ፈልግ

የሮም ከተማ ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ የሮም ከተማ ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ   (@Vatican Media)

የሮም ከንቲባ ‘ያሳለፍነው የኢዮቤልዩ ዓመት መቼም ቢሆን የማይረሳ ነው’ ማለታቸው ተነገረ

የሮማ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሮቤርቶ ጓልቲየሪ የጎረጎሳዊያኑን የ 2025 ቅዱስ ዓመትን በማስመልከት ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት “በጣም የበለጸገ ይዘት እና ጥልቅ መንፈሳዊ እሴቶች” የነበሩት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ትብብር እና መስተንግዶ” በጉልህ የታየበት “ያልተለመደ” ኢዮቤልዩ ነበር ያሉት የሮማው ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የ2025 የተስፋ ኢዮቤልዩ አስመልክተው የመጀመሪያ ግምገማ ያቀረቡ ሲሆን፥ ከንቲባው በቶር ቬርጋታ በተከበረው የወጣቶች ኢዮቤልዩ ላይ ስለተሳተፉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች እና ከዝግጅቱ በፊት በሮም ስለተከናወኑ ዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶች አንስተው ተወያይተዋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ በር ሊዘጋ ሰባት ቀናት በቀሩበት ወቅት ስለኢዮቤልዩ ያላቸውን ግምገማ ከቫቲካን ዜና የተጠየቁት ከንቲባ

ሮቤርቶ፥ የእሳቸው ግምገማ በጣም አዎንታዊ እንደነበር፣ በተሳትፎ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን የተሳተፉበት እና ከእውነተኛ ብሎም ተጨባጭ የተስፋ መንፈስ የታየበት ያልተለመደ ኢዮቤልዩ እንደነበር ገልጸው፥ ወደ ሮም የመጡ እና አሁንም ድረስ እየመጡ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን ማየታቸውን ተናግረዋል።

ስለ ዓለም አዎንታዊ ገጽታ ያሳዩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያስታወሱት ከንቲባው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ቡል ኦፍ ኢንዲክሽን’ ተብሎ በሚወጣው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው እንደጠየቁት የተስፋ ምልክቶችን የሚጠራ እጅግ የበለጸገ ይዘት እና ጥልቅ መንፈሳዊ እሴቶች ያለው ኢዮቤልዩ እንደነበር ገልጸው፥ ከዚህም ባለፈ ሮም እራሷን እንድታድስ እና እራሷን እንድትቀይር ያነሳሳ ለከተማዋ በጣም አስፈላጊ ኢዮቤልዩ እንደነበር አስረድተዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 2024 ወደ ካፒቶሊን ሂል በመጡበት ጊዜ ስለ ኢዮቤልዩ የጸሎት እና የንስሐ ጉዞ አድርገው ሲናገሩ ከመለኮታዊ ምሕረት ከጌታ ጋር ሙሉ እርቅን ለማግኘት እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው፥ በተመሳሳይ ጊዜ ብፁዕነታቸው የኢዮቤልዩ በዓል እንዴት በከተማይቱ ገፅታ ላይ በጎ ተጽእኖ እንደሚያሳድር፣ እይታዋን እንደሚያሻሽል እና መሃል ከተማውን ከዳርቻው ጋር በተሻለ ሁኔታ እንደሚያገናኝ አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መንፈሳዊ ነጋዲያንን በተሻለ መንገድ እንድንቀበል እና በተመሳሳይ ጊዜ የኢዮቤልዩ እሴቶች በከተማው ፊት እንዲታዩ መጋበዛቸውን የገለጹት ከንቲባ ሮቤርቶ፥ በበርካታ ተግባራት ይህንን መልዕክት በተግባር ለማዋል ሞክረው እንደነበር እና ይህም በመሆኑ ሮም ይህን ኢዮቤልዩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተቀበለችው ከመልካም ግንኙነት እና ተግባቦት አንፃር እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በዚህ ምክንያት የቅድስት መንበር ለህዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ እንዲሁም የቅድስት መንበር የኢዮቤልዩ ዋና ሰው ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ ሪኖ ፊሲ-ቻላ ጋር በመሆን በርካታ የኢዮቤልዩ ዝግጅቶች በከተማዋ ውስጥ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲዘጋጁ ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ የማርሽ ባንዶችን እና ወንድማማችነትን ያጣመረው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ኢዮቤልዩን ጨምሮ የተለያዩ ልምዶች የታዩበት ጊዜያት በከተማው አደባባዮች መታየታቸው እና ከሮማውያን ጋር ተቀላቅለው የጉዞአቸውን እና የተስፋቸውን ትርጉም ማስተላለፋቸውን በመግለጽ፥ ይህም ልዩ ትዝታ እንዳለሁ እና በከተማቸው ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ እጅግ የሚያምር፣ ያልተለመደ ኢዮቤልዩ እንደነበር አስረድተዋል።

እንደ አንድ ሮማዊ እና እንደ አንድ ከንቲባ ያለፈውን ቅዱስ ዓመት እንዴት እንዳከበሩት የተጠየቁት ከንቲባው፥ እርሳቸው በአደራ የተሰጣቸው የመንግስት የኢዮቤልዩ አስተባባሪነት ሚና ከከንቲባነት ሚና ጋር ተዳምሮ ስለነበር በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ሲሰሩ እንደነበር ገልጸው፥ አንዳንድ ጊዜ በጣም አድካሚ ነገር ግን ጥልቅ የሆነ እርካታ የሚሰጥ በጣም ጥሩ እና አስደሳች ትውስታ እንዳላቸው ጠቁመው፥ ከተማዋ ስለ ተከበረው ኢዮቤልዩ አመስጋኝ መሆን እንዳለባት እና ሮም ለኢዮቤልዩ ታላቅ ቁርጠኝነት ማሳየቷን እና በርካታ በጎ ፈቃደኞች ማበርከቷን፥ ነገር ግን ከተማዋ ከዚህ ኢዮቤልዩ ብዙ ገንዘብ እንዳገኘች መዘንጋት እንደሌለበት፣ ብሎም የከተማዋ ገጽታ መሻሻሉን አስታውሰዋል።

ከንቲባ ሮቤርቶ በቃለ ምልልሱ የትኛው የኢዮቤልዩ ወቅት ወይም ክስተት በጣም እንዳስደነቃቸው ተጠይቀው፥ በርካታ በጣም ልብ የሚነኩ ጊዜያት እንደነበሩ በማስታወስ፥ ለአብነትም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለወጣቶች ኢዮቤልዩ ከመጡት ወጣቶች ቡድን ጋር ቁርስ የበሉበትን አጋጣሚ፣ እንዲሁም በጥንታዊው ‘ሰርከስ ማክሲሞስ’ አደባባይ የተደረጉ የኑዛዜ መርሃ ግብሮች ከልብ መገረማቸውን ፤ እነዚያ ሁሉ ወጣቶች ተሰልፈው የሰላም እና የወንድማማችነት እሴቶችን ሲገልጹ የበለጠ የሚያምር፣ ፍትሃዊ እና የተሻለ አንድነትን እንደሚያመለክቱ ጠቁመው፥ እነዚህ ወጣቶች በጠራራ ፀሀይ ስር በደስታ መንፈስ በጋራ ተሰብስበው ሲታዩ መንፈስን እንደሚያረካ የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የወንድማማችነት መንፈስ በታየበት በታዳጊዎች ኢዮቤልዩ አማካይነት በጣም ጥንታዊ በሆነው በታዋቂ ስሜቶች ታሪክ ውስጥ ሥር የሰደዱ የሃይማኖት ዓይነቶችን ማየት አስደሳች እንደሆነ ገልጸዋል።

ወደ ሮም የመጡ የኢዮቤልዩ ተሳታፊዎች በርካታ ገፅታዎች እንደነበሯቸው እና እነርሱን መመልከቱ የሰው ልጅ በታሪክና በባህል የተለያየ ቢሆንም በተመሳሳይ ጊዜ ሁሉም ወንድማማች እና እህትማማች እንደሆኑ ያሳያል ብለዋል።

‘በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ እንኳን ሳይቀር ሁልጊዜም በአዎንታዊ መልኩ አብረን እንሰራ ነበር’ በማለት በከተማው አስተዳደር እና በቫቲካን መካከል ያለው ትብብር የገለጹት ከንቲባው፥ ብዙ ጊዜ ወደ ቫቲካን በሚወስደው ዋናው መንገድ መጀመሪያ ላይ ስለሚገኘውን ‘ፒያሳ ፒያ’ አደባባይ ሲናገሩ ትርጓሜው “ሌላውን ሰው የመቀበል አደባባይ” እንደሆነ ይናገሩ እንደነበር አስታውሰው፥ ይህም ማለት ምንም እንኳን ዛሬ በዓለማችን የፖለቲካ እና የመንግስት ዓለማዊ ተፈጥሮ መርህ በጥብቅ የተመሰረተ ቢሆንም፥ የጋራ የሆነ ነገርን ፍራቻ ወይም ድንበር መሻገርን በተመለከተ ስጋት ሳያስፈልግ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የቅድስት መንበር በሮም መገኘት አዎንታዊ ግብዓት መሆኑን አሳስበዋል።

ከንቲባው ‘ፒያሳ ፒያ’ የጣልያን ግዛት ውስጥ የሚገኝ አደባባይ ቢሆንም ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ጋር በመሆን የሁለትዮሽ አደባባይን በመመስረት፥ ከሎጀስቲክ አንፃር ከ150,000 እስከ 200,000 የሚደርሱ ሰዎችን መያዝ የሚችል አንድ ቦታ መፍጠር እንዳስቻለ አብራርተዋል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንዲሁም

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ከጋዜጠኛው የተጠየቁት ከንቲባ ሮቤርቶ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በጣም ጠንካራ እና ጥልቅ እንደነበር ጠቁመው፥ ብፁዕነታቸው ቀደም ሲል ካደረጉት ጉብኝት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ ካፒቶሊን ሂል ለመመለስ የመረጡት ሮም በኢዮቤልዩ ውስጥ ስላላት ሚና ጠቃሚ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለሮም ከተማ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን እና መንፈሳዊውን ገጽታ በአስደናቂው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ማመላከታቸው ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን ስለሚሰሩ ሥራዎች ዓይነት እና ጣልቃገብነቶች መመሪያ በመስጠት እንደነበር ገልጸዋል።

ከንቲባ ሮቤርቶ በሌላ በኩል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጣም አስፈላጊ ነገር ለማድረግ መምረጣቸውን እና ይሄም እጅግ አስገርሟቸው እንደነበር አስታውሰው፥ ብፁዕነታቸው ለከተማው የሲቪል መንግስት ትኩረት ለመስጠት ሲሉ የሮም ጳጳስ ወይም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መቀመጫ የሆነውን የቅዱስ ጆን ላተራን ባዝሊካን ለመጎብኘት በሄዱበት ጊዜ ካፒቶሊን ሂል ላይ ለአፍታ ለመቆም መምረጣቸውን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጥልቅ መንፈሳዊነት እና በተመሳሳይ ጊዜ እንደ ሥራ እና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተፅእኖ ለመሳሰሉ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት መስጠታቸው በጣም ያስደንቃቸው እንደነበረም ጭምር ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ሮም ሰላም የሰፈነባት ከተማ መሆኗን እና ዓለም አቀፋዊ የሰላም መልዕክት የሚወጣባት ከተማ መሆኗን የገለጹት ከንቲባው፥ እ.አ.አ. በ 2033 የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ የሚታወስበት ኢዮቤልዩ እንደሚከበር በማስታወስ፥ ይህም የሮም ከተማ በርካታ፣ ብዙዎቹ በስኬት የተከናወኑት ለቅድስት መንበር ምስጋና ይግባውና ዋና ዋና ዝግጅቶችን የማዘጋጀት ችሎታን እንደሚያጠናክር ገልጸው፥ ከተማዋ ሰላምን እና የአካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ ስብሰባዎችን የምታስተናግድ ሲሆን ይህም በጣሊያን እና በቅድስት መንበር መካከል ያለው የጠበቀ ትብብር ተጨማሪ እሴት አካል መሆኑን አስረድተዋል።

“በርካታ አወንታዊ ተግባራትን ሰርተናል” ያሉት ከንቲባው፥ ነገርግን የኢዮቤልዩ በዓል በመልካም ሁኔታ መከበሩ ችግሮችን፣ ድህነትን እና መገለልን እንደማያጠፋ፥ ሆኖም ግን ይህ አወንታዊ ኃይል እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንዲሁም መከፋፈልን እና ስብራትን ለመቀነስ አቅም እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የከተማቸው የመስተንግዶ አቅም ወደሚጠብቃቸው ፈተናዎች መቅረብ እንዳለበት በማሳሰብ አጠቃለዋል።

 

 

02 Jan 2026, 15:43