የኦሽዊትዝ የማጎሪያ እና የዘር ፍጅት የተካሄደበት ካምፕ የተዘጋበት 81 ኛ ዓመት ሲከበር የኦሽዊትዝ የማጎሪያ እና የዘር ፍጅት የተካሄደበት ካምፕ የተዘጋበት 81 ኛ ዓመት ሲከበር   (ANSA)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሆሎኮስት የመታሰቢያ ቀን ላይ ቤተ ክርስቲያን ማንኛውንም ዓይነት ፀረ-ሴማዊነት አትቀበልም ማለታቸው ተነገረ

የኦሽዊትዝ የማጎሪያ እና የዘር ፍጅት የተካሄደበት ካምፕ ከተዘጋ ወይም ነፃ ከወጣ ከ81 ዓመታት በኋላ በሆሎኮስት የጠፋውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት የሚታወስ ሲሆን፥ በማንኛውም መልኩ የዚህ ዓይነቱ “ጭፍን ጥላቻ፣ አክራሪነት እና ዘረኝነት” እንዳይደገም ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን በተቆጣጠረቻቸው የአውሮፓ ክፍሎች ውስጥ በፖላንድ በነበረው የኦሽዊትዝ ካምፕ ብቻ ከ1.1 ሚሊየን አይሁዶች በላይ መገደላቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህ ማጎሪያ ካምፕ የዛሬ ሰማንያ አንድ ዓመት በዛሬዋ ዕለት መዘጋቱ ይታወቃል።

ኦሽዊትዝ በደቡባዊ ፖላንድ የሚገኝ የፖላንድ ጦር ሰፈር ሲሆን ናዚዎች ሀገሪቱን በመስከረም 1939 ሲቆጣጠሩ ወደ ፖለቲካ እስረኞች ማቆያነት ቀይረውታል።
በሕይወት የተረፉ ሰዎች ከማጎሪያ ካምፑ ነፃ የወጡበትን ታሪካዊ ወቅት ለማክበር ጥር 27 እንደ ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ቀን ተደርጎ በተባበሩት መንግስታት እ.አ.አ. በ 2005 ዓ.ም. መመረጡ የሚታወስ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት ዘንድሮ ለ 25ኛ ጊዜ መከበሩ ተነግሯል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጳጳሳዊ የትዊተር ገፃቸው ላይ ዓለም አቀፍ ቀኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማንኛውም ዓይነት ፀረ-ሴማዊነት ጋር በተያያዘ ‘ኖስትራ አቴቴ’ በተሰኘው የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ላይ የወጣውን የማያወላውል አቋም በታማኝነት ማክበሯን ትቀጥላለች ያሉ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያን በዘር፣ በቋንቋ፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ማንኛውንም ዓይነት መድልዎ ወይም ትንኮሳ አትቀበልም” በማለት አክለዋል።

የጥላቻ እና የአክራሪነት አደጋዎች
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና ከአስከፊው የሆሎኮስት ጥቃት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመ ሲሆን፥ ዓላማው ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ፣ ለተቸገሩ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ መስጠት፣ ሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ እና ዓለም አቀፍ ህግጋትን ማስከበር እንደሆነ ይታወቃል።

የተባበሩት መንግስታት ይህንን ተልዕኮ ከግምት ውስጥ በማስገባት እ.አ.አ. በ 1948 ሁለት መሰረታዊ ሰነዶችን ያጸደቀ ሲሆን፥ እነዚህም የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል እና መቅጣት የሚሉ የስምምነት ማእቀፎች ናቸው።

ከነዚህ ሰነዶች ጎን ለጎን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይሄንን ዓለም አቀፍ ቀን በመሰየም እልቂት ‘ለሁሉም ሰዎች የጥላቻ፣ የትምክህተኝነት፣ የዘረኝነት እና የጭፍን ጥላቻ አደጋ ለዘላለም ማስጠንቀቂያ ይሆናል’ ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

የማስታወሻ መንገዶች
በዚህ ውሳኔ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት "ወደፊት የዘር ማጥፋት ድርጊቶችን ለመከላከል መጪውን ትውልድ በሆሎኮስት አማካይነት ግንዛቤ የሚያዳብሩ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን እንዲያዘጋጁ ያሳሰበ ሲሆን፥ ለዚህ ጥሪ ከሃያ አንድ ዓመታት በኋላ የተለያዩ ሃገራት በራሳቸው መንገድ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህም መሰረት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተመሰረተው የሆሎኮስት ትምህርት ማዕከል አማካይነት ድርጊቱ እንዴት እና ለምን እንደተከሰተ ለመረዳት የተለያዩ ጥናቶች ይደረጋሉ። በማዕከሉ የሚደረገው ጥናት የሚያተኩረው ሆሎኮስት በቀላሉ ትዝታ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር፥ ከዚህም ይልቅ ታሪኩ እና ትምህርቶቹ ለአሁኑ ትውልዶች መተላለፋቸውን ለማረጋገጥ ነው ተብሏል።

በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዲፕሎማቶች እና የህዝብ ተወካዮች ከሆሎኮስት የተረፉ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ዓለም አቀፍ ቀንን ለማክበር ይሰበሰባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የ 25 ዓመታት ድምፆች እና ታሪኮች
የዚህ ዓለም አቀፍ ቀን 25ኛ ዓመት መሪ ቃል “የሆሎኮስት ትውስታ ለሰብዓዊ ክብር እና መብቶች” የሚል ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው “መታሰቢያነቱ በሆሎኮስት ሰለባ የሆኑትን እና በሕይወት የተረፉትን ለማስታወስ እንደሆነ ገልፆ፥ በቀኑ ናዚዎች ለማጥፋት የፈለጉትን ማህበረሰቦች እና ወጎች እንዲሁም የሚወዷቸውን ሰዎች ይታወሳሉ ተብሏል።

ይሄንን ድርጊት ማስታወስ ሁሉም ሰው “የፀረ-ሴማዊነት እና የጥላቻ እንዲሁም ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት እና የግዴለሽነት ውጤቶች ላይ እንዲያሰላስል ግፊት የሚያደርግ እንደሆነ ይገለፃል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው እልቂቱ ከተከሰተ ከስምንት አስርት ዓመታት በላይ በኋላ ሰዎች ዛሬ በዓለም ዙሪያ በየቀኑ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው ያመላከተ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ፀረ-ሴማዊነት እየጨመረ መምጣቱን እና የሆሎኮስትን ታሪክ መካድ እና ማዛባት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።

የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የፀረ-ሴማዊነት ጽህፈት ቤት ባወጣው ዘገባ መሰረት በመላው አውሮፓ "የጥላቻ ይዘት 400 በመቶ መጨመሩን ይፋ አድርጓል።

ሆሎኮስትን በማስታወስ ግን “ክህደትንና መዛባትን መከላከል፣ ውሸትን መቃወም፣ ጥላቻን መጋፈጥ፣ የተጎጂዎችን ሰብአዊነት አጥብቆ መጠየቅ ይቻላል በማለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።

ብሄር፣ ሀይማኖት እና አስተዳደግ ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ሰው ሁለንተናዊ መብቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ሰላምን ለማምጣት እጅግ አስፈላጊ እና የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ ማዕከላዊ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ዓለም አቀፍ ቀን የጭፍን ጥላቻ፣ አክራሪነት እና የፀረ-ሴማዊነትን ተግባራት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ ማንቂያ ደወል ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፥ ይሄንን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት “የሆሎኮስት ሰለባዎችን በማክበር የጋራ ሰብአዊነታችንን እናረጋግጣለን፥ ብሎም የሁሉንም ሰዎች ክብር እና ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅ ቃል እንገባለን” ብሏል።

ከዚህም በላይ የሆሎኮስት መታሰቢያ ቀን ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ የጥሪ ቀን ሲሆን፥ መርሳት እንደማይገባ፥ ይልቁንም እንደ ሆሎኮስት ያሉ አሰቃቂ ድርጊቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ዓለምን ማንቃት እንደሚገባ ተነግሯል።

28 Jan 2026, 15:12