ሞዛምቢክ ከሳምንታት ከባድ ዝናብ በኋላ ከባድ የጎርፍ አደጋ  ደርሶባታል ሞዛምቢክ ከሳምንታት ከባድ ዝናብ በኋላ ከባድ የጎርፍ አደጋ ደርሶባታል  

የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ከባድ የጎርፍ አደጋዎች ተባብሰው እንዲከሰቱ ማድረጉ ተነገረ

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ሳይንቲስቶች ያካሄዱት ጥናት እንደሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥ በቅርብ ጊዜ በተከሰተው አስከፊ የአየር ሁኔታ ላይ ያለውን ተጽእኖ ያሳያል ማለታቸው ተነግሯል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በደቡባዊ አፍሪካ ክፍሎች ላይ እየደረሰ ያለው የጎርፍ አደጋ እየተባባሰ የመጣው የሰው ልጆች የአየር ንብረት ለውጥ እንዲከሰት በሚያደርጓቸው በጎ ያልሆኑ ተግባራት ምክንያት እንደሆነ ይፋ የተደረገው አዲስ ጥናት አመላክቷል።

የዓለም የአየር ንብረት ትንበያ ተመራማሪዎች የእነዚህን ክስተቶች መንስኤዎችን ሲመረምሩ ባገኙት ውጤት በሞዛምቢክ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሰሜናዊ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባብዌ ሃገራት በአስር ቀናት ውስጥ ብቻ የአንድ ዓመት የዝናብ መጠን መዝነቡን አረጋግጠዋል።

በእነዚህ ሃገራት የተከሰቱት የጎርፍ አደጋዎች ታኅሣሥ 17 የጀመረው እና ከጥር ወር መጀመሪያ ጀምሮ ተጠናክሮ በቀጠለው እጅግ ከባድ እና የማያባራ ዝናብ ውጤት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካባቢዎች በአንድ ቀን ከ200 ሚሊ ሜትር በላይ የዝናብ መጠን መመዝገቡ ታውቋል።

በዚህም ምክንያት በመኖሪያ ቤቶች እና በመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት የደረሰ ሲሆን ከ100 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው እና ከ300,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸው ተገልጿል።

በሞዛምቢክ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕንፃዎች በጎርፍ መጥለቅለቃቸው የተነገረ ሲሆን፥ በደቡብ አፍሪካ እና በዚምባብዌ ደግሞ መንገዶች እና ድልድዮች መውደማቸውን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ሳይንቲስቶች ጥናቱን ያካሄዱት የአየር ንብረት ለውጥ በአስከፊ የአየር ሁኔታ ላይ ያለውን ተጽእኖ ለመገምገም እንደሆነ ተነግሯል።

በየ 50 ዓመቱ ብቻ የሚከሰት ክስተት
በሳይንቲስቶቹ ግኝት መሰረት፣ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ከመሆኑ የተነሳ የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር በየሃምሳ ዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚከሰት የገለጹ ሲሆን፥ የጥናቱ ተባባሪ ጸሃፊ እና በኔዘርላንድ የሚቲዎሮሎጂ ተቋም ከፍተኛ የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑት ኢዚዲን ፒንቶ ጥናቱ ምን ያህል የአየር ንብረት ለውጥ የቅርብ ጊዜውን የጎርፍ መጠን እንዳወሳሰበው በእርግጠኝነት ማወቅ አለመቻሉን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ሳይንቲስቱ በሰዎች ምክንያት የሚፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ለ40 በመቶ የዝናብ መጠን መጨመር ብቸኛው አሳማኝ ማብራሪያ እንደሆነ ጠቁመው፥ በዚህም ምክንያት የተጠበቀው ከፍተኛ የዝናብ ወቅት ከፍተኛ ጎርፍ ማስከተሉን እና የአካባቢውን ማህበረሰቦች ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ክልል ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ የተለመደ ቢሆንም በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት አደጋዎች መጠን በሳይንቲስቶቹ ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠሩ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በሞዛምቢክ ውስጥ የሚያልፉት ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ወንዞች መኖራቸው በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ ያለውን ቀውስ ማባባሱ ተነግሯል ።

የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ክልሎች ላይ ያለውን ተፅእኖ የበለጠ ለመረዳት ተመራማሪዎቹ በአፍሪካ የአየር ንብረት ሞዴሎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት የሰጡ ሲሆን፥ በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የአየር ንብረት ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፍሬደሪክ ኦቶ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “እኛ ያሉን ሁሉም የአየር ንብረት ሞዴሎች ከአፍሪካ ውጭ ናቸው” ብለዋል።

ስለዚህ አብዛኞቹ ሞዴሎች በቅርቡ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ምን ያህሉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደተከሰተ በትክክል ለመወሰን መቸገራቸውን አመላክተዋል።

30 Jan 2026, 13:04