለጹት ኃላፊው፥ አስጊ ሁኔታ ካልታየ በስተቀር ሆን ተብሎ የመግደል እርምጃን መውሰድ ዓለም አቀፍ ህግን እንደሚጥስ አመላክተዋል።
ቤተሰቦችን አንድ ላይ ማቆየት
ቱርክ እንዳመለከቱት በሁሉም አሃዛዊ መረጃዎች እና ሪፖርቶች መሰረት ቁጥሮቹ መበራከታቸው እና የሰው ልጅ ዋጋ ክብር ማጣቱን እንደሚያሳዩ ጠቁመው፥ በተለይም ቤተሰቦችን በተመለከተ ምን ያህሉ እስራት እና ማፈናቀል እንደደረሰ ያሳያሉ ካሉ በኋላ፥ ይህም ህፃናትን ለከባድ እና ለረጅም ጊዜ ጉዳት ያጋልጣል ብለዋል።
በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሁሉም ደረጃ ያሉ መሪዎች “ማዘናጋት እና መለያየትን የሚከተሉ ስልቶችን” እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋው፥ ይህም በተራው ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችን ለ“ጥላቻ እና በደል” ያጋልጣል ብለዋል።