ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የግብጽ ታላቁ ኢማም አል ታይብ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ በፈረሙበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የግብጽ ታላቁ ኢማም አል ታይብ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ በፈረሙበት ወቅት 

የአርሜኒያ - አዘርባጃን የሰላም ስምምነት የ2026 የዛይድ ሽልማትን አሸነፈ

የ ‘2026 የዓለም አቀፍ የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት’ ሽልማት በአርሜኒያ እና በአዘርባጃን መካከል ለተደረገው የሰላም ስምምነት እና በአፍጋኒስታን ሴት ህፃናት ትምህርት ማግኘት እንዳለባቸው ለምትሟገተው ዛርቃ ያፍታሊ መሰጠቱ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የ 2026 የዛይድ ሽልማት ለሰብዓዊ ወንድማማችነት አሸናፊዎች ጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ የሆነ ሲሆን፥ በተቋሙ ይፋዊ መግለጫ መሰረት የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ጥር 27 በሚከበረው የዓለም አቀፍ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ቀን አቡ ዳቢ በሚገኘው እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን መታሰቢያ በተሰራው ሐውልት እና የጎብኚዎች ማዕከል ውስጥ እንደሚከበር ተገልጿል።

ከሽልማቱ አሸናፊዎች መካከል ነሃሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በሁለቱ ሀገራት መካከል ታሪካዊ የሰላም ስምምነትን በዩናይትድ ስቴትስ የተፈራረሙትን የአርሜኒያ ሪፐብሊክ እና የአዘርባይጃን ሪፐብሊክ ልዑካን እንዲሁም በአፍጋኒስታን ህፃናት ሴቶች ትምህርት እንዲማሩ ለረዥም ጊዜ ስትሟገት ለቆየችው ዛርቃ ያፍታሊ ይገኙበታል።

ዓለም አቀፉ ኮሚቴ ከካውካሰስ ክልል እና አፍጋኒስታን አሸናፊዎችን ሲመርጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፥ ካውካሰስ የሩስያን፣ ጆርጂያን፣ አዘርባጃንን እና አርሜኒያን ክፍሎች ያቀፈ ጂኦግራፊያዊ ክልል መሆኑ ይታወቃል።

ሰላም እንደ ቀጣይ ጉዞ
መግለጫው እንደገለጸው ይህ በሁለቱ የካውካሰስ ክልል ሃገራት መካከል የተደረገውን ስምምነት ዕውቅና የመስጠት ውሳኔ በሁለቱም አገሮች የተካሄደውን “የሰላም፣ የውይይት፣ የማረጋጋት እና የግጭት አፈታት ሂደት” እውቅና እንደሚሰጥ እና እርቅ “አንድ እርምጃ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ጉዞ” መሆኑን አጽንኦት ይሰጣል ተብሏል።

ስምምነቱ በካውካሰስ ክልል ውስጥ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት እና ሰብአዊ ስቃይ ለማስቆም የታለመው “አርቆ አስተዋይ አመራር የሚመራ ታሪካዊ ውሳኔ ውጤት ነው” ተብሏል።

የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን “ይህን ታሪካዊ ስምምነት” ለመደገፍ የተደረገውን ጥረት በመገንዘብ ሽልማቱን “ታላቅ ክብር” ሲሉ ገልፀውታል።

የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ በበኩላቸው ሽልማቱ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መስራች የሆኑትን የቀድሞውን ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያንን ስም የያዘ መሆኑን በመጥቀስ የሽልማቱን አስፈላጊነት ያሰመሩበት ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እና በአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል ጣይብ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ለአፍጋኒስታን ልጃገረዶች ድምፅ
በመግለጫው ላይ ዛርቃ ያፍታሊ “ሙሉ ህይወቷን ለሴቶች እና ህፃናት የመማር መብትን ለማስጠበቅ የሰዋች ደፋር ሴት” ተብላ የተገለጸች ሲሆን፥ ዛርቃ በአፍጋኒስታን ውስጥ ከ100,000 ለሚበልጡ ሰዎች የትምህርት ግብዓቶችን፣ የስነ-ልቦና ድጋፍን እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንደሰጠች እና ይህም እጅግ በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚኖሩ ወጣት ሴቶች ተስፋን የሰጠ መሆኑ ተነግሯል።

በሽልማቱ “በጣም መነካቷን” ዜናው ከተሰማ በኋላ የገለጸችው ወይዘሮ ዛርቃ ያፍታሊ፥ ይህ ለአፍጋኒስታን ሴቶች “ጠንካራ እና ትርጉም ያለው መልዕክት ነው” በማለት ገልፃለች።

እውቅናው በተለይ በቀጥታ አውታረ መረብ ላይ ትምህርታቸውን ለሚማሩ ተማሪዎች እንዲሁም የሰላም፣ ደህንነት እና የአመራር ኮርሶችን ለመማር ለተመዘገቡ ወጣት ሴቶች ተስፋ እና ድፍረት የሚሰጥ መሆኑን ገልጻለች።

ውይይት እና አብሮ የመኖር ባህልን ማበረታታት
አሸናፊዎቹ የተመረጡት በገለልተኛ ዓለም አቀፍ የዳኞች ኮሚቴ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ በቅድስት መንበር የባህልና ትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጽህፈት ቤት ሃላፊ ብፁዕ ካርዲናል ሆሴ ቶለንቲኖ ዴ ሜንዶንካ ይገኙበታል።

የዛይድ ሽልማት ዋና ፀሀፊ የሆኑት ዳኛ መሀመድ አብደልሰላም ለአርሜኒያ እና አዘርባጃን እውቅና መስጠት የሽልማቱ ዓላማ የሆነውን ‘የውይይት እና አብሮ የመኖር ባህልን ማበረታታት እና ማሳደግ’ የሚያንፀባርቅ መሆኑን በመግለጽ፥ ስምምነቱ በካውካሰስ ወደ አራት አስርት ዓመታት የሚጠጋ ውጥረትን እና ግጭትን በማስቆም፥ ለሁለቱም ህዝቦች ለመጪው ጊዜ የጋራ እና የበለጠ አስተማማኝ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛዋ የዳኞች ኮሚቴ አባል የሆኑት የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል በበኩላቸው ኮሚቴው በተለይ ዛርቃ ያፍታሊ ጥልቅ በሆኑ ተግዳሮቶች በተሞላ አውድ ውስጥ ሴቶችን ለማብቃት ላሳየችው ቁርጠኝነት እውቅና ለመስጠት ፍላጎቱ እንደነበረው ገልጸዋል።

የኡዝቤኪስታን ፕሬዝዳንት አስተዳደር ኃላፊ ሳይዳ ሚርዚዮዬቫ የ 2026 ተሸላሚዎች ምርጫ ለሰላምና ለሰብዓዊ ክብር ያለውን ዓለም አቀፍ የሞራል ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አዲስ የተስፋ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጸዋል።

እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. በአቡ ዳቢ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና አህመድ አል ጣይብ ሰብዓዊ ወንድማማችነትን አስመልክቶ የተዘጋጀው ሰነድ ላይ የስምምነት ፊርማቸውን ማኖራቸውን ተከትሎ እና በሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ትሩፋት ላይ የተመሰረተው የዛይድ ሽልማት በሰብዓዊ ወንድማማችነት እሴት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ፣ ተስማምቶ የሚኖር እና ሩህሩህ ዓለም ለመገንባት አስተዋፅዖ ያደረጉ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን በማክበር ይሸልማል።

ሽልማቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከ19 ሀገራት ለመጡ 19 ተሸላሚዎች መሰጠቱ ተነግሯል።

20 Jan 2026, 16:23